>

ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ወደ አአዩ ተመልሷል! (ውብሸት ሙላት)

ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ወደ አአዩ ተመልሷል!

ውብሸት ሙላት
ከትላንት ጀምሮ አንዳንድ ሰዎች ከታማኝ ምንጮች ባገኘነው መረጃ መሠረት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሷል የሚሉ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣በብሔሩና በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ የማስተማር ውሉን አናራዝምም በማለት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መባረሩ ይታወቃል፡፡ የሌሎች ባለሥልጣናት ጫና ሊኖር ቢችም ዋናዎቹ ፊታውራሪ አባራሪዎች፣ውሉ እንዳይታደስ ያደረጉት ግን በዋናነት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ (አሁን የማሌዥያ አምባሳደር) እና በአጋዥነት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ካሳ ተክለብርሃን (አሁን አሜሪካ አምባሳደር) ናቸው፡፡
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አይደለም የዶክተር ዳኛቸውንና የዶ/ር መረራን ያህል ዕድሜ ያላቸው ቀርቶ 80 ዓመት የሞላቸው መምህራኖችም በማስተማር ላይ አሉ፡፡ ዶክተርን High School ያስተማሩትም ጭምር እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ውላቸው እየተራዘመላቸው አሉ፡፡ በፍልስፍና እና በፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍሎችም እንዲሁ ውላቸው እየታደሰላቸው ማስተማራቸውን የቀጠሉ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከመንግሥት የተለዬ ሐሳብ ቢኖራቸውም እንኳን  ባለመግለጻቸው ከማስተማራቸው የነቀነቃቸው የለም፡፡
አንዳንዱ ግጥምጥሞሽ ያስተዛዝባልም፤ያስድንቃልም፤ፖለቲካዊ ሴራውንም ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ሁለቱ አባራሪዎች የብአዴን አባላት ናቸው፡፡ አማራውን ውከልው ነው በእነሱ ቤት፡፡ ተባራሪው ደግሞ ብአዴን ያልሆነ፣የምናውቀው  አማራው ኢትዮጵያዊው ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ነው፡፡ ከሁለቱ ታራሚ ብሔሮች አንድኛው (አማራ) ስለሆነ የራሳቸውንም ከሌላ የተቀበሉትንም ጅራፍ አሳረፉበት፡፡
ዶክተር ዳኛቸውን ሲያባርሩት ሌላም ግፍ ፈጽመውበታል፡፡ ሁለቱ አባራሪዎች ተባብረው፡፡ ሰባት ዓመታት ያህል ካስተማረ በኋላ የሴባቲካል ፈቃዱን (የአንድ ዓመት እረፍት) ከልክለውታል፡፡ በርካታ ገጾች ያሉት አቤቱታ ከነማስረጃዎቹ ለፕሬዚዳንቱ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ቢያስገባ (እኔም አብሬ ነበርኩ) በማግስቱ ጧት “በጥልቀት እንደመረመርነው ፈቃዱ ማግኘት የሚችሉበት አግባብ የለም” በማለት ፕሬዚዳንቱ መለሱ፡፡
ከእዚያም ወደ አስተዳደር ፍርድ ቤት ለመሔድ የቦርዱን ውሳኔ ማግኘት አስፈላጊ ስለነበር ወደ ካሳ ተክለብርሃን ቢሮ (የፌደሬሽን ምክር ቤት) ቅሬታ አስገባ፡፡ የካሳ ተክለብርሃን (ፌደሬሽን ምክር ቤት) የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከዩኒቨርሲቲው መረጃ መሰብሰብ ቢጀምሩም አልቀጠሉበትም፡፡
ዶክተር ዳኛቸውም ከካሳ ቢሮ ቢመላለስ ቢመላለስ ከካሳ ዘንድ መፍትሔ ሳይገኝ የፌደራል ጉዳዮች እና አርብቶ አደር ሚኒስትር ሆኑ፡፡ አሁንም ምንም መፍትሔ ሳያገኝ አምባሳደር ሆኑ፡፡ የሴባቲካል ፈቃዱንም የአሁኖቹ ሁለት አምባሳደሮች በዚህ መንገድ ነፈጉት፡፡
ዶክተር ዳኛቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ውሉ ተቋርጦም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በተወሰኑ የትምህርት ክፍሎች የማስተርስ እና የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን አልፎ ማስተማሩን ቀጥሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቱ ከሕግ ትምህርት ቤቱ ፈቃድ ውጭ በቀጠሩትና የሕግና አስተዳደር ኮሌጅ ዲን ባደረጉት፣አሁን በወንጀል የሚፈለግ፣በዲስፕሊን ተከስሶ ቅጣቱን ፕሬዚዳንቱ ከማጽደቃቸው በፊት አገር ጥሎ በሔደው ዶክተር አማካይነት በሕግ ትምህርት ቤት ማስተማሩን አቆመ፡፡
የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ደግሞ የማስተርስ የኤክስቴንሽን ተማሪዎችን ያስተማረበትን ክፍያ፣በኮሌጅ ደረጃ የሚፈጸምን፣ እንዳይከፈለው ተደረገ፡፡ አንድ ዓመት ያህል ከቆዬ በኋላ  ክፍያውን በፕሬዚዳንቱ ትእዛዝ ያገደውንና በቀጥታ የሚመለከተውን ኃላፊ በወንጀል ጭምር እንደሚከሳቸው ፣ፕሬዚዳንቱንም ጭምር   እንደሚከሳቸው በቃል ማስጠንቀቂያ ለእዚህ ኃላፊ ሰጣቸው (ሰጠናቸው)፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚያው ሳምንት የዶክተር ዳኛቸው ክፍያ እንዲከፈል ደብዳቤ ጻፉ፡፡ ዶክተር ዳኛቸው ግን ለፕሬዚዳንቱ ማመልከቻ አላስገባም ነበር፡፡
በደብዳቤው መሠረት ጉዳዩ የሚመለከተው የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ክፍያውን ለመፈጸም እየተዘጋጀ እያለ በአጋጣሚ አንድ ሳምንት ገደማ ፈጀ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቀድመው የጻፉትን ደብዳቤ ይርሱት ወይም በወንጀል ከመከሰስ በመፍራት ክፍያው እንዲፈጸም በድጋሜ ደብዳቤ ጻፉ፡፡ ዶክተር ዳኛቸው ግን እንኳንስ ሁለተኛ ይቅርና አንድ ጊዜም ለፕሬዚዳንቱ ማመልከቻ አላስገባም፡፡ ሲጀመርም እንዲህ ዓይነት ክፍያዎች በኮሌጅ ደረጃ ብቻ የሚያልቁ ናቸው፡፡ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በሌሎች ኮሌጆች (ፕሬዚዳንቱ ስላልሰሙ ይመስላል) ያስተማረባቸውን ይከፈላል፡፡
ያው እንዲህ እንዲህ እያለ ዶክተር ዳኛቸውም ስድስት ኪሎ ግቢ ብቻ ማስተማር ተከልክሎ ቆዬ፡፡ በዚሁ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች በየክልሉ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች አልፎ አልፎ እያስተማረ ቆየ፡፡ ከዚያ አድማሱም ሆነ ካሳ ከዩኒቨርሲቲው ርቀው አንድኛቸው ወደ ምዕራብ፣ አንድኛቸው ወደ ምሥራቅ የዓለም ጫፍ ተሸኙ፡፡ ለዩኒቨርሲቲውም  ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ፡፡
የትምህርት ክፍሉ በመምህር እጦት እየተሰቃየ ባለበት፣ የውጭ ምሁራንን ቢቀጥርም ሳይመጡ በቀሩበት ሁኔታ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳኛቸው እንዲቀጠር ስለፈቀዱ፣ የአገራችን የፖለቲካ ንፋስ ስለተቀያየረ የትምህርት ክፍሉም በዛሬው ዕለት የቅጥሩን ጉዳይ  በደስታ ተቀብሎት (ኮሌጁም የሰው ሐብት አስተዳደሩም ጭምር)  ከእንደገና በኮንትራት ለመቅጠር የመጨረሻው ጫፍ ላይ ናቸው፡፡ የቀረው ነገር ቢኖር የቅጥር ደብዳቤ መቀበል ነው፡፡
“ላንቺ ይብላኝ እንጂ ውልሽ ለፈረሰው …” .እንዳለው ዘፋኙ ይብላኝ ለፕ/ር አድማሱ ጸጋዬ እና ለካሳ ተክለብርሃን እንጂ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋስ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊመለስ ነው፡፡ በቀድሞው ወንበሩ ፍልስፍናም ሊያስተምር ነው!!!!!!!!
(አንተ እያልኩ መጻፌ ጨዋነት ጎድሎኝ ሳይሆን ቀረቤታዬን ስለሚያርቀው ነው፡፡)
እንኳን ደስ ያለህ ዶክተር፣እጅግ በጣም ወደምትወደው ሥራ በመመለስህ!
በተያያዘ ተወዳጁ የተቃውሞው መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ሥራቸው ተመልሰዋል ።
Filed in: Amharic