>

አፋጣኝ እርምጃዎች ያስፈልጋ ል!!! (መሳይ መኮንን)

አፋጣኝ እርምጃዎች ያስፈልጋል!!!

መሳይ መኮንን
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ከጥቂት ሰዓታት በፊት በኢቲቪ መግለጫ ሲሰጡ አይቼ ነበር። አሁን ደግሞ ከስልጣናቸው መነሳታቸውን ሰማሁ። እኚህም ሰው ከቀን ጅቦቹ አንዱ ነበሩ ማለት ነው። ጉዳዩን በቀላሉ ማየት አደጋው ከባድ ነው። ዶ/ር አብይ እንዳሉት ጥቃቱ የተፈጸመው በሙያው በተካኑ ሰዎች ነው። በግልጽ ለመናገር ሁኔታውና ጊዜው አልፈቀደላቸውም እንጂ የህወሀት ሰዎች ያቀነባበሩት የግድያ ሙከራ መሆኑን ጠ/ሚር አብይ ያውቁታል። እናም ዶ/ር አብይ የፖሊስ ም/ል ኮሚሽነሩ ላይ የወሰዱት ፈጣን እርምጃ በእሳቸው ብቻ መቆም የለበትም። የፖሊስ መኪና እንዲሰማራ እስከማድረግ የደረሰ የግድያ ሙከራ ለነገ የሚያድር ውሳኔ እንደማያስፈልገው በግልጽ ያመላከተ ነው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ አቶ ዘይኑም መፈተሽ መበርበር አለባቸው። ጉዳዩ እስኪጣራ ኮሚሽነሩ ከሃላፊነታቸው መነሳት ግድ ነው። የህወሀትን ትብታብ እየበጣጠሱ የመጡት ጠ/ሚር አብይ እስከመጨረሻው የማስወገዱ ስራ ላይ ዛሬ ሳይሆን አሁኑኑ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገኙበትን እንዲህ ዓይነት መድረክ ጥበቃ በማድረግ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ይልቅ  ሃላፊነት ያለበት የፌደራል ፖሊስ በመሆኑ ያንን ቤት ከህወሀት ቆሻሻ ሳያጸዱ ወደ ሌላ ስራ መግባት የለባቸውም። ደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ የተጀመረውን የማራገፍ እርምጃ ጊዜ ሳይሰጡ ማጠናቀቅ አለባቸው።
 ጠባቂዎቻቸው ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው የዛሬው አደጋ በግልጽ ያሳየ ነው። እንደሚግ የሚወነጨፉ፡ ተወርዋሪና ተስፈንጣሪ የሆነ አካላዊ ብቃት ላይ የደረሱ፡ በቅጽበት የሚጠብቁትን ሰው ደህንነት አስተማማኝ የሚያደርግ እርምጃ የሚወስዱ፡ በዘርፉ ሙያም ሳያንሳዊ በሆነ ስልጠና የላቀ ደረጃ የደረሱ ጠባቂዎች እንጂ ዛሬ እንዳየነው ቀርፋፋና ደካማ የሆነ ጥበቃ በሚያደርጉ ሰዎች መታጀብ የለባቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩን የኢትዮጵያ አምላክ ከተወረወረባቸው ሰይፍ አዳናቸው እንጂ በጠባቂዎቻቸው ዝርክርክነትና ቀርፋፋነት ቢሆን ኖሮ የጥቃቱ ውጤት የከፋ ይሆን ነበር።
ህወሀት ያስታጠቃቸው በሺዎች የሚቆጠር ሰዎች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ኤርሚያስ ለገሰ በተደጋጋሚ ያነሳል። ይህንን የሚያስረግጡ መረጃዎች እየወጡ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዩ ትዕዛዝ እነዚህን ሰዎች በአስቸኳይ ትጥቅ ማስፈታት አለባቸው። ዛሬ እንደተሰማው ሲቪል የለበሱ መሳሪያ ደብቀው የያዙ ሰዎች ታይተዋል። አንዲት እብድ መስላ ጥቃት ያደረሰች ሴት ሽጉጥ ሳይቀር ታጥቃ እንደነበረ የአይን ምስክሮች ሲናገሩ ሰምቼአለሁ። ጠ/ሚሩ ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ህወሀት ለማን፡ ምን ዓይነት መሳሪያ እንዳስታጠቀ መረጃው አላቸው። በአድራሻ እየተፈለጉ የታጠቁትን መንጠቅ ወሳኝና ቁልፍ እርምጃ ነው።
ህዝባችንም አንዳንድ ጊዜ በስሜት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ምናልባት ቦምቡ የፈነዳባት የፖሊስ መኪናን ያቃጠለው በድርጊቱ የተቆጣው ህዝብ ከሆነ ጥሩ እርምጃ አለነበረም። ምክንያቱም በመቃጠሉ ሊገኝ የሚችል ማስረጃ አብሮ ይወድማልና ነው። ድርጊቱን ፈጻሚዎች ማስረጃ እንዳይገኝ ሆን ብለው አቃጥለውት ሊሆንም ይችላል። አንድ የፖሊስ ባልደረባ ነኝ የሚልንና በህዝቡ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰውም እንደዛ መደብደብ አልነበረበትም። ህይወቱ ቢያልፍ ከእሱ ሊገኝ የሚችል ማስረጃና መረጃ ቀልጦ ይቀር ነበር።
እንደሰማነው አደጋውን ያደረሰው አካል መጠነ ሰፊ ጉዳት ለማድረስ እቅድ ነበረው። ያልፈነዱ በርካታ ቦምቦች በተለያዩ የሰልፉ አከባቢዎች መገኘታቸው ታውቋል።  ህወሀት ቀሽም ነው። ነውረኛ ነው። ክፉ መንፈስ የተጠናወተው አውሬ ነው። ይህ ዛሬ ያደረገው የጥፋት ተግባር ቢሳካለት ኖሮ ኢትዮጵያ ላይ ሊከተል የሚችለው እልቂት እጅግ ዘግናኝ ይሆን ነበር። ፍላጎታቸው በእርግጥ ይሐው ነው። አሁንም የሚተኙ አይሆንም። ጠ/ሚር አብይ አህመድ ደህንነቱንና መከላከያው ላይ የሚወስዱት እርምጃ በዘገየ ቁጥር ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችል ሰይጣናዊ ተግባራቸውን ከመፈጸም ወደ ኋላ አይሉም። ጌታቸው አሰፋ የተባለው የቀድሞ የቶርቸር ሚኒስትር የህወሀት ስልጣን እየተዳከመ ከመጣ ይህን መስሉ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲሰናዳ እንደነበረ መረጃዎች ይፈነጥቃሉ። እንደእኔ እምነት ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ የተወሰኑ የህወሀት ባልስልጣናትን በቁጥጥር ስር ማድረግ ትልቁን አደጋ ለማጥፋት ወሳኝ እርምጃ ይሆናል።
ከሆነ በኋላ መቆጣት፡ ጸጉር መንጨት ትርጉም የለውም። የዛሬው በዚህ መልኩ ባያልፍና እንደፈጻሚዎቹ እቅድ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ የሚከተለው በጣም አስፈሪ ይሆን ነበር። አሁንም ስጋቱ አለ። ይበልጥ አስጨናቂው ነገር ከፊት ተደቅኗል። የዛሬው ምልክት ነው። ማስጠንቀቂያ ነው። የህወሀት የጥፋት እጆች ለእልቂት እየተወለወሉ መሆኑን ተረድተናል። መዘናጋት አያስፈልግም። የዛሬው ሰይፍ የተወረወረው ጠ/ሚር አብይ ላይ እንዳልሆነ ህዝባችን ተረድቶታል። ኢትዮጵያ ላይ ነው። ከምንጊዜውም በላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መቆም እንደሚገባ የዛሬው ጥቃት አመላክቷል።
(በነገራችን ላይ የዛሬው የዶ/ር አብይ ንግግር አስር ጊዜ ቁጭ ብድግ አድርጎኛል። ኢትዮጵያዬ እንዲህ በመሪ አንደበት ስትወደሺ እንደመስማት የሚያስደስት ምን ነገር አለ?!!)
ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርካት!!!!
Filed in: Amharic