>

የትናንትናው ጥቃት ዒላማውን ቢመታ የሀገራችን መፃኢ እድል ምን ይሆን ነበር?!? (አፈንዲ ሙተቂ)

የትናንትናው ጥቃት ዒላማውን ቢመታ የሀገራችን መፃኢ እድል ምን ይሆን ነበር?!?

ይህንን የጻፈው: አፈንዲ ሙተቂ
እኔ የምለው? ታሪክን አታውቁትም ማለት ነው? ታላላቆቻችሁን አትጠይቁም ማለት ነው? ይገርማል።
እስቲ አንድ ነገር ላስታውሳችሁ። የሩዋንዳው ጭፍጨፋ እንዴት ነበር የተጀመረው? ረሳችሁት ማለት ነው?
የዘመኑ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጁቪኔል ሀቢየሪማና እኤአ ሚያዚያ 6/1994 ከቡሩንዲው አቻቸው ጋር የሚጓዙበት አውሮፕላን በኪጋሊ ከተማ ባለው የአየር ማረፊያ ለማረፍ ሲቃረብ ከምድር በተተኮሰ ጥይት (መትረየስ) ተመታ። ሁለቱ ፕሬዚዳንቶችም ተገደሉ። በዚህም የተነሳ በስልጣን ጉዳይ ለዘመናት በጥርጣሬ በሚተያዩትና ሁቱ እና ቱትሲ በሚባሉት የሀገሪቱ ታላላቅ ጎሳዎች መካከል ከባድ ጦርነት ተቀሰቀሰ። የሰው ልጅ እንደ ከብት መተራረድ ጀመረ። እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ በሁለት ወር ውስጥ ብቻ 800 ሺህ ሰው ተጨፈጨፈ። (ጭፍጨፋው በዚህ ፍጥነት የተካሄደው በመታወቂያ ወረቀት ላይ የጎሳ ስም ተለይቶ ይጻፍ ስለነበረ ነው)።
በኋላ ላይ ነገሩ ሲጣራ አውሮፕላኑ የተመታው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር በተኮሰው መሳሪያ መሆኑ ታወቀ። እንግዲህ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር በዚህ ዘዴ ህዝቡን አስጨርሶና አጨራርሶ ነው ስልጣን የያዘው።
—-
ትናንትና (ሰኔ 16/2010) ለኛ የታሰበው ይህ ነበር።  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገደሉ ኖሮ የሚጠብቀን አደጋ ይኸው ነው። ለዚህ ደግሞ የማጅራት መቺው ስርዓት በቂ የሆነ የጥላቻና የበቀል ዘር በመላው ሀገሪቱ ዘርቷል። በመታወቂያ ላይ ብሄርን ለይቶ መጻፍ፣ ሰውን በብሄር እየለዩ ከትውልድ ስፍራው ማፈናቀል፣ ብሄርና ጎሳ እየለዩ ከስራ ማባረር፣ ብሄርን ከብሄር ጋር ማጋጨት፣ ለጥቂት ብሄሮች ብቻ የልዩ መብት ተጠቃሚነት መስጠት፣ በሀይማኖት ለይቶ ማጥቃት፣ በተለያዩ ሀይማኖት ተከታዮች መካከል ጥላቻን መዝራት፣ ቤተ እምነቶችን እያፈረሱ በሌሎች ሀይማኖት ተከታዮች ማሳበብ ወዘተ በሰፊው ይካሄዱ ነበር።
በሰለጠነው ሀገር የሚሠሩ የኢንተሌጀንስ መሥሪያ ቤቶች የየሀገራቱን ጸጥታና ደህንነት ነው የሚያስከብሩት። የሀገራችን የኢንተሊጀንስ መሥሪያ ቤት ግን ጥላቻንና ሁከትን ሲዘራ ነበር የቆየው። ክፋቱ ደግሞ የስርዓቱን መሠሪነት አውቀን በመንቃት ፈንታ ሁላችንም ስሜትን እየተከተልን ጎል የምንገባለት መሆኑ ነው።
እስቲ አስቡት! የትናንትናው ጥቃት ዒላማውን ቢመታ የሀገራችን መፃኢ እድል ምን ይሆን ነበር? እኔ እንጃ!! የኢትዮጰያ ህዝብ ሃይማኖተኛ በመሆኑ እንደ ሩዋንዳው ዓይነት የከፋ አደጋ ላይከሰት ይችላል። ነገር ግን ሁከትና ግርግር ተፈጥሮ ማጅራት መቺዎቹ የተመኙት ነገር ሊሰምርላቸው ይችል ነበር። ይኸውም ህዝቡ የተጎናፀፋቸውን ድሎች መንጠቅና የቀድሞውን የአፈና አገዛዝ መመለስ ነው።
ጓዶች!
ብዙዎቻችሁ ከትናንት ጀምሮ ስለ ፖሊሶቹ መኪና እየጻፋችሁ ነው። በኛ በኩልስ የሚጠበቅብንን አድርገናል? በጭራሽ! ጥንቃቄ በጣም ይጎድለናል። እጅግ በጣም! ከፍተኛ መዝረክረክ ታይቶብናል። እስቲ ባለፉት ጥቂት ቀናት ያየናቸውን እንከልስ!
 1 ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ኤርሚያስ ለገሰ እና አቶ ጀዋር መሀመድ የስርዓቱን መሰሪነት በመጠቃቀስ ጥንቃቄ እንድናደርግ እየደጋገሙ ሲመክሩን ነበር። ምክራቸውን በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ አድርገናልን? አላደረግንም።
2. በወያኔ ስርዓት ሰውን ደብድቦ ማሰቃየት በዚህ ሳምንት የተጀመረ ይመስል ከሀዋሳ የተቀዳውን ቪዲዮ በዚህ ወሳኝ ወቅት በሶሻል ሚዲያው ላይ ማሽከርከር  ምን ይባላል? የሰልፉ ቀን እስኪያልፍ ድረስ መታገስ አይቻልምን? በፌስቡክ ላይ በቆየሁበት ዘመን በመቶ የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ቪዲዮዎች ደርሰውኛል። ጊዜውንና ወቅቱን ያልጠበቀ ከሆነ ሼር አላደርገውም። ብዙዎች ግን የሰልፉ ቀን እስኪያልፍ በመጠበቅ ፈንታ እየደጋገሙ ቪዲዮውን ወደኔ ኢንቦክስ ይልኩታል (ቲሽ! በዘበዛ! ብሽቅ! ትልቅ የምትሉት ሰው ሁሉ ነው እንዲህ የሚያደርገው)።
አዎን! ቪዲዮው በአዋሳ ተቀድቷል። ነገር ግን በዚህ ሰዓት ከማጅራት መቺዎቹ ቤት የተለቀቀ ለመሆኑ አልተጠራጠርኩም። ስለ ፍትሕ መናገር ተገቢ ነው። ነገር ግን ሀገር እንዳይበጠበጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። “አጥፍተውን ሊጠፉ የተነሱ የቀን ጅቦችን እንከላከል” የተባለው ለዚሁ ነው።
3. ሰልፉ ቦታ ስትሄዱ ከክብር ትሪቡኑ ራቅ ብላችሁ ቁሙ ተብላችሁ ነበር። ሰልፈኞቹ የሚቆሙበት ስፍራ ከክብር ትሪቡኑ (ከመድረኩ) ቢያንስ ሽጉጥ ተተኩሶ ጉዳት ማድረስ የማይችልበት ርቀት ያህል ሊኖረው ይገባ ነበር። ነገር ግን ተግባራዊ አልተደረገም። የህንዶቹ ኢንዲራ ጋንዲና ራጂቭ ጋንዲ (እናትና ልጅ)፣ የፓኪስታኗ ቤናዚር ቡቶ፣ የኮንጎው ፓትሪስ ሉሙምባ የሞቱበት ሁኔታ ተረስቷል ማለት ነው።
ውጥረት ባለበት ሀገር መሪው በአደባባይ ስብሰባ ላይ ከተገኘ ተመሳሳይ ነገር መከሰቱ የሚጠበቅ ነው (በነገራችን ላይ በኋላ ላይ በወጣው ቪዲዮ እንዳየነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገው ጥበቃ በጣም የሳሳ ነው። ፈጣሪ በጥበቡ አትርፎናል እንጂ ትልቅ ጥፋት ተደግሶልን እንደነበረ በቀላሉ መረዳት ይቻላል)።
4. “ሶሻል ሚዲያውን ስትጠቀሙ የብሄርን ስም እየጠቀሳችሁ ማንንም አትዝለፉ” የሚለው ምክርም እየተሰራበት አይደለም። ፓርቲና ህዝብን መለየት፣ ፓርቲና ቋንቋን መለየት፣ ግለሰብንና ህዝብን መለየት የሚሉት መርሆዎች በትክክል እየተሰሩበት አይደለም። በዚህ ሳቢያም የተወሳሰበውን ችግራችንና ፈተናችንን ማቃለል አስቸጋሪ እየሆነብን ነው።
ወዳጆች
ማንኛችንም በፌስቡክ በምንለጣጥፈው ነገር እየተከፈለንና የተለየ ጥቅም እያገኘንበት አይደለም።  በአንፃሩ ብዙ ነገር እየሰዋንበት ነው እዚህ ላይ የምናድረው (በየጊዜው የሞት ዛቻ ጭምር ሲሰነዘርብን እንዳለየን ሆነን ነው የምናልፈው፣ የግል ስራችንንም መዝጋት ሲኖርብን እንዘጋለን)።
እኛን እዚህ ያሰባሰበን ሀገራችንና ህዝባችን ነፃነትን በማያውቁ ጨካኝ ገዥዎች እጅ መውደቃቸው ነው። ገዥዎቻችን የዘረጉት የማጅራት መቺ ስርዓት ከሚወድቅበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ተባብረንና ተደማምጠን የመከራውን ቀን በጋራ ትግል ልናልፈው ይገባል።
 ካልተደማመጠን የቀን ጅብ ብቻ ሳይሆን የቀን ቀበሮ፣ የቀን ተኩላ፣ የቀን ዘንዶ፣ የቀን ድራጎን፣ የቀን እፉኝት እስከ ቤታችን ድረስ ገብተው እየዘነጣጠሉ ይበሉናል። ስለዚህ እንደማመጥ! እንተባበር! እንደመር! አንድ እንሁን!! ይህንን ስርዓት በጋራ አሽቀንጥረነው ልጆቻችን በነፃነት፣ በእኩልነትና ከዘረኝነት በፀዳ መንፈስ እንዲያድጉ እድል እንፍጠርላቸው።
——
ድል ለሰፊው ህዝብ!
Injifannoon Ummata Bal’aaf!
ዓወት ንሓፋሽ!
Victory to the Mass!
አል-ዒዘቱ ሊ-ሽ-ሻዕብ
Filed in: Amharic