ውድድ አብይን!
ደረጄ ደስታ

አገር የሱን ምስል ከደረቱ አድርጎ ለጥይት ደግሞ ደረቱን ሲሰጥለት ማየቱ ትንግርት ነው። ህዝብ ደግሞ ያው መቸም ከወደደ “ብሔሩን ጥሎ አበደ” ነውና መንደርና ሰፈሩን ትቶ “ኢትዮጵያ!” ሲል ዋለ። ደግሞ ያው አንድ ፍሬ ልጅ ወዲያው አዛውንት ሆኖ እንደ ስብከትም እንደ ምርቃትም ያለ ነገር ይናገራል። አንዳንዱማ እንዲያውም ቡራኬ ሁሉ ይመስላል። ቢፈላሰፍስ ምን ይለዋል! ብቻ ዘና ብሎ አገር ዘና እሚያደርግ ንግግር ሲናገር አፍ ያስከፍታል። “እሚሻክረውን አፍ ሁሉ ዘግተህ አድማጭ ጆሮ ያደረግከው አምላክ ምን ይሳንሃል!” እያሉ ለምስጋና እሚያጉተመትሙ ባልቴት ከሰልፈኛው መካከል አይኖሩም ብሎ ማን ይከራከራል። ወጣቱማ አይቶ እማያውቀውን፣ ቢያውቅም ለዘፋኝ በኮንሰርት እሚያደርገውን ዓይነት ፈንጠዚያ ለአገር መሪ ሲያሳይ ዋለ። አንተ አንቱየዋ የተባሉት መሪም ከፍ ሲሉ እያከበሩ ዝቅ ሲሉ እየተከበሩ መድረኩን ያደራርጉታል። እሱም ሆኑ እሳቸው የተለዩ ሰው ናቸው።

መቸም ሰው አንድ ነገር ቢሆን ኖሮ ውዳሴው ሰማይ ይነካ ነበር። ተርፏልና ተብሎስ ባይቀር ምን ነበረበት። አንተ እምንለው ወጣቱ አብይ ያሳሳል። እሳቸው እምንላቸው አብይ ደግሞ ፖለቲከኛ፣ ጮሌ፣ ነገ በቃላቸው እሚገኙም እማይገኙ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ። ያንን ያልገባኝ ይመስል ማንም እንደጅል አስር ጊዜ መላልሶ እንዲያሳስበኝ አልሻም። በየጊዜያቸው እንዳመጣጣቸው አስተናግዳቸዋለሁ። መንግሥት እሚደግፈው ከፈለገ አንድ ሺ ካድሬና ተቋማት እንዳሉት አውቃለሁ። ስለዚህ እሚያፈነዱት ተቋም እንኳ ባይሆን መቸም ሊደግፉት ሳይሆን ሊቆጣጠሩትና በዓይነ ቁራኛ ሊያዩት እሚገባ ተቋም እንደሆነም አውቃለሁ።
የእስከዛሬው አብይ ግን አገር የተደሰተባቸው፣ የተገፉና የተበደሉትን እሽሩሩ እሚልባቸው፣ ውድ ልጁ ናችው። እኔ ደግሞ ያን በዛሬው ሰልፍ ፈንድቆና አገር አስፈንድቆ ያየሁት ልጅ ደስታው በቅጽበት ተቀምቶ፣ አይኑ እምባ ተሞልቶ ስለሁኔታው መግለጫውን ሲሰጥ ሳየው አዘንኩ። ያንን ለጋ ተስፈኛ ልጅ በሰውነቱ ብቻ ወደድኩት። ውድድ አብይን! እንኳን አተረፈህ! – ማለቴ እንኳን አተረፍዎት!