>
5:13 pm - Monday April 20, 3722

ከዶ/ር አብይ አመራር ጋር መደመር (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

/ር አብይ አመራር ጋር መደመር

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

በቅድሚያ የፍቅር ሐዋርያና የኢትዮጵያ ማንዴላ ለሆኑት ዶ/ር አብይ፤ በሕይወታቸው የተቃጣውን እኩይ ሴራ ስንመለከት፤ ከደጋፊነት አልፈን በፍጥነት ወደ ረዳትነት መሸጋገር ሀገራዊ ግዴታ እንደሆነ መገንዘብ ይገባናል። ለማመንታት ጊዜ የለም። በቃ። በዚህ የመደመር መርሀ ግብር ውስጥ መከናወን ያለባቸው አራት አብየት ጉዳዮች አሉ።

1ኛ/ ጥናት፦ የኢትዮጵያን አስተዳደር በተመለከተ ያስከተለውን ግጭትና የሕዝብ መፈናቀል መዘዝ ይጠና ያሉትን ዶ/ር አብይን በዚህ ጥናት ላይ መሳተፍና የመፍትሄው አካል መሆን። ባለፈው 44 ዓመታት የሞከርናቸውን የለውጥ መንገዶች በሙሉ መፈተሽና ወደ ብርሃን ማምጣት።

2ኛ/ ትምህርት፥ መከላከያው፥ ፍርድ ቤት፥ ሚዲያ፥ ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ ሆነው ለዲሞክራሲ ዘብ እንዲቆሙ ዶ/ር አብይ የጀመሩትን የማስተማር ሂደት ላይ ተባባሪ በመሆን የጨለማውን ጊዜ አካሄድ በእውቀት ብርሃን መግለጥ። ጊዜው የፍቅር ይቅርታና መደመር ነውና ይህንን አዲስ ርእዮተ ዓለም በሁላችንም ዘንድ እንዲሰርፅ መማርና ማስተማር።

3ኛ/ ለውጥ፥ መከላከያው፥ ፍርድ ቤት፥ ሚዲያ፥ ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት መዋቅራዊና ሕጋዊ ለውጦች ላይ በሚደረገው ሂደት በተሳታፊነት ራስን በማቅረብ፤ ለውጡ ከውስጥ ወደ ውጭ እንዲዘልቅና ለተዐማኒ ምርጫ መሰረት እንዲጥል ማድረግ። ሕዝብም በነፍስ ወከፍ ልውጠትን በማካሄድ ለአዲሱ የኢትዮጵያ የብርሃን ዘመን መዘጋጀት።

4ኛ/ ፀሎት፥ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ተዐምራዊ ጉዞ የኢትዮጵያ አምላክ እጅ ያለበት ስለሆነ፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እኩይ እንዳያኮላሽብን በየቤተ እምነታችን ሆነን ወደ ፈጣሪ መጮህን ማብዛት። ይህም የፀሎት አጀንዳ በገሃድ ስናደርግ እርስ በርሳችን በፍቅር ሰንሰለት እያያያዘን ወደ አንድነት ያመጣናል።

ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ በሚያስኬድ ሽግግር ላይ ትገኛለች። ለዚህ የሽግግር ሂደት የሽግግር መንግስት ማቋቋም ለዛሬ መፍትሄ አይደለም። ነገር ግን የሚያስፈልገው በሕዝብ ዘንድ ተዐማኒ የሆኑትና የሽግግር ድልድይ ከሆኑት ከዶ/ር አብይ ጋር መደመር ነው። ይህንን አስተሳሰብ ለመፈተሽ እንዲረዳን ከዚህ የሚከተሉትን 8 ነጥቦች አነሳለሁ።

1ኛ/ በአብሮነት መላ መፍጠር። መፍትሄን እንደ ስጦታ ከመጠየቅ በአብሮነት መላ መፍጠር ይሁንልን። ከእኚህ የኢትዮጵያ ልጅ ዶ/ር አብይ ጋር ተያይዘን በመስራት፤ የዶ/ር አብይ የሽግግር ድልድይ ጋር መደመር ይሻለናል። አጋርነትን መግለፅ ማለት በሩቅ ሆኖ “ጥሩ ጅማሬ ነው” ብሎ መደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ ቀረብ ብሎ ዲሞክራሲ እንዲወለድና ለእውነተኛ ምርጫ ተአማኒነት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በአብሮነት ማሳለጥ ነው።  

2ኛ/ የዶ/ር አብይ አህመድ ስብዕና። ዶ/ር አብይ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያዊነትን ገፅታ እያንፀባረቁ ይገኛሉ። አንድም በፓርላማ ሆነው ሲናገሩ አንበሳ ናቸው ያሰኛል። ደግሞ የእርቅን ዘንባባ ይዘው ለውስጥም ለውጭም የፍቅር ጥሪ ሲያቀርቡ ርግብ ናቸው ያሰኛል። ከዚህ እልፍ ስንል ደግሞ ተበጣጥሰንና አጥር አበጅተን ስንባላ፥ ከኢትዮጵያ አልፈው የምስራቅ አፍሪካ ድንበር አልታያቸው ብሎ አንድ አፍሪካን ሲያልሙ፤ ምድር ላይ ትል ከሚለቅመው ዶሮ ይልቅ ከፍ ብሎ የሚበረው ንስር ናቸው ብለን እንደመድማለን። የኢትዮጵያዊነትን ምንነት በስብዕናቸው የሚያንፀባርቁትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ፤ ጥሪያቸውን ተቀብለንና በወንበር ዙሪያ ተቀምጠን እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማስወለድ ለእርሳቸው የአዋላጅነት ዕድል ለመስጠት የሚታመኑ ናቸው። ምክንያቱም በዶ/ር አብይ አህመድ አመራር ምክንያት ሕዝብ በአደባባይ ፍቅሩን ሰጣቸው። እሳቸውም የሕዝብን ድምፅ በመስማት ከምንም በላይ ለሕዝብ ታማኝነታቸውን በየዕለቱ ሲገልጡ ይታያሉ።

3ኛ/ ኢትዮጵያ የተዐምር ሀገር። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ጉዞ በዚህ አጭር ጊዜ ያየነው ከተለመደው ወጣ ያለ ነው። ተዐምር ሆኖብን በእውነት የኢትዮጵያ አምላክ አለ አልተባለምን? ታዲያ በተዐምር የተጀመረው ይህ ሂደት በተዐምራዊነቱ እንዲቀጥል እምነት ልናጣ አይገባም። በሁሉም ጎራ የተሰለፉትን የኢትዮጵያ ድንቅዬ ልጆቿን አሳትፋ፤ ዓለም ከዚህ በፊት ያላየውን አዲስ መንገድ ኢትዮጵያ ማሳየት ትችላለች። ሌሎች ሀገሮች የኢትዮጵያ መንገድ ብለው የሚጠሩት አካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቀየስ እንነሳ።  

4ኛ/ የትግሉ ባለአደራና ጠባቂ ሕዝብ ነው። እናውቅልሃለን ብለን ሕዝቡን ከራሳችን ጎን ማሰለፍ ከእንግዲህ አይቻልም። የሚያዋጣው ራሳችንን ከሕዝብ ጎን ማሰለፍ ነው። የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ባለቤት ሕዝብ ነው። ባለአደራውም ሕዝብ ነው። ከእንግዲህ ሕዝብ ራሱ ንጉስ ሆኖ በምርጫ ካርድ አገልጋይ የሚሆነውን መንግስት እስኪመርጥ ድረስ አያርፍምና፤ ሁላችንም የሕዝብን ድምፅ እያደመጥን ከዶ/ር አብይ አመራር ጋር መንገዳችንን በአብሮነት መጓዝ ጥሩ ነው።

5ኛ/ የራስን የቤት ስራ መወጣት። ድሮ ድሮ ምርጫ ስለሌለ ሁሉም ተቃዋሚ መሆን ነበረበት። ግማሹ በሰላማዊ ትግል፥ ሌላው በትጥቅ ትግል ግዴታ ስለሆነ ተሰለፈ። ተወያይቶ ሀሳብን ያማከለ ህብረት በማድረግ ለመቀናጀት ፋታ አልነበረውም። ዛሬ ግን ሁኔታው እየተቀየረ ነው። ጊዜው የተበታተነው ተፎካካሪ በአስተሳሰብ ዙሪያ ሃይሉን በማቀናጀት ፈርጠም ያለ ተፎካካሪ በመሆን መቅረብ የሚጠበቅበት ወቅት ነው። ጊዜው የትግል ስልት የሚያስቀይር ነው። የተፎካካሪው ውበት እንዲወጣና እንዲያስደምመን፤ የራስን የቤት ስራ መወጣት ይጠይቃል። ታዲያ ይህንን የራስን የቤት ስራ ለመስራት ጥድፊያ ላይ እንሁን።  

6ኛ/ ልዩ ብቸኛ አጋጣሚ። ሁልጊዜ ከዜሮ መጀመር ለአሁኑ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ መልስ አይደለም። ያለውን ስርዐት ድምጥማጡን አጥፍቶ፤ አዲስ ሽግግር መንግስት እናቋቁም ብለን ከምንታገል፤ በሕዝብ የፀደቀውን የዶ/ር አብይ አህመድ ድልድይ የመሆን ልዩ ብቸኛ አጋጣሚ በመጠቀም፤ ወደ እውነተኛ ምርጫ መሄድ ላይ ማተኮር ይሻላል። ይህን የተጀመረው የለውጥ መንገድ እንዳይሰምር በመንግስትና ኢህአዴግ ውስጥ ሆነው እንቅፋት የሚሆኑትን ወንድሞቻችንን አይጠቅማችውም ብለን ልንሞግታቸው ያስፈልጋል።

7ኛ/ ሕዝብ የወለደው አመራር። ብዙ ጊዜ የሽግግር መንግስት ከአምባገነን መሪ ለመላቀቅ፤ ወይም መንግስት በአመፅ ምክንያት መግዛት ሲሳነውና ሲፍረከረክ፤ ከዜሮ ለመጀመር ሲገደድ የሚደረግ ክስተት ነው። አሁን ያለው አመራር ግን በሕዝብ ምርጫ የመጣ ባይሆንም በሕዝብ ትግል የተወለደ ነው። እነ አቶ ለማ፥ አቶ ገዱ፥ አቶ ደመቀና ሌሎችም የለውጥ አራማጆች ተጋዳይነትና በኢትዮጵያ ወጣቶች ደምና እንግልት የመጣ ነው። ስለዚህ ይህንን አክብሮ ከዚህ ሕዝባዊ ከሆነ አመራር ጋር መደመርና ሌሎችም እንዲደመሩ ተግቶ መስራት መልካም ነው።

8ኛ/ አዲስ ጊዜ፥ አዲስ አመለካከት። ሁሉም የሽግግር መንግስት እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዳመጣ ታሪክ አይነግረንም። ትላንት በጨለማው ዘመን የሽግግር መንግስት ስንል ከርመን፥ ዛሬ ጊዜው ተቀይሮ ብርሃን ሲወጣም፤ ይህ የድሮ ሀሳባችን ጊዜውን ይመጥነው እንደሆነ ሳንለካው፤ ትላንት የፃፍነውን ወረቀት ዛሬም ያንኑ ብቻ ማንበብ እውቀት አይሆንም። ከሩቅ በመሆን፤ የማያባራ ትዕዛዝ ለዶ/ር አብይ ከመስጠት፤ ጠጋ ብለን በጋራ የምንስማማበት የዲሞክራሲ ውልደት ፍላጎት ላይ ተመስርተን ወደ ውይይት ማምራት ይሻላል።

የኢትዮጵያ ልጆች ከሩቅ ከቅርብ ለዶ/ር አብይ ተልዕኮ መሳካት ሲረባረቡ ማየት፤ ይህ ህዝብ ታሪክ ሊሰራ ቆርጦ መነሳቱን ያሳያል። አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን፥ አብሮ መስራትም የተካነ እንደሆነ ሊያስረግጥ ተነስቷል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፤ ይባርካታልም።

ኢሜል፡ ethoStudy@gmail.com

Filed in: Amharic