>

ድብቅ ጦሩን ማምከን (ተመስገን ደሳላኝ)

(የትላንቱ የሽብር ጥቃት በታሪካችን የመጀመሪያው ይመስለኛል፤ ከዚህ ቀደም በሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች በተሰበሰቡበት አደባባይ መሰል ሙከራ እንኳን መደረጉን አላውቅም፤ ተፅፎም አላነበብኩም፤ ሌላው ቀርቶ የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግል በይፋ ያወጀችው ኢህአፓም ብትሆን ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን ጎዳና ላይ አድፍጣ ለመጥበስ አሴረች እንጂ፣ እንዲህ በአየነው መልኩ ሕዝብን መድፈሯንም፣ መናቋንም፣ መጥላቷንም አልሰማንም። …ፈጣሪ ሰማዕታቱን ያስብ፤ የቆሰሉትን ደግሞ ጤናቸውን ይመልስ።)

አሁንም አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ዒላማውን በንፁሃን ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ተደጋግሞ ሊከሰት የሚችልበት ክፍተት ገና አልተደፈነም። ጠ/ሚ አብይ አህመድም ከጥቃቅኖቹ ይልቅ፣ አስቸኳይ ውሳኔ ወደ ሚያሻቸው ጉዳዮች ትኩረቱን ማዞር ‘ለነገ የማይለው’ የቤት ሥራው ነው። ሰሞኑን የደህንነት አለቃ የነበረው ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ከኃላፊነት የተነሱ በርካታ የተቋሙ የአመራር አባላት የትዳር- ጓደኞች የሚያሽከረክሩትን የመንግስት መኪና እንዲያስረክቡ ተደርጓል (በነገራችን ላይ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ ሹመት ሊያገኝ ይሁን-አይሁን ባላረጋግጥም የእርሱ ባለቤት ብቻ እንድትመለስ አለመታዘዟን ሰምቻለሁ።)

ይህ አሰራር ህጋዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀዳሚው ግን ከተማይቱን ከጥፋት ማዳን ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ በሕዝቡ ውስጥ የተበተነውን ስፍር-ቁጥር የሌለው የጦር-መሣሪያን መሰብሰብ ነው። ሆነ ተብሎ መሳርያ ከታደላቸው እልፍ-አእላፍ ሲቪሎች በተጨማሪ በሠራዊቱ የተለያዩ ግምጃ-ቤቶች ላይ የተቀነባበሩ አያሌ ዘረፋዎች ቁጥራቸውን ለማወቅ የሚያስቸግር ዜጎችን ማስታጠቁ ይገመታል። አይበለውና የተፈራው ቢደርስ ይህ ድብቅ-ጦር በአንድ ጀንበር አዲስ አበባን የመታገያ ሜዳ አድርጎ፣ አብዘተን የሰጋንበትን ሀገራዊ-ፍርሰት እና የእርስ-በርስ እልቂት ሊያከስትብን ይችላል።

ስለዚህም መንግስት የሚመለከታቸው ተቋማት የሚወከሉበትና ተአማኒነት ያለው ግበረ-ኃይል አቋቁሞ፣ ቢያንስ ለሁለት ቀን መስሪያ ቤቶች ተዘግተው፣ የዝውውር እንቅስቃሴዎች ታግደው የቤት-ለቤት ፍተሻ አካሂዶ መሳሪያዎቹን በመሰብሰብ ከተማዋን ከተደገሰላት መልከ-ብዙ ጥፋት መታደግ ይኖርበታል። በአሰሳው ወቅት የመሳሪያ-ፍቃድ ያላቸውንም ቢሆን የፊርማና የማህተብን እውነተኛነት ብቻ አይቶ በዋዛ ማለፉ አግባብ አይደለም። እንዴትና በምን መስፈርት ፍቃዱ እንደተሰጣቸው ከአዋጁ ጋር እያመሳከሩ በደንብ ማጣራት ያስፈልጋል።

የ1969 ዓ.ም የደርግን እና የ1983 ዓ.ም የወያኔን የቤት-ለቤት ፍተሻ ተሞክሮን በመውሰድ፣ እንዲሁም ሠብዓዊ መብት-ሳይጣስ፣ ማንገላታት፣ ማዋከብ፣ ማስፈራራት… ሳይፈፀም፣ አክብሮት ባልተለየው መንገድ ፍተሻውን ማካሄድ ታሳቢ ይሁን። በዚህ አጋጣሚ መሳሪያው የሚያዝባቸው ዜጎችም ትጥቁን ከፈቱ በቂ ነው። በወንጀል መክሰሱ ከተጀመረው የይቅርታ ልማድ ይቃረናልና።

በአናቱም በመከላከያ፣ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ስር ያሉ የጦር-መሳሪያ፣ የፈንጂ፣ የቦንብ፣ የጥይት… ግምጃ-ቤቶች ላይ ከወትሮ የተለየ ጥበቃና ቁጥጥር የማድረጉን አስፈላጊነት እንዳይዘነጋ።

Filed in: Amharic