>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9076

 ክቡርነትህ እባክህ፤ ለህዝብህ ታስፈልገዋለህ !!! (ሃራ አብዲ)

የአዲስ አበባዉ ሰላማዊ ሰልፍና የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ በሰላም አደባባዩን መልቀቅ፤   

 ክቡርነትህ እባክህ፤ ለህዝብህ ታስፈልገዋለህ !!!! (ሃራ አብዲ)

ከየትኛዉም ቁምነገር ብነሳ፣ይህን ጽሁፍ መጀመር ቀላል አልሆነልኝም። ከሰልፉ ዉጥን ሀሳብ፤፤ ለሊቱን ወደ መስቀል አደባባይ ሲጎርፍ ካደረዉ ህዝብ ደስታ፤ ታይቶ ከማይታወቀዉ የህዝብ ወፈ-ሰማይ፤ እንደ ጠል ከሚያረሰርሰዉ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ንግግር፤ ሰላምና ወንድማማችነት ከናኘበት የህዝብ አንድነት፤ሌት ከቀን ተግቶ ያንን አስገራሚ ዝግጅት ካከናወነዉ አስተባባሪ ኮሚቴ፤ ወይንስ፤ ከቦምብ ፍንዳታዉ~~~

ለመሆኑ፤ ምን እስኪያደርጉ ነዉ የሚጠበቀዉ??

ያ፣ሁሉ የህዝብ ሱናሚ ነጋ ፤ አልነጋ ብሎ መስቀል አደባባይ ከተመ። ፍቅር ተሰብኳል አና፤ህዝቡ በፍቅርና በወንድማማችነት ስሜት በደስታ አስተያየቱንና ለለዉጡ ያለዉን ድጋፍ ሲሰጥ አረፈደ፤ ቅዳሜ ሰኔ 16, 2010 እኢአ ። ከሀገራችን ሰማይ የራቅነዉ  ደግሞ፣ በአካል ተገኝተን ሰልፍ ለመዉጣት ባንታደልም፤ «እንቅልፍ ለምኔ »ፕሮግራሙን ተከታተልን። ልባችን ለሰልፍ ተነሳ፣ እኛም ከቴሌቪዢን ፊት ለፊት ተቀመጥን፤ ለወትሮዉ ከመጤፍ የማይቆጠሩትን እነ ኢቲቪን ከፍተን በስስት ታደምናቸዉ፤ ዘመን ሲለወጥ,,,ምን የማይለወጥ ነገር አለ??

የምንኖርበት መልክአ-ምድር ሳይለያየን፤ ነፍሳችን የተጠማችዉን ፍቅርና አንድነት በምናብ ዋንጫ ስንጎነጭ አርፍደን/አምሽተን፤ በማሳረጊያዉ፤ የቦምብ ፍንዳታ ተሰማ!! እርግጠኛ ነኝ፤ ብዙ ሚሊዮኖች ያን «ደ~~~ፍ ፤ ያለዉን፤ የስጋት ድምጽ፤ በብርሀን ፍጥነት ጆሮችን መዝግቦታል፥፥፥ በጥፍራችን አቁሞናል!!

እንደ አብዛኛዉ ወገኖቼ እኔም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በሰልፈኛዉ መካከል ይገኛል መባሉ ምቾት አልሰጠኝም ነበር። ለአፋታም  አይኖቼን ከመድረክ እንቅስቃሴው ሳልነቅል ፤ፍንዳታዉን ስሰማ ትንፋሽ አጠረኝ!! ምን እንደተፈጠረ በፍጥነት ባለመገለጹ ደግሞ ስጋቴን ጨመረዉ። ለነገሩ፤ ያ ሁሉ ህዝበ-ሰራዊት፣ተስፋ ላደረግንበት ለዉጥ ድጋፉን ለማሳየት እየመጣ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  እንዴት ሊቀር ይቻለዋል?

ከዚያ ሁሉ የፍቅር ና የመቻቻል ብስራት በሗላ ቦምብ ተወርዉሮ፣ ቁጥራቸዉ በርካታ የሆነ ዉድ ወገኖቻችን  ተጎዱብን። ታዲያ ይህንን ሴራ ያቀናበሩ ጨካኞች፤ የፍቅር ወሬ ሰምተዉ ያዉቃሉ??

ለመሆኑ፤ ምን እስከሚያደርጉ ነዉ የሚጠበቀዉ??

-ህወሃት በፖለቲካ የሽንፈት ብልኮዉን ከተከናነበ ወዲህ፤ ግብረ-አበሮቻቸዉ ፤በየ ድረ-ገፁ ያዙን፤ ልቀቁን  ካላጠፋን፣ካላተራመስን፤ በማለት ያለመታከት ጥፋትን እየጋበዙ መሆናቸዉ ይታወቃል።

-ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ህዝባችንን አሰቃይተዉ፤ ሀገራችንን አደህይተዉ፤ራሳቸዉንና ተባባሪዎቻቸዉን አበልጽገዉ የሚኖሩት ማንነት በይፋ እየተገለጸ ነዉ።

-እነዚሁ አካላት እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በስልጣን ላይ ናቸዉ። ጥቂቶቹ በጡረታ ቢሰናበቱም በአንድ የስልክ ጥሪ ጉዳያቸዉን የሚፈጽሙላቸዉ ቱባ ወንጀለኞች፤ አሁንም ባላስልጣን ናቸዉ።

-በጣት ከሚቆጠሩት ፤ከነ ጌታቸዉ አሰፋ ገለል መደረግ በቀር፣ አሁንም በስለላና መረጃ መስሪያ ቤት ዉስጥ የጥፋት ተልእኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ድርጅታዊ አቅሙ ያላቸዉ በርካቶች እንደሆኑ ይታመናል።

-ሳሞራ የኑስ ጡረታ ቢወጣም በርካታ የህወሃት ጄኔራሎች ከነ ትጥቃቸዉና ፣ከነታጣቂዎቻቸዉ በመንግስት ዉስጥ ያለ መንግስት ሆነዉ አፍጠዉ ቁጭ ብለዋል።

-ሕወሃት በጦር መሳሪያ ግዢ ተጠምዶ መክረሙንና እጅግ በርካታ የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ዉስጥ ለማስገባቱ በርካታ መረጃዎች ተዘግበዋል።

-ይህ በገፍ ተገዝቶ የገባዉ መሳሪያ ለምን ጥቅም ሊዉል ታስቦ እንደተገዛ መጠርጠር ቢቻልም፤

የመሳሪያዉ ክምችት የት ፣ የት እንደሚገኝና መሳሪያዉ ከግምጃ ቤት እንዲወጣ ቢፈለግ የሚያዙበት እነማን እንደሆኑ ያታወቃል ወይ? እነዚያ የጦር መኮንኖች ግምጃ ቤቱ በቁጥጥራቸዉ ስር እያለ ለጥፋት ተልእኮ እንደማያዉሉት እርግጠኛ መሆንስ ይቻላል ወይ?

-ይህንንና ይህንን የመሳሰሉ በርካታ ጥያቄ የሚያጭሩ ሁነቶች በዙሪያችን ከበዉን ስላሉ ፣ጉዳዮቹ ተገቢዉ ጥንቃቄ ተወስዶባቸዋል ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

መቼም ጥቅሙ የተነካ፣ ባለስልጣን፤ በተለይም በብዙ ወንጀል እጆቹ የረከሱበት ባለስልጣን «ሳልቀደም ልቅደም»  ብሎ አያስብም ብሎ መገመት የዋህነት ነዉ።

-የሰይጣን ጆሮ አይስማና አነ ጄነራል መርእድ ንጉሴ ያን የመሰለ አሳዛኝ ክስተት ላይ የወደቁት፣ ቀድመዉ እርምጃ መዉሰድ ባለመፈለጋቸዉና ጫካኔዉን በመጠየፋቸዉ ነበር። እርግጥ ሌሎችም ሁኔታዎች ለምሳሌ (የጄነራል ተስፋዬ ወልደስላሴ፤ እነጄነራል መርእድን መክዳት)«ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸዉ ብለዉ እነ መንግስቱ እንዲያቅራሩ አስችሎአቸዋል። እያልኩ ያለሁት ወንጀለኞቹን ልቅምቅም አድርገን ለቁርስ እናድርጋቸዉ አይደለም። የዶ/ር አብይ መርህ የሰለጠነ ፖለቲካ ነዉ። ሀገር ወዳዶች ሁላችን ስንናፍቀዉ የኖረ ተወዳጅ መርህ ነዉ። እያልኩ ያለሁት ግን፣ጥቅማቸዉ የተነካ፣ የሚነካና ፣ወንጀለኞች የሆኑ፤ባለስልጣናት ጉዳት የማድረስ አቅም ( capacity) እንዳይኖራቸዉ ማድረግ ለእነሱም ወንጀላቸዉን ሊያቀል ይችላል፤ በሌሎች ላይም ጉዳት ማድረስ አይችሉም ነዉ።

አሁን ባለዉ ሁኔታ ግን፣ የጠ/ሚ/ር ደህንነት ~~~~ትንሽ ያሳስበናል። ለምሳሌ፤ ዶ/ ር አብይ፤ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል t ተገኝቶ በህዝብ መካከል በቦምብ ፍንዳታዉ የተጎዱትን ሲጎበኝ መዋሉ በጣም ደስ ያሰኛል።በሌላ በኩል ደግሞ፤እንደትናንቱ አይነት የተነጣጠረ ጥቃት፤ ዳግም እንደማይፈጠር ምን ማስረገጫ አለን?

እንግዲህ፤ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከኮሎኔልነት እስካገራችን የመረጃ መስርያ ቤት አዋቃሪነት ድረስ ድንቅ የሰራ መሪ በመሆኑ፤ እንደ ጌታ ክርስቶስ «የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእኔ ላይ ጣሉት» እንዲለን እንፈልጋለን።

እስከዚያዉ ድረስ፤ ክቡርነትህ፤ ለቤተሰብህ ብቻ ሳይሆን ለህዝብህ ታስፈልገዋለህ!!

ለአሁኑ፣ ዶ/ር አብይ በሰላም ተመልሶልናል። ለወደፊቱም ከህዝቡ ጋር የሚመጣዉን ለመቀበል ቁርጠኛ ነዉ!! እኛም ከጎኑ ነን።    

እግዚአብሄር ኢትዮጵያና ህዝብዋን ይባርክ!!   

Filed in: Amharic