>

በተቃጠለችው የፖሊስ መኪና በጭካኔ የተረመረመው ህዝብ ዜናው ለምን እና በማን ተደበቀ?!? (ኢሳያስ መኩሪያ)

በተቃጠለችው የፖሊስ መኪና በጭካኔ የተረመረመው ህዝብ ዜናው ለምን እና በማን ተደበቀ?!?
ኢሳያስ መኩሪያ
“ምንም እንኳን በጋዜጥኝነት ሙያ ለሦስት አስርት ዓመታት ለተጠጉ ጊዜያት ባገለግልም ላለፉት ስምንት ዓመታት ግን በየትኛውም የመገናኛ ብዙኃንም (Medium) ሆነ ዓምደ-መረብ (Website) ላይ አንድም ፅሁፍ በሥሜ አውጥቼ አላውቅም፡፡ አንድ ሁለት ሦስት ጊዜ ቤተሰቦቼን አልያም ተፈጥሮን የሚያሳዩ ምስሎችን (Photographs) በማኅበራዊው የመረጃ መለዋወጫ ዓምደ-መረብ (Facebook) ላይ ለጥፌ የነበረ ከመሆኑ በስተቀር፡፡
ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም  “ሹም ካዘዘው ስሜት የወዘወዘው” ሆኖበት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለሠላማዊ ትዕይንት በወጣው ወፈ-ሰማይ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን በዐይኔ ያየሁትንና በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኬም (Mobile phone) የቀረጽኩትን የአሸባሪዎች የሽብር ድርጊት በስሜ ዓደባባይ አውጥቼ ማውገዝ የሠውነት መገለጫዬ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እኔ እስከ አሁን በተከታተልኳቸው የመገናኛ ብዘሁሃን ዘገባዎች ላይ በዕለቱ የደረሰው አደጋ “በተወረወረ የእጅ ቦንብ” የደረሰ ጥፋት ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መዘገቡ ምናልባትም መረጃውን ባለማግኘታቸው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ስላሳደረብኝ ከቦንቡ ጥቃት በተጨማሪ ለአዕምሮ በሚከብድ መልኩ በፖሊስ መኪና የተረመረመውን የሠው ልጅ ጥፋት የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል (Video Footage) ማጋራት አለብኝ ብዬ በማመኔም ነው፡፡
በዚህ የፖሊስ መኪና የተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት የሆነው ሎንዶን፣ ፓሪስ ወይም ኒውዮርክ ላይ ቢሆን ኖሮ በስንቱ ዓለም-አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የአሸባሪ ድርጊት (Terrorism Acts) ተብሎ ይወገዝ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡
ይህ ግን እንዴት በኢትዮጵያዊ ዜጋ በኢትዮጵያውያን ላይ በኢትዮጵያ ምድር ተፈፀመ? ብለን ቆም ብለን ልንጠይቅ ይገባል እላለሁ፡፡
 ለመሆኑ በእለቱ በፖሊስ መኪና በጭካኔ የተረመረመው ህዝብ ዜናው ለምን እና በማን ተደበቀ?!?
ተጠርጣሪዎቹን በአግባቡ እና ከፍተኛ የሙያ ሥነ-ምግባርን በተላበሰ ምርመራ ማጣራት ተደርጎ ለፍርድ ማቅረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ ከንዴት እና ከበቀል በፀዳ መንፈስ ልንጠይቅ የሚገባው ሌላው ጥያቄ ደግሞ የዚህ ድርጊት ፈፃሚዎች እንዲያው ምን አይነት ብሶትና ምሬት ቢደርስባቸው ነው እንዲህ መሰሉን ዘግናኝ ድርጊት በህዝብ ላይ ለመፈፀም የተነሱት? የሚል መሆን አለበት፡፡
በመጨረሻም በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል (Video Footage) ላይ የምትታየው የፖሊስ ተሸከርካሪ ከጥፋት ድርጊቷ በኋላ በተቆጣው ህዝብ እንድትቃጠል መደረጓን ዘግይቶ ደግሞ በእሳት አደጋ ተከላካዮች  ሙሉ ለሙሉ ከመውደም መትረፏን ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
Filed in: Amharic