>

በውጭ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እደግፋቸዋለሁ አለ - ኢሳት

በውጭ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እደግፋቸዋለሁ አለ
(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 18/2010)
በውጭ ሃገር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እንደሚደግፍና ከጎናቸው እንደሚቆም ይፋ አደረገ።
እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበርም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጎን በመቆም አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ባወጣው መግለጫ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጎን እንደሚሰለፍ ከማረጋገጥ ባሻገር በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት አውግዟል።
 “በሃገራችን ሕዝብ ዘንድ እየታየ ያለው ፍቅርና አንድነት የማያስደስታቸውና እኩይ ተግባር የተጠናወታቸው ክፉዎች የዚህን ታላቅ ሕዝብና ታላቅ መሪ አላማ እንዲሁም የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማደናቀፍ በመስቀል አደባባይ ያደረሱትን የቦምብ ጥቃት ቅዱስ ሲኖዶሱ ያወግዛል”ያለው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ ሁሉም የእምነት መሪዎች ድርጊቱን እንዲያወግዙም ጥሪ አቅርቧል።
ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ለተጎዱት ምህረትን የተመኘው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ በእለቱ የነበረው ደስታ በሃገራችን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነበር ሲል ገልጿል።
“እግዚአብሔር አምላክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን መሳሪያ አድርጎ ሃገራችን ኢትዮጵያን ለዘመናት ከኖረችበት የግድያና የምቀኝነት ጨለማ አውጥቶ የፍቅርና የአብሮነት ሸማ አልብሷታል።–ለዚህም እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ብሏል በመግለጫው።”
የሕዝቡ አንድነትና ፍቅር እንዲሁም ለመሪያቸው የሚያቀርቡት ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ባልደረቦቻቸውን ይበልጥ ከሕዝብ ጋር ልብ ለልብ ያስተሳስራቸዋል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም:-  የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር በዋሽንግተን ዲሲ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፉን ገልጿል። 
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 27 አመታት ሲያልመውና ሲታገልለት የቆየው የትግል ሒደት፣በዶክተር አብይ አመራር ተቀባይነት በማግኘቱ ከለውጡ ሃይል ጎን ተሰልፈናል ብሏል።
“ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የምናስተላልፈው መልዕክት ይህንን የተቀደሰ የለውጥ ጅምር ወደ ታለመለት አላማ ለማድረስ ከዶክተር አብይ አህመድና ከለውጥ ሃይሉ ጎን እንዲሰለፍ ነው “ሲል የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪውን አቅርቧል።
ለውጡን በመደገፍ ሒደቱን ለመቀልበስ የሚንቀሳቀሱትን ነቅቶ መጠበቅ የሁሉም ሃገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ያሳሰበው የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር እኛም ለዚህ የተቀደሰ አላማ ከሕዝቡ ጎን ተሰልፈናል ብሏል።
Filed in: Amharic