>

ሰለሞን ተስፋዮ ተሊላን ለቀን ጅቦቹ አሳልፈን አንስጠው! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ሰለሞን ተስፋዮ ተሊላን ለቀን ጅቦቹ አሳልፈን አንስጠው!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ወልቂጤ ሄደው ” በጉራጌ ተከብቤያለሁ!” ሲሉ በጭንቅላቴ ከመጡት ሰዎች መካከል ቺፍ ኦፍ ስታፉ ፍፁም አረጋ፣ የብሮድካስቲንግ ሐላፊው ሰለሞን ተስፋዮ ተሊላ እና የፓሊስ አዛዡ ዘይኑ ናቸው።
 እስከማውቀው ድረስ ሰለሞን ተስፋዮ ተሊላ በብቃቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት ይችል ይሆናል እንጂ በፍቅር፣ ይቅርባይነት እና መደመር ላይ በቁጥር አንድ የሚቀመጥ ነው። ብቃቱም ቢሆን በረከት፣ ህላዌና ዘርአይ አስግዶም እየተፈራረቁ በማእከላዊነት እና ስድብ ደፈቁት እንጂ ብሮድካስትን ለመምራት የሚያንስ አይደለም። ደሞ ለብሮድካስት!… ዶክተር አቢይ “የቀን ጅብ” በሆነው ዘርአይ አስግዶም ምትክ ሰለሞንን ሲያመጣ ይሄን ከግምት የከተተ ይመስለኛል። ልክ ለማ መገርሳ ዶክተር ነገሬ ሌንጮን እንደወሰደው ሁሉ!…
ለዚህም ነው በሰለሞን (ብሮድካስት)፣ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ( ኦሮሚያ)፣ ንጉሱ (አማራ) መካከል ከፍተኛ መናበብና መደመር የምንመለከተው። ያለምንም ጥያቄ ሶስቱም ሶስትም አንድም ሆነው በሲነርጂ እየሰሩ ነው። ይሄ ደግሞ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ነው።
ሰለሞን ለትግራይ ቲቪ እና ENN ቴሌቪዥን የፃፈው ደብዳቤ ከህግ አኳያ ክፍተት የለውም። አዋጅ ትክክል ነው/ አይደለም የሚለው የሰለሞን ጉዳይ አይደለም። ህውሓቶች የፓለቲካ የበላይነት በነበራቸው ሰአት ያወጡት በመሆኑ ተንጋለው የተፉትን መዋጣቸው ተገቢ ነው። ሕጉ ሲሻሻል ሰለሞንም እንዲህ አይነት ደብዳቤ እንደማይጽፍ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰለሞን ደብዳቤውን ሲጽፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አማክሮታል የሚል እምነት አለኝ። ጉዳዩ የህግ የበላይነትን ከማስከበር ተሻግሮ ፓለቲካዊ ትርጉሙ ከፍተኛ ስለሆነ። የትግራይ ቴሌቪዥን እና ENN ሽፋን መስጠት ያልፈለጉት የሚዲያ ነፃነትን ለመጠቀም ( ኤክሰርሳይስ ለማድረግ) ሳይሆን በፓለቲካዊ ምክንያት ነው። የለውጡ አደናቃፊዎች ስለሆኑ ነው። ከዶክተር አቢይ ኢትዮጵያዊነት በተቃራኒ ስለቆሙ ነው። በመሆኑም እነዚህ የሚዲያ ተቋማት በአደባባይ ሊጋለጡና ሊዋረዱ ይገባል። ይሄንን መረዳት ያቃተው ” ፓለቲከኛ” ስመለከት ትንሽ አስገርሞኛል።  በተለይም ለቀን ጅቦቹ ካራ ስሎ እየሰጠ ያለ ” የተቃዋሚ ፓለቲከኛ” ሁኔታውን ከውስጠ ድርጅት ሽኩቻና ትግል እንዲሁም መከፋፈል አንፃር መመልከት አለመቻሉ በመጠኑ አስደንግጦኛል።
በእኔ እምነት የለውጥ ሀይሉም ሆነ የሚዲያ ተቋማቱ ማተኮር ያለባቸው ” ትግራይ ቲቪ እና ENN ለምን ሽፋን ሳይሰጡት ቀሩ? ከዚህ ጀርባ ያለው ነገር ምንድነው? እነማን ናቸው? ከደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ጋር የሚያይዘው ነገር ይኖር ይሆን ወይ?” የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የኢህአዴግ ምክር ቤት በግንባሩ አባል በሆነው ህውሓት (መንግስት እና ፓርቲ) የሚተዳደሩት ትግራይ ቲቪ እና ENN በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ አለበት። በሌላ አነጋገር የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ለህውሓትና ENN ቦርድ ሰብሳቢ ለሆነው ደብረጺዮን ደብዳቤ እንዲፅፍ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል። ደብረጺዮን እንደ ፓርቲ ሊቀመንበርነቱ፣ እንደ መፈንቅለ ፕሬዝዳንትነቱና እንደ የኢ•ኤን• ኤን• ቦርድ ሰብሳቢነቱ የጽሁፍ አሊያም የድምፅ ማብራሪያ መስጠት አለበት።
በተረፈ “ፓለቲከኞች” የውስጠ ድርጅት ሽኩቻውን እና ፓለቲካዊ የሀይል አሰላለፉን ወደ ጐን ትተን ሰለሞን ላይ ውርጅብኝ ማውረድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ጥንቃቄ ብናደርግ ጥሩ ይመስለኛል። ሰለሞን በቀን ጅቦቹ እንዳይበላ ድጋፍ ብናደርግለት ይሻላል። የህግ የበላይነት የሚቆረቁረን ከሆነ ደግሞ አዋጁ እንዲሰረዝ ብንጠይቅ ይሻላል።
በተያያዘ ሰበር ዜና
 
ኢኤን ኤን(ENN) ቴሌቭዥን ጣቢያ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ስርጭቱን አቋርጦ በይፋ ሊዘጋ መሆኑ ተሰማ።
በመጪው አርብ 110 የሚሆኑ ቋሚ ሰራተኞቹን በይፋ ሊያሰናብት መዘጋጀቱንም የቅርብ ምንጮች ነግረውናል።
ምንጭ ፡ዋዜማ !
Filed in: Amharic