>

ከግድያ ሙከራው በስተጀርባ!!! (ፋሲል የኔአለም)

ከግድያ ሙከራው በስተጀርባ!!!
ፋሲል የኔአለም
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም በዶ/ር አብይ አህመድ ላይ የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ፣ ጠ/ሚኒስትሩ 
” ያያችሁም የሰማችሁም  መረጃዎችን ለፖሊስ ላኩ” ባሉት መሰረት እኔም የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት በማሰብ  ይህን ጻፍኩ።
 ከዚህ በፊት እንደጻፍኩት በአገሪቱ ውስጥ ለሚነሱ ግጭቶችም ሆነ በጠ/ሚኒስትሩ ላይ ለሚደረጉ የግድያ ሙከራዎች እቅዶች የሚዘጋጁት መቀሌ ነው።  እቅዱን ደግሞ በበላይነት የሚነድፉት እና የሚያስተባብሩት የቀድሞው የኢንሳ ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወልዳረጋይና ምክትሉ ቢኒያም ተወልደ ነው። ሁለቱ ሰዎች በበላይነት የሚመሩት ቡድን የአብይን መንግስት ለመገልበጥ ወይም እንዳይሳካለት ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ከመመደቡም  በላይ፣  በኢንሳ ውስጥ ያገኙት ልምድ መረጃዎችን ለመደበቅ እየጠቀማቸው ነው። ይህን ስራ ሲሰሩ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ይወቁ አይወቁ እስካሁን ማወቅ አልቻልኩም ።  ይሁን እንጅ አንዳንድ ነባር የህወሃት አመራሮች በግለሰብ ደረጃም ቢሆን አብረዋቸው እንዳሉ መረጃው አለኝ።
እነዚህ ሁለት ሰዎች ኢንሳን ለቀው ከወጡ ጀምሮ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ፣ እሱም ስምሪት ለመስጠት፣ ካልሆነ በስተቀር ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው  አያውቁም። ሰዎቹ ግጭቶችን በየቦታው ከማስነሳትና የግድያ ሙከራዎችን ከማድረግ በተጨማሪ፣ የትግራይ ህዝብ በአብይ ላይ እንዲነሳ እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። የትግራይ ብሄርተኝነት ከፍ እንዲል  አረናና የኢሮብ አክቲቪስቶችን ጭምር ለመጠቀም  ተደጋጋሚ ምክክሮችን አድርገዋል።  የኢሮብና የአረና ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የእነዚህ ሰዎቸ መጠቀሚያ እየሆኑ ነው። ማስረጃ ካስፈለገ ከአረና አባላትና ከኢሮብ አክቲቪስቶች ጋር ሰኞ በ11 ሰዓት በማዕበል ቱሪዝም ቤት ብልኢ በሚገኘው እኖህ ሆቴል ሲመክሩ እንዲሁም ሰኔ 16 ፣ ቦንብ በፈነዳበት ዕለት አክሱም ሆቴል ተሰብስበው የመከሩበትን መጥቀስ ይችላል። አረናዎችም የኢሮብ አክቲቪስቶም እንደማይክዱት እርግጠኛ ነኝ።
ይህ መረጃ በደህንነቱ ክፍል አይታወቅም ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገር አልችልም።  ዶ/ር አብይ ሙያቸውን ተጠቅመው ያሉዋቸው ሰዎች  ከፖሊሶች ይልቅ እነ ተክለብርሃንን  ይመስለኛል።
ከዚህ በፊት በባህርዳርና በቤተመንግስት ግቢ ታቅዶ በከሸፈው የመግደል ሙከራ ነባር የህወሃትና አንድ ነባር የብአዴን አባላት እንደነበሩበት ሰምቻለሁ። ሰዎቹ አሁንም ሆነ ለወደፊቱ  በአብይ፣ ገዱ ፣ ለማና ደመቀ ላይ  እርምጃ ለመውሰድ ሙከራቸውን የሚያቆሙ አይመስለኝም።
በመጨረሻም፣  አንዳንዶቻችሁ በጥላቻ የእነዚህን ሰዎች ስም እያጠፋሁ የሚመስላችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁ።  የሰዎችን ስም በሃሰት ማጥፋት ወንጀልም ሃጢያትም ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን  የሰው ስም ላለማጥፋት በሚል ጥንቃቄ እንዲህ አይነት መረጃዎችን አፍኖ ማስቀመጥ በአገር ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ ከአገር የሚበለጥ ነገር ደግሞ የለም። ስለዚህ እኔ የምድሩንም የሰማዩንም እዳ ተሸክሜ የሰማሁትን በመተንፈስ ጥቆማዬን ለማስተላለፍ ከህሊናዬ ጋር ተሟግቼ ያደረኩት በመሆኑ ይህን በማድረጌ አይጸጽተኝም።  ሰዎቹ ተይዘው ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ ነጻ ካላቸው በይፋ ይቅርታ ልጠይቃቸው ዝግጁ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ።
Filed in: Amharic