>

"በትግራይ ስም እንደራጅ እንጂ የኛ አመለካከት ቀድሞውንም ኢትዮጵያዊ ነው" ዶ/ር አረጋዊ በርሔ

ቢቢሲ አማርኛ

የህወሐት መስራችና የቀድሞ አመራር የነበሩት አቶ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በሀገሪቱ ካለው ለውጥና የተቃዋሚዎችና ተፎካካሪዎች ወደ ሀገራችሁ ጥሪ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ እንደሆነ አስታውቀዋል። ወደ አገር ውስጥ ስለመመለስ ውሳኔያቸው፣ ከህወሐት ጋር ያላቸውን ልዩነትና ቀጣዩ የትግል መስመራቸውን በማስመልከት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱት ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው፤ አሁን ለመመለስ የፈለጋችሁት ለምንድነው?

በመግለጫችን ላይ እንዳስታወቅነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ለውጥ እየመጣ ነው። እስከዛሬ ከነበረው አገዛዝ ለየት ያለና ተቃዋሚዎችን እንደ ተፎካካሪ የሚያይ፤ መብታቸውን የሚጠብቅ ሆኖ አግኝተነዋል። እንዲሁም አብሮ ሊያሰሩ የሚችሉ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው፤ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን የኛን ራዕይና አላማ ለህዝቡ ለማሳወቅና ካለው ለውጥ ጋርም አብረን እንድንጓዝ አስተዋጽኦ ለማድረግ ወስነን ነው ለመግባት እየተዘጋጀን ያለነው።

ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ጠይቃችሁ በጎ ምላሽ እንዳላገኛችሁ ይታወቃል። እስኪ ስለሁኔታው ይንገሩን?

አዎ! ብዙ ግዜ ሞክረናል። በተናጥል እንደ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር፤ የተለያዩ ህብረቶች አባል እንደመሆናችን በቡድንም በተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገናል። ነገር ግን የነበረው መንግስት አምባገነናዊ የሆነ ባህሪ ስለነበረው፤ እስካሁን የኛን ጥያቄዎች ውድቅ እያደረገ ነው የመጣው። አሁን ግን ውድቅ የሚያደርግ ሳይሆን ወደ ሃገራችን እንድንገባ የሚወተውት፤ እንድንገባ የሚተባበር አዲስ ሃይል ስለተፈጠረ፤ እኛም ለመግባት ወስነናል። የአዲሱ ለውጥ አራማጆች አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የእነ ዶክተር ዐብይ አህመድ ቡድን፤ ተቃዋሚዎችን ከውጪ እየሰበሰበ፣ እየጠራ፣ እየተቀበለና እያስተናገደ ነው። ይህ አይነት ጸባይ ባለፈው መንግስት አልነበረም። አመቺ ሁኔታ እንዳልነበር ሁሉም ሰው ያውቀዋል።

የእስረኞች መፈታትና የማዕከላዊ መዘጋት ውሳኔ አንድምታዎች

መንግስት ጥሪ ከማድረግ ባለፈ በሃገሪቷ ፖለቲካዊ ሁኔታ የናንተን አስተዋጽኦ ለመቀበል መንገዶች ተመቻችተዋል ብለው ያምናሉ?

አንደኛ አያያዛቸውን ስናየው ለጋራ ተሳትፎ የሚተባበሩ መስሎ ነው የታየን። ለምን እንደዚህ አልክ ብባል፤ ተቃዋሚ የነበሩ ሃይሎችን ሲቀበሉ አይተናል። እንደውም በትጥቅ ትግል ተሰማርተው የነበሩትን ሳይቀርም እየተቀበሉ ነው። ሁለተኛ፤ አፍነው ይዘዋቸው የነበሩና ታስረው የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ሲፈቱ አይተናል። ለብዙ አመታት ታስረው የነበሩ የሚዲያ ሰዎችም በአንድ ጊዜ ሲፈቱ አይተናል። ስለዚህ፤ እነዚህ ተጨባጭ እርምጃዎች ናቸው። ከንግግር ባለፈ በተቃዋሚ ወይም በተፎካካሪዎች ላይ ምንም መጥፎ አመለካከት እንደሌለ በተጨባጭ ያመለካክታሉ። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ለኛ ትልቅ ተስፋ አሳድሮብናል። ይህ ትንሽ ነው ካልን ደግሞ ራሳችን ገብተን ሰፋ እንዲል፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲዳረስ የማድረጉ ኃላፊነት የኛ ነው። ነገር ግን ከውጪ ሆነን እንደዚህ ካላገደረጋችሁ አንገባም የምንልበት ምክንያት ወደ ኃላ መሸሽ መስሎ ነው የሚታየኝ።

ወደሃገር ውስጥ ከተመለሳችሁ በኋላ በምን መንገድ ነው ተሳትፎ ለማድረግ ያሰባችሁት? በተጨባጭ የያዛችኋቸው ዕቅዶች አሉ?

ዕቅዶች አሉን። በሁለት አቅጣጫ ነው የምንታገለው። የመጀመሪያው የትግራይ ህዝብን ወገኑ፤ እህቱ፤ ወንድሙ ከሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋራ አንድነት፣ ሰላም ፍቅር ስለሚፈልግ ይህን እናስተጋባለን። ይህ እንዲሆንም እንታገላለን። እስካሁን ድረስ የመለያየት ፖለቲካ ነበር የሚራመደው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተዋደቀ እንደመሆኑ ኢትዮጵያዊነቱን አስረግጦ ከወገኑ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ወደ እድገት ጎዳና፣ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እንዲጓዝ ለመስራት ነው እቅዳችን። ሁለተኛው ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥ መልክ ባለው መንገድ እንዲቀጥልና የጋራ ስርአት እንዲመሰረት ለማድረግ ከለውጥ አራማጆቹ ጋር ለመስራት ነው። የአንዱ ሃይል ሌላውን የሚያሸንፍበት አይነት ጉዳይ ሳይሆን በጋራ ለሁላችንም የሚጠቅም ስርአት እንዲመሰረት ለማመቻቸት ነው። ለሁላችንም የሚበጅ ስርአት ከተመሰረተ በሰላም ለመወዳደር ነው የምናስበው። እያንዳንዱ ፓርቲ የሚፈልገውን ለህዝብ እያሰማ የህዝብ አመኔታና ድጋፍ እያገኘ ለተወሰኑ አመታት ሊመራ ይችላል። እዛ ለመድረስ የጋራ ስምምነትና ስርዓት መመስረት ያስፈልጋል። አሁን ያሉት ሁኔታዎች ደግሞ አመቺ ስለሆኑ እንደሚሳካልን ተስፋ አደርጋለሁ። ከህዝባችን የኢትዮጵያ ህዝብ መሃል ገብተን፣ ድጋፋቸውን አግኝተን ሃገሪቱ ከነበረችበት ችግር ወጥታ እንደሌሎቹ የበለጸጉና የተከበሩ ሃገራት እንደምትሆን እርግጠኞች ነን።

በትውስታ ወደላ እንመልስዎትና በህወሀት አመራር ላይ ሳሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንድ ጥፋት አጥፍተው እንደቀጧቸው ይነገራል። ስለጉዳዪ ሊያብራሩልን ይችላሉ?

(ሳቅ) ያለፈ ነገር ምን ያደርጋል? የወደፊቱ ላይ ብናተኩር የሚሻል ይመስለኛል። ሁኔታዎች ሲረጋጉ ቀስ ብለን በሰፊው እናወራዋለን፤ እንተነትነዋለን።

ከህወሐት ተገንጥሎ ወጥቶ እንደገና በተቃዋሚነት ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ተስፋ ምን አይነት ስሜት አለው?

በመጀመሪያ ከህወሃት ጋር አልተስማማንም። ህዝቡና ታጋዩ ሌላ ነው። ሁሌም ቢሆን ህዝቡ ግን እኛ የምንለውን ሃሳብ የሚደግፍ ነበር። በጊዜው የነበሩት አመራሮች ግን እኛን ለማግለል ውስጥ ውስጡን ይሰሩ ነበር። በዚህ ምክንያት አላማ መቃወስ ስለመጣ በዚያ ሁኔታ መቀጠል አልቻልንም።

የኛ አመለካከት ድሮውንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ነው። በትግራይ ስም እንደራጅ እንጂ የኛ አመለካከት ቀድሞውንም ኢትዮጵያዊ ነው። እቅዳችን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖር ለማድረግ ነበር። እነሱ ወደ መገንጠሉ የሚያዘሙ ነበሩ። እኛ ከወጣን በኋላ ቀናቸውና ስልጣን ያዙ። ኢትዮጵያውያን መስለውም እስካሁን ድረስ ሲመሩ ቆይተዋል። ይህንን ውጭ ወጥተን መቃወም፣ ማጋለጥና ትግሉ ፈር እንዲይዝ ለማድረግ እስካሁን ተንቀሳቅሰናል። ውጭ ሆነን አላረፍንም።

እስካሁን ድረስ እኛን ከሚመስሉ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖር ከሚመኙ ደርጅቶች ጋር ያላሰለሰ ትግል አድርገናል። እውነት ነው በውጭ ሀገር ለመታገል የተገደድነው ሀገር ውስጥ አምባገነን ስርዓት ስላለ ነው። ይህ ስርዓት እስካለ ድረስ ጠብ የማይል ነገር ሊኖር እንደማይችል ይገባኛል። ኢህአዴግን ህወሐት እየመራው ቢቆይም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ግጭቱ ስለበረከተ እየተዳከመ ሄዶ ከውስጥ በነዶክተር አብይ አህመድና አቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኃይል ተፈጠረ። ኢህአዴግን ከውስጥ ስላዳከመው የድሮውን መስመር ሊይዝ አልቻለም። ስለዚህ የአሁኑ መስመር ድሮ እኛ የምንለው፣ የምንደግፈው ስለሆነ ነው ለመግባት የወሰንነው።

ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ወደ 23 ዓመታት የቆየ ፓርቲ ቢሆንም ብዙም አይታወቅም። ለምን?

አፈና ነዋ! የታፈነ ሁኔታ ነበር ያለው። በተለይ የድሮ የህወሃት መሪዎች ትግራይ ውስጥ ማንም የፖቲካ ድርጅት ዝር እንዳይል፤ ጋዜጣ ለማንበብ እንኳን ምንም እድል እንዳይከፈት አድርገዋል። ከዛም ባሻገር እስከ አሁን ድረስ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ሳይሆኑ፤ አንድ ናቸው እያለ፤ እነሱ በኢትዮጰያ ህዝብ ላይ የሚሰሯቸው በደሎች ለህዝቡ እየተረፈ ነው። በዚህ ምክንያት ህዝብ፤ ህዝብ እየተጋጨ ነው። አሁን በትግራይ ህዝብ ላይ እየወረደ ያለው ግፍ ሰርቶ የሚያድር ህዝብ በየአካባቢው እንደ ጠላት መታየቱ ነው። ይሄ የተሳሳተ አመለካከት ነው። ለዚህ ተጠያቂዎቹ የድሮዎቹ የህወሃት መሪዎች እንጂ ህዝቡ ሊሆን አይችልም። ህዝቡ አይደግፋቸውም። ህዝቡ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ታፍኖ እየኖረ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ አልቻልንም። አፈናው በርትቶብን ነበር። ህዝቡን ልናነጋግር ይቅርና፤ የምንጽፈው ጽሁፍ ወደዚያ እንዳይገባና የምንናገረው ንግግር እንዳይሰማ ሙሉ በሙል ተቆጣጥረውት ነበር። በዚህ ምክንያት እንቅስቃሴያችን ብዙ ሳይታወቅ ቆይቷል። ይህንን የአፈና አጥር እየሰበረ መከታተል የሚፈልግ ሰው ያውቀናል። በእርግጥ ከሃገር ውጪ ከተቃዋሚ ሀይሎች ጋር እየተሰባሰብን የምናደርገው እንቅስቃሴ በስፋት ይታወቃል። ሀገር ቤት ግን በብሄር ደረጃም ሆነ በሀገር ደረጃ እነሱ የሚቆጣጠሩት ሚዲያ ነው ያለው።

ወደ ሃገር ውስ የመመለሳችሁን ጉዳይ ከመንግስት ጋር ተወያይታችኋል ወይ? የመመለሳቸሁ ሂደትስ እንዴት ነው የሚከናወነው?

ከመንግስት ጋር በደንብ ተወያይተናል። የነሱንም ይሁንታ አግኝተናል። ምን ያህል የፓርቲው አባላት ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለሱ ለጊዜው መናገር ባንችልም፤ አንድ ቡድን ግን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳል

Filed in: Amharic