>

የማንነት ጥያቄ ምንጩ የማንነት ፖለቲካ ነው (ከይኄይስ እውነቱ)

የማንነት ጥያቄ ምንጩ የማንነት ፖለቲካ ነው

ከይኄይስ እውነቱ

ወያኔ ትግሬ በኢትዮጵያ ላይ ከተከለው ነቀርሳ ዋናው የማንነት ፖለቲካ ነው፡፡ ይህንንም ያገኘው ከፋሺስት ጥልያን እና የጥቂት ነጮች የዘረኝነት አገዛዝ (አፓርታይድ) ሰፍኖ ከቆየባት ከደቡብ አፍሪቃ ለመሆኑ ሕወሓት ላለፉት 27 የግፍ ዓመታት እነዚህ ከጠቀስናቸው የዓለማችን አስከፊ አገዛዞች በጎሣ ፖለቲካ ጥግ ድረስ ሂዶ አገርንና ሕዝብን ለማጥፋት የፈጸማቸው የሽብር ድርጊቶች፣ ወንጀሎችና ዝርፊያዎች ሕያውና ግዙፍ ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህንን በመክሥተ ደደቢት የወጠነውን ሴራ በማስመሰያ ሕገ መንግሥቱ ሽፋን ሰጥቶታል፡፡  የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ‹አስተዳደር› ከመጣ ወዲህ፣ ይህ ሥጋ የለበሱ አጋንንት ስብስብ ቡድን በጻዕረ ሞት ላይ ቢገኝም የሰው ሕይወትን እያስገበሩ ያሉና በማንነት ላይ የተመሠረቱ ግጭቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ቆስቁሶ ይህንን ጥፋት እንደ ሰደድ እሳት ለማዛመት እየጣረ ይገኛል፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገራት በወረራ የነጠቃቸውን መሬቶች ሕጋዊ ለማድረግ ሲል ሕዝብ ያልሆነውንና ያልፈለገውን ማንነት በመጫን የ‹ጎሣ ሻምፒዮኑ› ወያኔ ትግሬ በኢትዮጵያ ምድር አዲስ ባርነት ፈጥሯል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ወያኔ ትግሬ በየግዛቱ የጎሠኝነት ‹አማልክት› አቁሞ ለዚህ ጣዖት የሚሰግዱ አያሌ ናቸው፡፡ ክርስቲያኑም፣ እስላሙም፣ ኢ-አማኒውም በየሃይማኖት አስተምሕሮው አመልከዋለኹ ከሚለው እውነተኛ አምላክ በላቀ ለጎሣ አማልክቱ በጭፍን መንበርከኩን ማንም የሚክደው አይመስለኝም፡፡ የአኖሌ ጣዖት ለዚህ አንዱ ሕያው ምስክር ነው፡፡

የማንነት ፖለቲካ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች/ቡድኖች ኢ-ፍትሐዊነት ተፈጽሞባቸዋል በሚል የፈጠራ ወይም እውነተኛ የሚመስል ትርክት ይዞ በዳይና ተበዳይ፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ፤ ያልተወከለና ከሚገባው በላይ ልዩ ጥቅም ያገኘ፤ ጥሩ እና መጥፎ በሚል እጅግ ከፋፋይ ንድፈ ሃሳብ ላይ ተመሥርቶ ግለሰቦችን በሰውነት፣ በዜግነት፣ በጠባያቸው ወይም በሚያከናውኑት ድርጊት ሳይሆን በጎሣ ወይም በነገዳቸው የሚፈርጅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በመሆኑም የዚህ ዓይነቱ ፖለቲካ አራማጆች ተባዳይ የሚሉትን ቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚል በዳይ፣ ጨቋኝ፣ ልዩ ጥቅም ያገኘ፣ መጥፎ ብለው የፈረጁትን የኅብረተሰብ ክፍል ማጥፋት፣ ሌሎች ዉጉዝ ከመ አርዮስ ብለው ደንጊያ እንዲጭኑበት ማድረግ ማኅበረሰቡ ላለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ኹሉ ፍቱን ፈውስ አድርገው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ የማንነት ፖለቲካ በተፈጥሮው (inherently) አደገኛ፣ ከፋፋይ፣ አግላይ፣ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን ሆን ብሎ የሚያገዝፍ፣ ሰዎችን የጋራ ፍላጎትና ተሞክሮ የላቸውም ከሚል እሳቤ በመነሳት በርካታ ሳጥኖችን የሚያበጅ፣ ማኅበራዊ አንድነትን የሚያናጋ፣ እንደ ጥልያኑ ፋሺስት እና ጀርመኑ ናዚ ያሉ አደገኛ ማንነቶችን እንዲበቅሉ ለም መሬት ሆኖ የሚያገለግል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕዝብን ከሰብአዊነት በታች እንዲዘቅጥ (dehumanize) የሚያደርግ ነው፡፡ በኢትዮጵያችንም በዘመነ ወያኔ የታየውና እስካሁንም ያላባራው ይኸው የማንነት ፖለቲካ የፈጠረው ቀውስ ነው፡፡

ይህ ጸሐፊ የማስመሰያ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ ወቅታዊ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ባቀረባቸው አስተያየቶች እንዳቀረበው በወያኔ ትግሬ አገዛዝ ዘመን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ ብሎ አያምንም፡፡ በዚህም ምክንያት የወያኔ ሕጎችንና ‹ተቋማትን› በዚህም መሠረት የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ለመቀበል ቢያንስ የሞራል ግዴታ እንደሌለበት ያምናል፡፡

በሌላ በኩል ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያን ወደ ነፃነት፣ እኩልነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊ አገር ለማሸጋገር ጸያሔ ፍኖት (መንገድ አቅኚ/ጠራጊ) እንደሚሆን በማሰብ ከመነሻው ድጋፉን ሰጥቷል፤ ለእስካሁኑም ተስፋ ሰጪና በቀላሉ የማይታዩ አበረታች የለውጥ ጅማሮች ምስጋናውን በየጊዜው አቅርቧል፡፡ ዶ/ር ዐቢይን የአዲስ አበባና የአካባቢው ሕዝብ በነቂስ ወጥተው ለምን ደገፉት? (አ.አ. በፖለቲካ ማዕከልነቷ ለኢትዮጵያ ኹሉ ማሳያ ስለምትሆን እንጂ ድጋፉ በኹሉም የኢትዮጵያ ክፍል ነው) ከጎሣ/ከነገድ ኢምንትነት ወጥተን ሰው ናችሁ ኢትዮጵያዊ ናችሁ ስላለን አይደለም እንዴ? ይህቺን የምንወዳትንና ብዙዎች የማይተካ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡላት ጥንታዊትና ታሪካዊት ኢትዮጵያን ከፍ ከፍ ስላደረገና በአንድነት/አብሮነት መንፈስ ለኹላችን እኩል እንድትሆን ቃል ስለገባና ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ መልካም ጅማሮዎችን ስላሳየን አይደለም እንዴ? መንደር ከሚልከሰከስ ወያኔያዊ አስተሳሰብ ወጥተን ትልቁን አገራዊ፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ሥዕልን እንድንመለከት ስላደረገን አይደለም እንዴ? የይቅርታ፣ የዕርቅ፣ የኅብረት/የመደመርን ሉዐላዊ ሃሳብ ገንዘባችን እንድናደርግ ስላመላከትን አይደለም እንዴ? ወዘተርፈ፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ተስፋችንን ለማጨለም የሚታገሉት ሕውሓትና ግብረ አበሮቹ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ኹሉ (በዘረኝነት በገነቡት የወያኔ መከላከያ ሠራዊት፣ የግላቸው ደኅንነት እና በዝርፊያ ባከማቹት ሀብት ምክንያት) አሁንም በስፋት ናኝተው ይገኛሉ፡፡ በዚህ ላይ ድንቁርናቸው ተጨምሮበት ቀናቸው እየተቆጠረ ባለበት ወቅት እንኳ የጨለማ ሥራቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ታላቁ መምህር ጋሼ መሥፍን ስለ ወልቃይት የማንነት ጥያቄ ባንድ አስተያየታቸው ‹ወልቃይት የማን ነው? የማይረባ ጥያቄ› ማለታቸውን እናስታውሳለን፡፡ ይህንን አባባል በስሜታዊነት ላነበበው እኚህ ሰው ምን ነካቸው? ቢል አያስደንቀኝም፡፡ ማስተዋልን ገንዘብ ያደረገ ወገን ኹሉ ጋሼ መሥፍን ትልቁን አገራዊውን ሥዕል እየተመለከቱ መሆኑን፣ የጥያቄው መንፈስ በወያኔ ጎሠኝነት ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚከተን ይረዳል፡፡ በወልቃይት የማንነት ጉዳይ ከዛሬ አርባ ዓመት ገደማ ጀምሮ የተገደሉትን፣ የተፈናቀሉትን፣ የተሰደዱትንና አሁንም ከባርነት በማይተናነስ ሁኔታ በገዛ አገራቸው የተገፉትን ኢትዮጵያውያን መከራና ስቃይ ሳይሰማቸው ቀርቶ ነው? በጭራሽ! ኢትዮጵያውያንን ኹሉ ያስቆጣል፡፡ የእስካሁን አካሄድና የጥያቄው አቀራረብ የሚፈልገውን መፍትሄ ስለማምጣቱ ዋስትና ስለሌለ እንጂ፡፡ ወያኔ ትግሬ ከጎንደርና ከወሎ መሬት በወረራ ወስዶ ትግራይን ሲያሳብጥ ትግራይን ለማልማትና በደደቢት መግለጫው እንዳስቀመጠው (ከኤርትራ ውድቀት ባይማርም) ታላቂቱን የትግራይ ሪፐብሊክ ለመመሥረት ይመስላል፡፡ ስለሆነም የማንነቱ (የጎሠኝነት) ጥያቄ አስኳሉ የመሬት ወረራው ይመስለኛል፡፡ ማንነትን መሠረት አድርጎ የተፈጸመው ግፍ የመሬት ወረራውን በጉልበት ለማስቀጠል የተደረገ ርምጃ አካል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ችግሩ ወያኔ ‹‹ክልል›› ብሎ ያዋቀረው የአስተዳደር ሳይሆን የማንነት ፖለቲካ መሣሪያ እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም ማንነትንም ሆነ የአስተዳደር ግዛት አከፋፈልን መሠረት አድርገው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚነሱ ጥያቄዎች በመሠረታዊ መልኩ ሊፈቱ የሚችሉት የኢትዮጵያን ግዛቶች ለኤርትራ አሳልፎ በሰጠና በአገር ክህደት ወንጀል በሚጠየቅ የውሸት ፓርላማ አቤቱታ በማቅረብ ወይም የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ በሞተባት ኢትዮጵያ ለወያኔ ፍርድ ቤት በማቅረብ አይደለም፡፡ መፍትሄው ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የጀመረውን መልካም የለውጥ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ እና የለውጡ ሂደት ሰፋ ብሎ ለማንነት (ጎሣ) ፖለቲካ መሠረት የሆነውን የማስመሰያ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እንዲቀየርና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሳተፍበት አዲስ ሕገ መንግሥት ረቅቆ እንዲፀድቅ ኹላችን ግፊት ስናደርግ ብቻ ነው፡፡ ሰሞኑን ‹‹ሕገ መንግሥቱን የማሻሻያ አዋጅ ሮድ ማፕ ወጣ›› በሚል አንድ አስተያየት ሰጭ የጻፉትን ተመልክቼአለሁ፡፡ በቅድሚያ እንደዚህ ዓይነቱ አገላለጽ ከመን ግሥት የቀረበ ስለሚመስል ብዙዎችን ያሳስታል፡፡ የማሻሻያ ሃሳቡ የቀረበው አቶ ግርማ ካሣ በሚባሉ ግለሰብ ሲሆን፣ አገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል በሚል እምነት ለውይይት ያቀረቡት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የሃሳብ መዋጮ ኹሉን አቀፍ (comprehensive) በሆነ መልኩ ከሌሎች የሕግ ባለሙያዎችና ምሁራን በስፋት እንዲቀርብ ይበረታታል፡፡ እንደሚታወቀው እንደ ወያኔ ትግሬ ያሉ አምባገነን አገዛዞች ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ በራሳቸው የሚጽፏቸው የይስሙላ ሕግጋተ መንግሥት ውስጥ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ቃል በቃል ተገልብጠው እንዲካተቱ ያደርጋሉ፡፡ ይህ አዝማሚያ የቀዝቃዛው ጦርነት ከሚባለው ክስተት ማብቂያ ጀምሮ አምባገነን አገዛዞች የሚከተሉት ቀመርና ፋሽን እየሆነ መጥቷል፡፡ ዓላማውም ምዕራባውያን ለጋሾችና አበዳሪዎች የእርጥባንና የብድር እጃቸው እንዳይታጠፍ ያለመ መሆኑ እነዚህ ድንጋጌዎች ከተጻፉበት ወረቀት አለማለፋቸው ታላቅ ምስክር ነው፡፡ በወያኔ የይስሙላ ሕገ መንግሥት እነዚህ ድንጋጌዎች ከመቶ 23 እጁን (35 ድንጋጌዎች) ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ ኹለንተናዊ ተቀባይነት ያላቸው የሰው ልጅ የጋራ መርሆዎች በመሆናቸውና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃም ስለሚያሻቸው መካተታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የእነዚህ ድንጋጌዎች መኖር የይስሙላ ሕገ መንግሥቱን ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው (legitimate) አያደርገውም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕገ መንግሥትን ያህል ታላቅ አገራዊ ሰነድ ሲሻሻልም ሆነ ሲተካ አንድ አላዋቂ ፖለቲከኛ ሲናገር እንደሰማሁት አውጡ እምትሉትን እናወጣለን፤ መካተት አለበት የምትሉን እናስገባለን በሚል መልክ የሚከናወን አይደለም፡፡ ጥናትን መሠረት አድርጎ ምን ዓይነት ሥርዓት ማቆም እንፈልጋለን፣ የፍልስምና መሠረቱ ምን ይሁን፣ ቊልፍ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች ምን ይሁኑ፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ምን ዓይነት ገደብ ይበጅለት፣ በታወቁት የመንግሥት የሥልጣን አካላት መካከል ምን ዓይነት የርስ በርስ ቊጥጥርና ምዝዝን ሥርዓት ይኑር፣ ታሪካችን እና ተቋሞቻችን ምን ይመስላሉ፣ መንግሥታዊ ቅርፁና ዓይነቱ ምን ይሁን፣ ሕገ መንግሥታዊ እውቅናና ጥበቃ የምንሰጣቸው አገራዊ የጋራ እሴቶች ምንድን ናቸው፣ የሕዝብ ብሔራዊ ማንነት እንዲሁም የወደፊት የጋራ ምኞታችን እንዴት ይገለጻል፣ ሰነዱ ቃለ እግዚአብሔር ባለመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት ይሻሻል ወዘተርፈ. የመሳሰሉ በማዕቀፍነት የሚያገለግሉ አንኳር ጉዳዮችን አንስቶ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ የእኔ እምነት ግን ኢትዮጵያን ሰቅዞ የያዛት ችግር ሥርዓታዊ፣ መዋቅራዊና ተቋማዊ ነው ከሚል እሳቤ ስለሚነሳ የይስሙላ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ መሠረታዊ ለውጥ (ነፃነት፣ እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) ያስፈልገናል፡፡ የዶ/ር ዐቢይን ‹አስተዳደር› የምደግፈውም በመስቀል አደባባዩ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ እንደተናገረው/ቃል እንደገባው መዳረሻው መሠረታዊ ለውጥ ነው ከሚል እምነት ነው፡፡ ከመደመር/አብሮነት ፖለቲካው ጋር የሚሄደውም መሠረታዊ ለውጥ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡  እስቲ እንምከርበት፡፡ ምሁራን እጃችሁ ከምን?

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና የማንነት ጥያቄ መሠረታዊ ምንጩ ወያኔ ትግሬ አስቀድሞ በደደቢት መግለጫው፣ ከዚያም በማስመሰያ ሕገ መንግሥቱ የነገዶችንና ጎሣዎችን መብት አስከብራለኹ በሚል በማር በተለወሰ መርዝ የተከለው የጎሣ ፖለቲካ (ቋንቋንና ጎሣን መሠረት ያደረገ የውሸት የፌዴራል ሥርዓት፤ ይህንንም ተከትሎ ከፋፍሎ ለማናቆር፣ ለመሬት ወረራና ለዝርፊያ እንዲያመቸው ያዋቀረው ‹‹ክልል›› የተባለ የአትድረሱብኝ አጥር ወዘተ.) መሆኑን በአሁኑ ጊዜ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ካለ ላገሩ ባዳ መሆን አለበት፡፡ የክርክሩን ጭብጥ አማራ/ትግሬ፤ የጎንደር/የትግራይ ከሚለው በዘለለ አርቆ ማየትን ይጠይቃል፡፡ ማንነትን መሠረት ያደረገ ግጭት በባሕርይው ከምክንያታዊነትና አመክንዮ ጋር ዝምድና ስለሌለው እጅግ ደም አፋሳሽ ነው፡፡ ከከፋም አገርን በታኝ ነው፡፡ እንደ ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) ያሉ አፍራሽ ቡድኖች ከጀርባ ሆነው፤ ተጨንቆ ተጠቦና በምርጫው ያላመጣውን ቋንቋውን፣ ነገዱን ተጠቅመው እንዲሁም መርዘኛ ትረካ ጨምረውበት ሺዎችን የሚነዱበት ምሥጢሩም ይኸው ምክንያታዊነትንና አመክንዮን ነጥቆ በስሜት እንድንነዳ÷ በመንጋ እንድንቀሳቀስ ስለሚያደርገን ነው፡፡ ምክንያት (እውቀትን መሠረት ያደረገ እሳቤ፣ ማስተዋል፣ ማመዛዘንና መወሰን) በሌለበት የሚሠለጥነው ጉልበትና አውሬነት/ጭካኔ ነው፡፡ ሰው የተፈጥሮ ወንድሙንና እህቱን የአገሩን (የኢትዮጵያ) ልጅ ወገኑን የሚገድል ከሆነ ከአውሬ በምን ይለያል? ለማስተዋል የተፈጥሮ እውቀት (ሕገ ልቡና) በቂ ነው፡፡ የግድ መደበኛ ትምህርትንና በዚህ የሚገኘውን እውቀት አይጠይቅም፡፡ ሰውነት በቂ ነው፡፡ ማንም እንደፈለገው እየነዳን ወገናችንን ስናጠፋ ግን የሰውነት ተፈጥሮ÷ የሰውነት ባሕርይ እንደሌለን እየመሰከርን ነው፡፡ ግጭቶች በሚሰሙባቸው ክፍላተ ሃገር የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ኹሉ እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ በወያኔ አውሬዎች (በነዚህ የምድሪቱ ትናንሾች) ወጥመድ አትግቡ፡፡ እባካችሁ ምድሪቱ (ኢትዮጵያ) ከግፍ ከመከራ ሰንበት (ዕረፍት) ታድርግ፡፡

Filed in: Amharic