የደሴ ሰልፍ እና የባንዲራ ጉዳይ መጨረሻ
አትክልት አሰፋ – ቫንኮቨር
የሆነው ሆነና የሰኔ 16ቱን በአዲስ አበባ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በተደረገበት ወቅት ደሴና ጎንደርም ተደምረው አደባባይ ወጥተዋል። በሁለቱም ከተሞች እንደ አሸዋ የተጠቀጠቀ ህዝብ ሲተራመስ፣ ሲፎክር፣ ሲሸልልና ሲያቅራራ፤ የአባቶቹን ጀግንነት እያስታወሰ ሰልፉን ሲመራ ተመልክተናል።
ልሂቅ ከደቂቅ አደባባይ ወጥተው ደሴ ፒያሳ በህዝብ ተጥለቅልቃለች። ከአራቱም ማእዘናት ከሚገኙ ሰፈሮች ወደ መናኸሪያዋ ፒያሳ አምርቷል። ከተማዋ በተለያዩ መፈክሮች ደምቃለች… ህዝብ በደማሪው ዶ/ር አብይ ምስል በታተሙባቸው ልብሶች አጊጦ ወጥቷል።
በዚህ ሰልፍ ላይ ወጣቱን ያልተመቸው… የጎረበጠው… ለሁለት አስርት ዓመታት ያለአቅሙ እየከበደው የተሸከመው… ነገር ነበር። የባንዲራ ጉዳይ…። ደም እና አጥነት በውህደት ያቆሟት፣ ከአእምሮ በላይ ሆና ለዘመናት ለቆመች ሀገር ተምሳሌት የሆነች ባንዲራ። …
ይህ ያንገበገበው የዚህ ዘመን ወጣት… ያልተመቸውን… ውስጡ ያልተቀበለውን ባንዲራ ሊሸከም ከቶ አልፈለገም። … እናም በቀጥታ ፒያሳ አደባባይ ላይ በሚገኘው በድሮ ስሙ መምሪያ ላይ የአባቶቹን ባንዲራ እየዘመረ ሰቅሎ አላበቃም… ወጣቱ በቀጥታ እየጨፈረ በብዙ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት አመራ እናም የአባቶቹን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በክብር በድጋሚ ሰቀለ…።
ወጣቱን ይህም ከቶ አላረካውም… ሌላ የሚቀር ቦታ አለ… የብአዴን ጽህፈት ቤት። እዛም በየእለቱ ሲያዩት ውስጣቸው የሚቃጠልበትና የሚናደዱበት የባለ ኮከቡ ባንዲራ አለ… ያስ ለምን ይቀራል…? ወረደ.. እናም በመሳሪያ ህግ ታስራ ነገር ግን በህዝብ ልብ ውስጥ እንዳትጠፋ ሆና የምትኖር አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በክብር ተውለበለበች። ይህንን ጉድ እየተከታተሉ ያዩ አንድ አዛውንት አባት አንገታቸውን ወደ ሰማይ ቀና አደረገው “አሁን ግደለኝ…” በማለት መማፀናቸውን ሰማሁ።
ድሮም ቢሆን እንደሌሎቹ ከተሞች ሁሉ ባንዲራና ደሴ ልዩ ትስስር አላቸው… ባንዲራ በደሴ የእለት ተእለት ጉዳይ ነበር። መቼ እንደተጀመረ ባይታወቅም በተለይ በዘውዱ ዘመንም ሆነ በመንግስቱ ኃይለማርያምም ወቅት በደሴ ከተማ መሃል ፒያሳ ላይ ባለው የፖሊስ መምሪያ ላይ ጠዋት እና ማታ የኢትዮጵያ ባንዲራ ትከብራለች። ጠዋት በ12 ሰዓት መመሪያው ማማ ላይ ፊሽካ ይነፋል… ያኔ ሁሉም በአካባቢው የሚገኝ ሰው ቀጥ ብሎ ይቆማል… ማንም መንቀሳቀስ አይችልም። ከዛም ክብርት ባንዲራዋ በተረኛ ፖሊስ በክብር ትሰቀላለቸ። ከዚያ ደግሞ ምሽት ሲመጣ ልክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በተመሳሳይ መልኩ ፊሽካ ይነፋል… ባንዲራ በክብር ትወርዳለች። ይህ ደሴንና ባንዲራን ያጣመረ ሀቀ ነው። ለዚህም ነው ደመራ /መስቀል/ እና ጥምቀት በመጣ ቁጥር በደሴ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በየዓመቱ የምናየው…።
…ጉዳዩ በዚህ አላለቀም… በሚቀጥለው ቀን እሁድ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አላሙዲን በሰራው ህንጻ ውስጥ ባለው ሩቅያ አዳራሽ ውስጥ ካድሬዎችን ሰብስበው ያወያያሉ የሚል ዜና ይሰማል። … ወሬው ታክሲ ተራ ገብቶ ኖሮ… /በደሴ ታክሲ ተራ ወሬ ከደረሰ በአጭር ጊዜ ከተማዋ ትዳረሳለች/ የከተማው ወጣት ደሴ ፒያሳን በነጋታው ዳግም አጥለቀለቀው።
ጥያቄያቸውም አንድ እና አንድ ነበር… “አቶ ገዱ ይውጡና ያነጋግሩን…” አቶ ገዱም ህዝቡን ሁኔታ ሰምተው ወጥተው አነጋገሩ። ወጣቱም በጥያቄ አዋከባቸው…
የተሰበሰቡት የህወሃት ተላላኪዎች ናቸው…
እኛን አይወክሉም…
ካድሬዎቹ ለውጡን የሚቀበሉ አይደሉም
ከአሁን በሗላም እነኝህ ሰዎች አይመሩንም … የሚሉ ጥያቄዎችም ተነሱ…
አቶ ገዱም ሁኔታውን ለማረጋጋት ከሰአት በሗላ በሆጤ ስታዲየም ተገኝተው የህዝቡን ጥያቄ እንደሚሰሙ በመፍቀዳቸው ከሰዓት በሗላ ስታዲየሙ ከአፍ እስከ ደፍ ሞልቶ ጠበቃቸው።
ጥያቄዎችም እንደገና ጎረፉ… የአስተዳደር… የሙስና…
የዶ/ር አብይ ለውጥ ሁሉ ተነስቶ ውይይት ተደረገባቸው…
በተለይ በተለይ በደሴ ዙሪያ ጢጣ በተባለ ሰፈር ሊሰራ ታቅዶ የነበረውና በህውሃት ሸፈጥ በጀት ተጎማምዶበት ተግባር ላይ ያልዋለው የወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ኮምፖውንድ ግንባታ ስራ /ሊሰራ ታቅዶ የነበረው ሆስፒታል ለምስራቅ አፍሪካ ሪፈራል ይጠቅማል የተባለለትና የልብ፣ የአይን፣ የኩላሊት የመሳሰሉ ማዕከላትን ታሳቢ ያደረገ እጅግ ትልቅ ፕሮጀክት ነበር/ እሱም የተቋረጠበት ምክንያት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ብዙ ክርክር አስነሳ…
ዋናው ነገር ግን አልተረሳም… የአባቶቻችን ባንዲራ ወደ ነበረበት ይመለስ። ሁካታና ጩኽት ሆነ… አቶ ገዱም ምላሽ ሰጡ …አዲሱ የለውጥ አመራር የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ገልጠው የሆስፒታል ግምባታውም ፌዴራል የሚፈቀድላቸውን በጀት ይዘው ከህዝቡ ጋር በመተባበር ፍጻሜ እንደሚያደርሱት ቃል ገቡ።
ዋንኛውና የባንዲራው ጉዳይ የህዝቡ ጥያቄ ከሆነ ወደነበረበት የማይመለስበት ምንም ምክንያት የለም ሲሉም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ህዝቡን አርጋጉ… በመለጠቅም እንዲህ አሉ… “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህ የባንዲራ ጉዳይ የህዝብ ጥያቄ መሆኑ አሳስቧቸው ጉዳዩን የሚያጠና ቡድን ማቋቋማቸውን ተናገሩ… ህዝቡም ድጋፉን በጭብጨባና በሆይታ አስተጋባ … ፤ አናም…
አያ ሆሆ ማታ ነው ድሌ… እያለ ጭፍራውን አቀለጠው…::
ከዚሁ አካባቢ በሰማሁት ቁም ነገር አዘል ወግ ላብቃ። ደንብ አስክባሪ የሚባሉ የኢህአዴግ አባል የሆነ ሰው ብቻ የሚቀጠርበት ቡድን /ስራ/ አለ.. ቡድኑ ቤት ማፍረስን ጨምሮ ልዩ ልዩ ስራዎችን በመስራት ይታወቃል:: አንድ ሰው በግቢው ውስጥ ያሳደጋቸውን ሶስት ዛፎች ይቆርጥና ሶስት መቶ ብር ይሸጣል… ደንብ አስክባሪዎች ሰምተው ቤቱ ድረስ መጥተው የአምስት መቶ ብር ቅጣት ይቀጡትና ይሄዳሉ:: ለዚያውም ለዛፍ ቆራጭ ተጨማሪ 100 ብር ከፍሎ ኪሳራው የበዛበትና ሁኔታው ያንገበገበው ይህ ሰው ቅጣቱን ከፍሎ ሳይጨርስ ከከብቶቹ መሀከል አንዷ ትወልድበታለች፤ ከዛም ቀጥ ብሎ ወደ ደንብ አስከባሪዎች ቢሮ ይግባና እንዲህ ይላል… “ላሜ ጥጃ ወልዳለች ላሚቱን ልለባት ወይስ ልተዋት?”
አበቃሁ!
ቸረ ለእናንተ