>

ሕወሓት እና መለስ በያሬድ ብዕር! (ሙሉዓለም ገብረ መድኀን)

ሕወሓት እና መለስ በያሬድ ብዕር!
ሙሉዓለም ገብረ መድኀን
***
የኢሕአዴግን ነገረ-ፖለቲካ በቅርበት የሚያጠኑ ምሁራን/ፖለቲከኞች ስለ ድርጅቱ ለመጻፍ በሚያደርጉት ጥረት የድርጅቱ አስኳል ከሆነው ሕወሓት ፖለቲካዊ ቁመና ጋር አስተሳስረው ይጀምራሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በየፈርጁ የቀረቡት የያሬድ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች በአመዛኙ ሕወሓት ላይ ማተኮራቸው በግል ፍላጎቱ የመነጩ ሳይሆን ከኢሕአዴግ ተፈጥሯዊ ባሕርይ የመነጨ ሆኖ አናገኘዋለን፡፡ ያሬድ ሕወሓትንም ሆነ መለስን የተመለከቱ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን ሲሰጥ/ሲጽፍ ለማንበብ የምንገደደው ብርቱ አንባቢ፣ ጥልቅ አሰላሳይና ድንቅ የሥነ-ጽሑፍ ችሎታ ስላለው ብቻ አይደለም፡፡
እንደአንጋፋ ፖለቲከኛነቱ ሕወሓትንም ሆነ መለስን ከበረሃ ጀምሮ በቅርበት ስለሚያውቃቸው ጭምር ነው፡፡ በተግባር የተፈተነ ግንዛቤ ያለው ያሬድ፣ ፖለቲካዊ ትንታኔዎቹ ምልሰት ያላቸው በመሆኑ የፖለቲካውን የከፋ ተለዋዋጭነትና የአመራሮቹን መሰሪ ባሕርይ በጊዜ ንጽጽር ለማየት ያስችላል፡፡ ትንታኔዎቹ ቅድመና ድኅረ-ደርግ የማጣቀሻ (ምልሰት) አቀራረብ ያላቸው በመሆኑ የሕወሓትንም ሆነ የመለስን ፖለቲካዊ ስብዕና አበጥሮ ለማስጣት ችሏል፡፡
የያሬድ ብዕር የሕወሓትን የዘመናት እኩይ ድርጊቶቹን በተመለከተ፤ በተለይም የብሔርተኝነት ቁስል የመንቆር አባዜቸውን (44)፣ ብሔራዊ ቅራኔዎችን በማጎን ለጠባብ ብሔርተኝነቱ መገንቢያ መጠቀማቸውን (45፣55)፣ ቅራኔውን የበየኑበት እምነትና ዴሞክራሲያዊ እኩልነትን ተቀብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ አብሮ መኖር ይቻላል በሚሉበት እምነት መካከል ያልረጋ መንፈስ ይፈታተናቸው (62) እንደነበር፣ ኢሕአዴግ የትግራይ ብሔርተኝነት ጥቅምና ፍርሃቶች ማስታገሻ የጎማ ማህተም መሆኑን (73)፣ ከብዙሃኑ ነጥቆ የትግራይ ጥቅም አስጠባቂነቱን (109)፣ ‹የትግራይ ዘመን ዘንድሮ ነው› በሚል ተአብዮ፣ ዛሬ የምናየው የትግራይ ልኂቃን እብለላ-ጥጋብ (255) ምንጩ ከወዴት እንደሆነ፣ ትግሬ የሰፈረበት መሬት ሁሉ የትግራይ ነው የሚለው የግዛት ተስፋፊነት ባሕርያቸውን (48፣150፣257) ከዐቢይ ማሳያዎች ጋር በያሬድ ብዕር ተፍታተው ቀርበዋል፡፡
በተለየ መልኩ ከዛሬ ባለፈ ለመጭው ትውልዶች ተሸጋጋሪ ዕዳ ሆኖ ቀርቦ ያለው የሕወሓት የግዛት መስፋፋትና የኢኮኖሚ ነጠቃ ተግባሩ ነው፡፡ ይኼ የገደል ላይ ሰርዶ ፍለጋ ሩጫ ሕወሓትንም ሆነ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ወዴት እንደሚወስደው ጊዜና ትውልድ መልስ ያላቸው ቢሆንም፣ የያሬድ ብዕር “የለቅሶ አዙሪት ውስጥ ራሳችን እንከታለን፡፡ ልናስብበት ይገባል፤” ይላል፡፡ ሰሚ ካለ፡፡ ያሬድ ሕወሓት ላይ ያቀረባቸው ትንታኔዎች ታሪካዊ ዋጋ ያላቸው ከመሆኑም ባለፈ የድርጅቱን ርዕዮተ ዓለማዊ ልሽቀትና ፖለቲካዊ መበስበስ (110-141) የተነተነበት አቀራረብ ሕወሓትንም ሆነ መለስን ድጋሚ እንድናጠናቸው የሚጋብዝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
በዚህ ረግድ መጽሐፉ የሚያቀብለን መረጃ መለስ ምን ዓይነት ፖለቲከኛ እንደነበር በተለየ አረዳድ ለመቃኘት ይጠቅማል፡፡ ስለ መለስ ዜናዊ የትንኮሳ ባሕርይ (73)፣ ፍጹም ብልግና ስለተሞላባቸው ንግግሮቹ (137) እና አጠቃላይ ስለ አእምሮ ሁኔታው አልተረዳነውም እንጅ ሰውየው Obsessive Compulsive Disorder (OCD) የተሰኘው በሽታ እንደነበረበትና በርካታ ምልክቶች እንደታዮበት (138) መጽሐፉ ያብራራል፡፡ ያሬድ የበሽታውን መጠሪያ ስም “የአይዞህ በለው ቀውስ፤” በሚል ወደ አማርኛ ተርጉሞታል፡፡ መጥፎ አስተሳሰብና የብልግና (አስቀያሚ) አነጋገርን ማዘውተር የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡
ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት ያህል በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ባለጌና አስቀያሚ ንግግሮች በየመድረኩ መናገር፣ ዘውግን መሠረት ያደረጉና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የሚያዋርዱና ቅስም የሚሰብሩ ስድቦችን ማዘውተር፣ የኅሊናና የፖለቲካ እስረኞችን በኢሰብአዊ መንገድ የማስቀጣት ሁኔታ፣ የመለስ ዜናዊ የባሕርይ “ትሩፋቶች” ከነበሩት ውስጥ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የባሕርይ መገለጫዎች በቀጥታ ከ“አይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ምልክቶች ጋር ይገናኛሉ፡፡ አንባቢ ለግንዛቤም ሆነ ለትዝብት እንዲረዳው ከላይ የተጠቀሰውን የበሽታ ዓይነትና ምልክቶቹን በተመለከተ ኢንተርኔት ላይ ቢዳብስ በርካታ መረጃዎችን በብላሽ ያገኛል፡፡ መረጃዎቹን ይዞ የመለስን የፓርላማና የጋዜጣዊ መግለጫ ንግግሮቹን በምልሰት ቢቃኝ ሰውየው የበሽታው ተጠቂ እንደነበር ለማመን ይገደዳል፡፡ አሟሟቱስ ከጭንቅላት ሕመም ጋር በተያያዘ አይደል!?
ያሬድ ይኼኛውን ፖለቲካዊ መጣጥፍ ሲያወዘጋጅ ጊዜው ሐምሌ 1993 ዓ.ም. ነበር፡፡ ያኔም ሆነ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ መለስ ከአንደበቱ ብቻ ሳይሆን ከብዕር ጠብታውም ጋር ስድብ የተዋሐደው ፖለቲከኛ ነበር፡፡ የአንጃው አባል የነበሩትን የሕወሓት አመራሮችን “በክት”፣ ካድሬዎችን “ዝንብ”፣ ፖሊሶችን “ውሾች፣ የመንግሥት ጋዜጠኞችን “አዝማሪዎች”፣ የግሉን ፕረስ ጋዜጠኞች “የቁራ ጩኸት የሚጮኹ”፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን “የጠነባ ኋላቀር አመለካከት ያላቸው”፣ ኢሕአዴግን “ከእንጥሉ የገማ” ወዘተ. እያለ ሲሳደብ ኖሯል፡፡ እነዚህ የስድብ ቃላት “የቦናፓርቲዝም አደጋ” በሚል በ1993 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ካወጣው 129 ገጾች ካሉት ጽሑፉ ጀምሮ ግብዓተ መሬቱ እስከ ተከወነበት ዓመት ድረስ በፓርቲው ልሳኖች ባወጣቸው ጽሑፎቹ፣ በፓርላማ ንግግሮቹ፣ በጋዜጣዊ መግለጫዎቹ የተናገራቸውና በብዕሩ ጠብታ ከተጻፉት ውስጥ እጅግ ጥቂቶቹን ለማሳያ ያህል የተጠቀሱ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ በቅድመ-1993ዓ.ም ከተናገራቸው እነ “ባንዴራ ጨርቅ ነው”፣ ዲያስፖራውን “አልጋ አንጣፊ” ወዘተ. የሚሉ ተንኳሽ ንግግሮቹን ሳንጨምር መሆኑ ነው፡፡
መለስ ዜናዊ ላይ “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ምልክቶችን በማየቱ ስጋት የገባው ያሬድ ሰውየው ባደረበት የአዕምሮ ቀውስ የተነሳ ገና ብዙ ጥፋት ያደርሳል የሚል ስጋት አለኝ (139) ብሎ ነበር፡፡ ያሬድ ይኼን ሲል፣ መለስ ወደ ማይቀርበት ዓለም ለመሄድ  ዐሥራ አንድ ዓመታት ቀርተውት ነበር፡፡ ያሬድ ይኼን ነገር ቀድሞ ከተነበየ በኋላ፣ በዋናነት በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ሰጭነት ድኅረ-ምርጫ 97 አዲስ አበባ ላይ የነበረውን መንግሥታዊ ፍጅት ጨምሮ፤ በጋምቤላ-አኝዋኮች፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ-ኦጋዴን ላይ የደረሰው ዘግናኝ ጨፍጨፋ ሰውየውን በዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተጠያቂ ሊያደርገው በተገባ ነበር፡፡ ምዕራባዊያኑ ከፀረ-ኢትዮጵያ ኀይሎች የሚያገኙት ጥቅም ያለ ይመስል “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ተጠቂውን መለስ ዜናዊን ጭፍጨፋ “ጉዳዩ ያሳስበናል” በሚል ተልካሻ የዲፕሎማሲ ቃላት ደጋግመው አለፉት፡፡ ሰውየው ከሞት ባያመልጥ እንኳ ከፍትሕ አመለጠ፡፡
በጊዜ ሂደት ሁኔታዎች ቢቀያየሩም ሕወሓት ከጫካ አስተሳሰቡ እና ከገንጣይ አስገንጣይ ፖለቲካዊ መሻቱ አልወጣም፡፡ በመሆኑም ድርጅቱን ደግሞ ደጋግሞ በማጥናት ከአገር በታኝ አውዳሚ ተግባሩ ለማስቆም ርዕዮታዊ ትጥቅ ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ ስለ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፖለቲካዊ ስብዕና ድጋሚ ማጥናት አስፈላጊ የሚሆነው ደግሞ ቢጤዎቹ በድርጅቱ የአመራር ቦታ ላይ የተኮለኮሉ በመሆናቸው እና “የአይዞህ በለው ቀውስ” በሽታ ምልክቶችን ስለሚያሳዩ፣ የበሽታቸው ሁኔታ ወደ መለስ ዜናዊ የበሽታ ደረጃ አድጎ አገሪቱን ከእርሱ በከፋ መልኩ ማጥ ውስጥ እንዳይከቷት ለመመከት እንዲያስችል ስለሚረዳን ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ በራሱ የሽታውን ደረጃ ላለማሳደጉ መረጃው የለንምና ዛሬ ላይ የነጋበት ጅብ ባሕርይ እያሳየ ያለውን ሕወሓት በጥንቃቄ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡
መቋጫ
የሕወሓትንም ሆነ የኢሕዴን/ብአዴንን የትግል ታሪኮች በድርጅት እና በአባላት ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት የተጻፉ መጻሕፍትን አንብበናል፡፡ በሁለቱም አካላት የተጻፉት መጻሕፍት ከአቅጣጫ በስተቀር በይዘት ደረጃ መመሳሰል ይበዛባቸዋል፡፡ የድርጅቶቹን “ከምንም መነሳት”፣ “ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር መከተል”፣ “ጥቂቶች ቆራጦች” ስለመሆናቸው፣ “በሕዝብ ድጋፍ” ወዘተ. ድል እንደተቀናጁ በግነታዊ ቃላት ይተርካሉ፡፡ ከበረሃ ጀምሮ በድርጅቶቹ ውስጥ በየጊዜው ያጋጠሙ ችግሮችና የተፈቱበት መንገድ በግልጽነት ለመቅረቡ አጠራጣሪ ነው፡፡ በስማዊው “የግንባር ቀደም ኀይሎች” ስብስብ “መንግሥት” ከሆኑ በኋላ በሚጽፏቸው ድርሳናትም ቢሆን አምባገነንነታቸውን በውስን ልማት ለመሸፈን እና ችግሮቻቸውን ውጫዊ ለማድረግ ሲፍጨረጨሩ የታዘብንበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ኹለቱን ድርጅቶች አብሮ በመሥራት የሚያውቃቸው ያሬድ፣ ከክላሽ እስከ ብዕር ድረስ የተጓዘበትን ያሬዳዊ ትዝታውን ሲያካፍለን፤በታገለበትና በደረሰበት መጠን ሁለቱም ድርጅቶች በረሃ ላይ ሊቀብሯቸው የሞከሯቸውን እውነቶች ፈልፍሎ አውጥቶ ‹እነሆ› ብሎናል፡፡
በግሩም የፖለቲካ ሥነ-ጽሑፍ ችሎታው ተንትኖ ያቀረበልን ሥራ የእርሱን ዘመን ትውልድ ለመረዳትና በሰከነ አዕምሮ ለመገምገም ዕድል ይሰጣል፡፡ ቅንነቱ ካለ እንዲህ ያሉ ዕድሎች በበረከቱ ቁጥር ከታሪክ ፈተናችን ለማለፍ የሚያስችል ፖለቲካዊ መግባባት መፍጠር ይቻለናል፡፡ የያሬድ ጥበቡ መጽሐፍ የፖለቲካ ስሜት ከፍታና ዝቅታ ቢኖረውም፤ ከራስ ታሪክ ጋር ለመታረቅ ያለመ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ ከራሱ ጋር የታረቀ ከሌላው ጋር ለመታረቅ አይቸግረውም፡፡ በዚህ መንገድ ይመስለኛል አገር መገንባት የሚቻለው፡፡ “ያራዳ ልጅ ብሔር የለውም” የሚለውን ተወዳጅ አባባሉን የትኛው የመታወቂያ ደብተሩ ላይ እንደሚያሰፍረው ባላውቅም፣ ያሬድ ጥበቡን የሚያህል አንጋፋ ፖለቲከኛ ወደ አገሩ ተመልሶ የለውጥ ውርጃ ላስቸገራት አገር ምጧን የሚያቀልላት የፖለቲካ ተንታኝ የሚሆንበትን ጊዜ እየተመኘሁ ላብቃ፡፡
Filed in: Amharic