>

የከረሩ ድምጾች - የተስፋና የቀቢጸ ተስፋ ሞገዶች!!  (መስፍን ነጋሽ)

የከረሩ ድምጾች – የተስፋና የቀቢጸ ተስፋ ሞገዶች!! 
መስፍን ነጋሽ
በበጎ ፈቃደኝነት በተነሱ ጥቂት ሰዎች አስተባባሪነት፣ በጥቂት ቀናት ዝግጅት በተጠሩ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፈቃዳቸው በተገኙባቸው ሰለፎች ላይ ከተሰሙ መፈክሮችና ዘፈኖች፣ ከታዩ የጽሑፍ መልእክቶች፣ ከተውለበለቡ ባንዲራዎች ወዘት ውስጥ አንዷን ነጥሎ አውጥቶ፣ የሰልፈኞቹ ሁሉ አቋም፣ አልፎም የሆነ ብሔረሰብ አባላት የጋራ መሻት አስመስሎ ማቅረብ ሙልጭ ያለ የፖለቲካ ነጋዴነት አለዚያም ማስተዋል የጎደለው ተግባር ነው።
ከዚህ በባሰና በአደገኛ መልኩ ደግሞ (እዚህ ባያያዝኩት ምስል ላይ እንደሚታየው) የታየ መፈክር ከመተርጎም አልፈው ያልነበረውንም በመፈብረክ፣ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል፣ አንዱን ለማስጠላት፣ ሌላውን ለማበሳጨት ተግተው የሚሠሩ ዞምቢዎች አሉ።
በየትኛው የአገሪቱ ክፍል የወጡት ሰለፈኞች በእርግጠኝነት የሚጋሩት ኢትዮጵያን እና የለውጥ ተስፋን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያሉት ነገሮች በሙሉ የግለሰቦች ግፋ ቢል የትንንሽ ቡድኖች ምርጫዎችና ስሜቶች ናቸው። ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ አስተሳሰቦች (ብንወዳቸውም ባንወዳቸው) በከረረ ድምጻቸው መሰማታቸው የለውጥ ወቅት ባህርይ ነው። እነዚህ የከረሩ ድምጾች የለውጡ አንቀሳቃሾች አይደሉም። እንዳይሰሙ ልንከለክላቸውም አይገባም፤ በሐሳብ ልንሞግታቸው እንጂ። በእነዚህ ጠርዝ ላይ የቆሙ የከረሩ ድምጾች ላይ ጉልበት ማባከን አስፈላጊ አይደለም። በተቃራኒው ግን እነዚህ የከረሩ ድምጾች ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆኑ የማድረግ ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ በእነርሱ አጀንዳ እንዳንጠመድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካለደረግን የለውጡን ጅምር አደጋ ላይ እንደምንጠለው ልብ ልንል ይገባል።
በሁሉም ጉዳይ ላይ አቋም ለመያዝ መሯሯጥ፣ በሁሉም አቋም ላይ በአንድ ጊዜ ለመነጋገርና ለመከራከር መሞከር አዋቂነት አይደለም። በቀላሉ ተጠምዝዞ መሣሪያ ለመሆን የሚያጋልጥ የስሜት ጎረምሳነት ነው።
አሁን ያለንበት ወቅት የተስፋና የቀቢጸ ተስፋ ሞገዶች የሚላተሙበት ዘመን ነው። ሞገድ በባህርይው ጥፋት ሳያደርስ አያልፍም። ግን ያልፋል። ውስጣዊና ውጫዊ ሞገዶቹ ይሰክናሉ። ሞገዱ እስኪያልፍ ድረስ ሰዎችና ቡድኖች ከሕሊና ይልቅ ለሞገዶቹ ይታዘዛሉ። መጠንቀቅ ያለብን ለዚህ ነው። እዚህ ሞገድ ላይ ተሳፍሮ፣ በነጣላ ክስተት ላይ እየተንጠለጠሉ ፍርድ መስጠት ያው የሞገዱ አካል መሆንን ከማመላከት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። የሚበጀው የተስፋና የወንድማማችነት ሞገድ እንዲያሸንፍ አስተዋጽዖ ማድረግ ነው። ቢያንስ የቀቢጸ ተስፋ ሞገድ እንዲጠናከር አለማድረግ ለሁላችንም ይበጃል።
አውቀን እንታረም! እንዲል ጸሐፊ።
Filed in: Amharic