>

ዛሬ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ   ተአምራዊና አጽናኝ የሆነ  ቃል ተሰማ!!! 

ዛሬ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ
  ተአምራዊና አጽናኝ የሆነ  ቃል ተሰማ!!!
           *★★★*
ዘመድኩን በቀለ
ሀገረ ስብከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አይነት መሪ ያገኘ ይመስላል። ለተሿሚዎቹ ፍጻሜውን ያሳምርላቸው። 
 
~ ቤተክርስቲያናችንን መለወጥ ከፈለግን የተማሩ ሊቃውንት ይከበሩ። 
 
~ ከውሻ ጋር ታግለው ቁራሽ ለምነው የተማሩት ሊቃውንት ትክክለኛውን ሥፍራ ይያዙ።
 
~ ቅዳሴን በቴፕ ያጠኑ፣ ወረቡን በካሴት ቀድተው ያጠኑ፣ የምእመናን ፊት እየገረፋቸው ከተማሩት ሊቃውንት በላይ ሆነው የሚመሩበት ጊዜ ያብቃ። 
 
~ ሰዎች በሚጠቀሙት ቁሳቁስ እና በሚለብሱት ልብስ የለበሱት አይመዘኑ። በአፈ ጮሌነትም አይከበሩ። 
 
~ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አድባራት ሥራዬ የተሳካ ይሆን ዘንድ ለ3 ቀን ያህል ጸሎት ይያዝልኝ ብለዋል። ተመስገን አምላኬ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ በጸሎታችሁ አስቡኝ ዘመን ያሸጋገርከን ተመስገንልን።
መምህር ይቅርባይ እንዳለ በዋና ሥራ አስኪያጅነት በተሾሙባት አዲስ አበባ ፤ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደረገላቸው፣
~ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዛሬው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ልክ ዶክተር ዐቢይ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ እንደወሰነው ሁሉ መምህር ይቅርባይም በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚታየውን የዘቀጠ አሠራርና፣ ቤተክርስቲያኒቷን ከሚያሰድባት አሠራሮች ለማፋታት በቁርጠኝነት መነሳታቸውን በይፋ አውጀዋል።
መቼም የዋና ሥራ አስኪያጁ የዛሬ የመጀመሪያ ቀን ንግግር የምጽፈውን፣ የምይዝ የምጨብጠውን ነው ያሳጣኝ። እስቲ የንግግራቸውን ሙሉ ቃል አንብቡና አስተያየታችሁን ሥጡበት። ኡፍፍፍፍፎፎፎይ  ተመስገን አምላኬ ለአንተ ምን ይሳነሃል። ባይሠሩበት እንኳ እንዲህ እምባን የሚያብስ ንግግር እንደመስማት ምን የሚያስደስት ነገር አለ ? ምንም። ምንም የለም ።
ለማንኛውም እነሆ የዋና ሥራ አስኪያጁን ንግግር ተጋበዙልኝ።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ
ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየመምሪያ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች የአድባራትና የገዳማት አለቆች፣ እንዲሁም ጸሓፊዎች በዚህ አቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ አለቆች የተገኛችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች።
በቅድሚያ እንዲህ አምራችሁና ተውባችሁ በሙሉ ፍላጎትና በውሳጣዊ ደስታ ተሞልታችሁ ይህንን የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ለማሳመር በዚህ ስፍራ በመገኘታችሁና በዚህ ከባድና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በእርጋታ ሆናችሁ ሰላምን ለማስፈን ላሳያችሁት መንፈሳዊ አባትነታችሁ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን በልዑል እግዚአብሔር ስም አቀርባለሁ
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጣም በርካታ ካህናትን ያቀፈና ባልብዙ ችግርም ጭምር በመሆኑ ምርጥ የሥራ ተሞክሮዎች እንዳሉት ሁሉ ብዙ የሥራ ውድቀቶችም አሉት። ምንም እንኳ ሥራው አስቸጋሪ ባይሆንም ነገር ግን ከሥራው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ግለሰቦች ጠባይ ሥራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው መገመት አያዳግትም። ይሁን እንጂ በጋራ ሆነን ሳንበጣጠስ፣ ሳንለያይ፣ ሳንገፋፋ፣  ዘርና ጎሳ ሳንቆጥር አብረን በጋራ ከሠራን ከተመካከርን እኔ ከበላሁ ሌላው ጦሙን ይደር የሚለውን #የሆዳሞችን አመለካከት ከተውን፣ እንዲሁም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለውን የአህያይቱን አባባል ከተጸየፍን እንኳን ለእኛ የሚሆን ሰላም ለዓለም የሚበቃ ሰላም ይኖረናል።
አሁን የምናየው ሁኔታ ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ብቻም ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒ እና ከመንፈሳውያን አባቶች ወንድሞች ቀርቶ ከዓለማውያን ሰዎች እንኳ የማይጠበቅ መገር በመሆኑ እያንዳንዳችን እንደየአቅማችን ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን። ቤተክርስትያናችንንም ዋጋ እናስከፍላታን።
~ ቤተክርስቲያናችንን መለወጥ ከፈለግን የተማሩ ሊቃውንት ይከበሩ።
~ ከውሻ ጋር ታግለው ቁራሽ ለምነው የተማሩት ሊቃውንት ትክክለኛውን ሥፍራ ይያዙ።
~ ቅዳሴን በቴፕ ያጠኑ፣ ወረቡን በካሴት ቀድተው ያጠኑ፣ የምእመናን ፊት እየገረፋቸው ከተማሩት ሊቃውንት በላይ ሆነው የሚመሩበት ጊዜ ያብቃ።
~ ሰዎች በሚጠቀሙት ቁሳቁስ እና በሚለብሱት ልብስ የለበሱት አይመዘኑ። በአፈ ጮሌነትም አይከበሩ።
መጽሐፍ እንደሚለው ” ያንን ጠቢብ ድኻ ሰው ማንም አላሰበውም ነውና ጠቢባን ወድቀዋል። ያልተማሩት ነግሠዋል። ሀቀኞች ጎስቁለዋል። ደላሎች ከብረዋል። ስንዴ ከእንክርዳድ ዱቄት ከአመድ ተቀላቅለዋል። እንዚህ ተለይተው ታወቁ። በአንድ ወንበር አይደባለቁ።ሁሉም አቅማቸውን ይወቁ። ያልተማሩ ለመማር የተማሩት ለማስተማር ወገባቸውን ይታጠቁ።
ክቡራን ሊቃነ መናብርት ዓለም አንድ በሆነችበት በዚህ ሰዓት ብንከፋፈል ራሷ ዓለም ትስቅብናለች። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላም የኢትዮጵያ ሰላም ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁከትም ኢትዮጵያ ሁከት ነው። ስለዚህ ለሃገራችን እና ለህዝባችን እንዲሁም ለራሳችን ስንል ሰላምን እናስፍን። በአድባራት ላይ ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ መብላት ያቁም። ውኃውን በጋራ እንጠቀም።
በሥራ አሥኪያጆችና በሠራተኞች መሀል ያሉት ደላሎች ይውጡ። በደላሎች የተነሳ ብዙዎች ተርበዋል። ከሥራ ተፈናቅለዋል። ቤተሰብ ብበትነዋል። ሁሉም ሰው ጊዳዩን እኩል ያቅርብ። ሁሉም ልጅ እንጂ ማንም የእንጀራ ልጅ አይሁን። በቦታው የተመደብነው ባለሥልጣናት ሰዓታችንን አክብረን ሥራውን ቢሮ ውስጥ እንሥራ። የቢሮ ሥራ በሆቴል አይሠራ። ባለ ጉዳይ የሚያቀርበው አቤቱታ ይሳካ አይሳካም በስርዓት ይስተናገድ። ምክንያቱም እኛጋ የሚቀርበው ባለጉዳይ ሌሊት ማኅሌቱን፣ ሰዓታቱን፣ ኪዳኑንና ቅዳሴውን ጨርሶ አገልግሎ መከራውን አይቶ የሚመጣብንን ጭምር ነውና እናክብረው።
የተከበራችሁ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ኃላፊዎች እንድትመሩ የተሰጣችሁን ቤተክርስቲያን #ከተሃድሶ_መናፍቃን ጠብቁ። የቀሚስ ውስጥ ምንፍቅና ይቁም። የፈረጂያ ስር ምንፍቅና ከቤተክርስቲያን ይወጣ። በአጠቃላይ መናፍቅ የቤተክርስቲያናችንን እንጀራ አይብላ። የቤተክርስቲያናችን የቀደመ ክብሯ ይመለስ። የክህነት ልዕልና የመለስ። በእኛው በአገልጋዮቿ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ክብሯን አጥታለች። የቤተክርስቲያናችን ክብር የሆነውን ቆባን፣ ቀሚሷን፣ እና መስቀሉን ለብሶ በየመጠጥ ቤቱና በየአልባሌ ቦታ መታየቱ ይቁም። የቀደመው የአባቶቻችን ካህናት ሥነ ምግባር ይመለስ።
በየአብያተ ክርስቲያናቱ የተመደቡ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልጋዮች በደጅ ጠኚዎች ብቻ እይሸፈኑ። የደመወዝ ቀን ብቻ ብቅ ማለት ይቁም። አንዳንድ ቤተክርስቲያን አክብራ የሾመቻቸው አስተዳዳሪዎች ስልጣንን መከታ በማድረግ አባቶቻችን ያቆዩልንን የቤተክርስቲያን መሬት የአለአግባብ መሸጥና ማከራየት ይቁም። 1ካሬ 40ሺ በሚሸጥበት መዲናችን በሁለት ብርና በ7ት ብሎም በሃያ ብር የቤተክርስቲያንን መሬት ማከራየት ይቁም።
መናፍቃን ቢሆኑ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን በድሉ? ምንፍቅናቸውን በኦርቶዶክሳዊት ትምህርት ድል እናደርጋለን። ካሻንም ከመካከላችን እንዲወጡ እናወግዛቸዋለን። ታዲያ በጉያ ውስጥ የተቀመጡትን ” ክርስቲያን ያልሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ማን ያውግዝልን? እንዲህ ዓይነቱን የመሪዎችን ጭካኔ የሚመለከቱ ምእመናን ይህችን ቅድስት ሃይማኖታቸውን ትተው እያዘኑ ፣ እያለቀሱ ወደ መናፍቃን ጎራ ይካተታሉ።  ታዲያ በቃለ እግዚአብሔር ሰብከው ከወሰዱብን ይልቅ በመጥፎ ሥነ ምግባራችን እንቅፋት ሆነ ሆነን ያባረርናቸውን ዓለም ይቁጠራቸው። ስለዚህ በጋራ ሆነን ብልሹ አሠራርን ወደ መልካም አስተዳደር እናምጣ።
ከዚህ በፊት በነበረው የአስተዳደር ሁኔታ በግፍ የተበደላችሁ፣ ፍትሕ በማጣት የተሰቃያችሁትን እና ልዩ ልዩ የሞራል እና ከሥራ የመፈናቀል አደጋ ውስጥ የገባችሁትን ሁሉ በእኔና የጽሕፈት ቤታችን ሠራተኞች ስም ይቅርታ እየጠየቅሁ የደብር አስተዳዳሪዎችም በግፍ የተባረሩትን አጣርተን ከቅዱስ አባታችን እና ከቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ተቀብለን በምናደርገው የመፍትሔ አቅጣጫ ሁሉ ከጎናችን በመሆን እንድትደግፉን ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በዛሬው ዕለት ለተደረገው አቀባበል ዋናው ምክንያቱ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አምነው የመደቡት ምደባ በመሆኑ ጉባኤው ቅዱስነታቸውን እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን እንዲያመሰግኑልኝ በትሕትና እጠይቃለሁ።
በመጨረሻ አዲሱ የሥራ አመራር የተሳካ ውጤታማ ሥራ ይሠራ ዘንድ በጋራ ሆነን በአደባባይ የተሰደበችውን ቤተክርስቲያን ከስድቧ እናላቅቃት ዘንድ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ለአሳራጊዎች አመራር እንዳያስተላልፉልን በእኔና ከእኔ ጋር ለተመደቡ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ወደፊት ሊመደቡ ለሚችሉ ሠራተኞች የሦስት ቀን ጸሎት ብፁዕ አባታችን እንዲያውጁልን በአክብሮት እጠይቃለሁ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።
በዚህ ላይ ምንም አይነት ቃላት መጨመር ነጭ ልብስን እንደማቆሸሽ ስለሚቆጠር ጮጋ ብዬ አልፌዋለሁ።
የምነግራችሁ ነገር ቢኖር ግን መምህር ይቅርባይንና ባልደረባዎቻቸውን በሀሳብም ሆነ ከሁሉም በላይ በጸሎት በማገዝ የቤተክርስቲያንን የቀደመ ክብሯን እናስመልስ።
መምህር ሆይ መልካም የሥራ ዘመን ይሆንልዎት ዘንድ ከልቤ ተመኘሁ። እመቤቴ ከእርስዎ ጋር ትሁን።
ሻሎም !  ሰላም ! 
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ሰኔ 25/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ ።
Filed in: Amharic