>

መጅሊስን በተመለከተ ወሳኝና ወቅታዊ መረጃዎች   (አብዱረሂም አህመድ)

መጅሊስን በተመለከተ ወሳኝና ወቅታዊ መረጃዎች  
አብዱረሂም አህመድ
ህገ-ወጡ መጅሊስ ስልጣኑን ለማስጠበቅና  በመጣው ለውጥ ምክኒያት ከስልጣኔ ልነሳ ነው  በሚል ስጋት  የተለያዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን እየፈጸመ መሆኑን ምንጮቻችን ገለጹ ።
የመጀመሪያው እንቅስቅቃሴ መጅሊሱን በእጅ አዙር ሲመሩት ከነበረው የቀድሞው ህወሃት ታጋዮች ከነ አቦይ ስብሃት ጋር በመሆን የአቦይ ስብሃት ወዳጅ ና የሀገር ሰው  የሆኑት የኡለማ ምክር ቤቱ ምክትል  ፕሬዝዳንት የሆኑት ታጋይ ኢዘዲን  ሙስሊሙን የሚያስቆጣ መግለጫዎችን በመስጠት ላይ ናቸው።  የቀድሞ የመጅሊስ ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ስለግለሰቡ እንዳጋለጡት  የድምጽ መቅጃ በመያዝ እየቀዳ ለህወሃቶች ሲያቀብል የነበረ መሆኑ ይታወቃል። አሁንም የቀድሞውን ስርአት ለማስመለስ   ለውጡን ለማደናቀፍና በአሁኑ ጊዜ ስልጣናቸው የተመናመነውን ህወሃቶችን ለመጥቀም ና ለውጡን ለመቅለበስ ፣ሙስሊሙን  በመተንኮስት እንቅስቃሴ እያደረጉት  መሆኑ ታውቋል።
ሌላኛው የጀመሩት ዘመቻ በየክፍለሃገሩ ያሉ አባላቶቻቸውን በመጪው እሮብ ስብሰባ  ጠርተዋል። ስብሰባውን ማንም እንዳይቀር በሚል  በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ነው የጠሩት። ለአባላቶቻቸውም  ዶክተር አብይን አነጋግረነው ከጎናችሁ ነኝ ራሳችሁን አጠናክሩ ብሎናል የሚል ፕሮፖጋንዳ እየነዙ ይገኛሉ። ዶክተሩ ይኼን ብሏቸው ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም ።
  በሌላ በኩል ከያዙት እቅድ አንዱ በመጪው ጊዜ የመጅሊስ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ እኛው ስልጣናችንን  መያዝ አለብን ወይም ከኛ ጋር የጥቅም ቁርኝት ያለው ነው መያዝ ያለበት በማለት በየክፍለሃገሩ እየዞሩ የመቀስቀስና ግጭት  የማስነሳት እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከከፋፈሉ በኋላ መንግስትም የሙስሊሙን ጥያቄ እንዳልመልስ መጀመሪያ እናንተ አልተስማማችሁም የሚል መልስ እንዲሰጥና ስልጣናቸውን እንዲያቆይላቸው የማድረግም እቅድ እንዳላቸው ታውቋል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ መጅሊሶች የጀመሩት እኩይ ተግባር በመረዳት በንቃት ሁሉን ነገር እንዲከታተልና በቀጣይ ጊዜ የመጅሊስ ምርጫ የሚካሄድም ከሆነ ለሙስሊሙ ይበጃሉ የሚላቸውን በአካባቢው እያሰበበት ቢቆይ መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡም አሉ። ሙስሊሙ ከምንጊዜውም በላይ አንድነቱን በማጠናከር  የተጀመረውም አገራዊ ለውጥ  እንዳደናቀፍ ማድረግ እንዳለበትም ተገልጿል ።
Filed in: Amharic