ቢመረንም ልንውጠው የሚገባ እውነታ!!!
ዮናታን ተስፋዬ
* ይሄንን የማሳይህ ልለያይህ አይደለም
ለተራ ብሽሽቅም አይደለም
* ይህን የማሳይህ አንድ ብንሆንም አንድአይነት እንዳልሆንን እንድትረዳው ነው የጋራ ቤታችንን ከማህከል ላይ ተገናኝተን እንድንገነባ ነው
* ይህን እውነታ ባሳይህም ካንተ ባላነሰ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ – ካንተ ባላነሰ አስብላታለሁ
ይህ ባንዲራ የኦነግ አይደለም። ይህ ባንዲራ የድርጅት አይደለም – ይህ ባንዲራ የኦሮሞ ህዝብ ለነፃነቱ የከፈለውን ዋጋ የሚወክልበት ልዩ ቀለሙ ነው። ኦነግ ህዝቡ ልብ ውስጥ ገብቶ ሲያበቃ- እንደ ድርጅት ሲከፋፋል መንፈሱ ያልጠፋው የህዝቡን ስሜት ስላንፀባረቀ እንጂ ኦነግ ለህዝቡ የሰጠው ነገር የለም – ህዝብ እወክልሀለሁ ላለው አካል መታገያውን መለያ አበረከተ እንጂ ከድርጅት አልወሰደም!
የኦሮሞ ወገንህ የገዳ ስርአቱ መገለጫ ዓላማውን ጥቁር ቀይ ነጭ እና የነፃነት ወካዩን ቀይ አረንጓዴ ቀይ ከመሃሉ በቢጫ መደብ ኦዳ ያረፈበት ባንዲራ እኔ እና አንተ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የነፃነት ባንዲራችንን የምንወደውን ያክል ይወደዋል – ይሞትለታል።
መቻቻል እንዲሰፍን የኔ ያለውን መለያውን ባትወድለትም አክብርለት – ተሰዶለታል ታስሮለታል ሞቶለታል …. መለያህ ይሄ ነው አትበለው – እሱ ለራሱ ያውቃል!
አዎ አንድ ቤት የጋራ ሀገር አለን – አዎ የጋራ መገለጫ ያስፈልገናል – የሁላችን የምንለው ባንዲራ ያስፈልገናል –
አምናለሁ ይኖረናል!!!
ስንከባበር አንድ መለያ ይኖረናል – አንድ በንዲራ አብረን እናውለበልባለን። ልዩነታችንን እውቅና ስንሰጣጥ ለጋራ ነገራችንም አንድ መለያ ላይ ተስማምተን አንድ ባንዲራ እኩል ዘምረን ከሰንደቁ ከፍ አርገን እንሰቅለዋለን።
መደመራችን እንዲያ ሲሆን ይሰምራል – ያምራል! ሀገር እንዲያ እንዲያ እያለ ይገነባል። ዴሞክራሲም እንዲህ የሰውን መብት በማክበር ይጎለብታል
ድል ለዴሞክራሲ!