>
5:16 pm - Thursday May 24, 5742

ጊዜ ጠባቂ ቦንብ ...(ዳንኤል ክብረት)

ጊዜ ጠባቂ ቦንብ . . ዳንኤል ክብረት

አንድን ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ በተመለከተ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደረጉ አሉታዊ የገጽታ ግንባታዎች ውጤታቸው ከሚታሰበውም የከፋ ነው፡፡ በዓለም ላይ አደጋ ላይ የወደቁ ማኅበረሰቦችን ታሪክ ስንመለከት ከሁለት ወገን የመጡ አካላት የቆሰቆሱት እሳት ያስከተለውን ረመጥ እናይባቸዋለን፡፡ አንደኛው እነርሱን ከሚወደው ወገን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከሚጠላቸው ወገን ነው፡፡
የተጠቂው ወገን ነኝ የሚለው አካል ያልተሰጠውን ውክልና እየወሰደ የሚፈጽማቸው ተግባራትና የሚያቀርባቸው ሐሳቦች በተቃራኒ ሆነው ነገሩን ለሚቆሰቁሱት ቢላዋ ያቀብላል፡፡
በጣት የሚቆጠሩ ልዩ ተጠቃሚዎች ሚሊዮኖችን ወክለው ለመታየት ይጥራሉ፡፡ እፍኝ የማይሞሉ አቀንቃኞች የማኅበረሰቡ አፈ ጉባኤ አድርገው ራሳቸውን እየሾሙ የሚናገሯቸው ንግግሮች የዚያ ማኅበረሰብ አቋም መስለው እንዲታዩ ይተጋሉ፡፡
በአንድ ማኅበረሰብ ስም ጥቅም የሚያገኙ አካላት በየዘመናቱ ይፈጠራሉ፡፡ በክርስትናና በእስልምና ስም በተፈጸሙ ወረራዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ቅኝ ግዛቶች፣ ጦርነቶችና ጭቆናዎች ተጠቃሚዎቹ አማንያኑ አይደሉም፡፡ ተጠቃሚዎቹ በእምነቱና በአማንያኑ ስም የሚነግዱት አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት እምነቱንም ሆነ አማንያኑን የሚፈልጓቸው ለሁለት ነገር ነው፡፡ ለምክንያትነትና ለከለላነት፡፡ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ግለሰባዊ ስግብግብነትና የሥልጣን ጥመኝነት ላስከተለው ክፉ ተግባር የተቀደሰው ሃይማኖት ምክንያት እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዘራፊዎቹና ገዳዮቹ እንዳይነኩ እምነቱን ለሽፋንነት ይፈልጉታል፡፡ እነርሱን መንካት እምነቱን መንካት ተደርጎ እንዲወሰድ፡፡ በዘር ከለላ ተከልለው የሚበዘብዙና የሚጨቁኑ ሰዎችም ይሄው ነው መንገዳቸው፡፡
በአንድ ማኅበረሰብ ስም የሚነግዱት አካላት በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጥሩት የተበላሸ ሥዕልም አለ፡፡ የእነርሱ መጠቀምና ክብር፣ ሥልጣን ማግኘትና መግዛት የማኅበረሰቡ ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርጉታል፡፡ በተለይ ደግሞ ግልጽነትና ጠያቂነት ባልዳበረበት ማኅበረሰብ ውስጥ እገሌ እና እገሊት፣ ይሄና ያ፣ እንዲህና እንዲያ ሁሉንም የሚገልጡ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጅምላ ፍረጃ ያጋልጣል፡፡ አበበ ተጠቀመ ማለት አበበ የተገኘበት ማኅበረሰብም ተጠቀመ ማለት ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ አበበም እንደዚያ እንዲሆንለት ይፈልጋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዐውቀውና ሳያውቁት ሌላውን ማኅበረሰብ የማጥላላት፣ የማናናቅና የመፈረጅ ዘመቻ የሚያደርጉም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግለሰብን ከማኅበረሰብ መለየት ያቃታቸው ናቸው፡፡ አንድ በሬ ከወጋቸው በሬዎችን ሁሉ የሚጠሉና ሊያርዱ የሚነሡ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ምንጊዜም የሚጠቀሰው በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን ክርስቶስን የተቃወሙት፣ ያስፈረዱበትና የሰቀሉት ከአይሁድ ወገን የተገኙ ባለ ሥልጣናትና ጥቅመኞች ቢሆኑም፣ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያትና ክርስቲያኖችም ከአይሁድ ወገን የተገኙ ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ በየዘመናቱ የተገለጠው ግን ስለ ሰቃዮቹ አይሁድ እንጂ ስለ ክርስቲያኖቹ አይሁድ አልነበረም፡፡ በጅምላ ‹አይሁድ ይህንን አደረጉ› እየተባለ የተነገረው ነገር ከ40 ሚሊዮን በላይ አይሁድ ያለቁበትን ጥፋት በየዘመናቱ አምጥቷል፡፡
በዘመነ ክርስቶስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አይሁድ እንደነበሩ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይናገራል፡፡ ከእነዚህ መካከል ግን በክርስቶስ መከራና ሞት የተሳተፉት ከአምስት ሺ አይበልጡም፡፡ መከራው ግን ለሁሉም ተረፈ፡፡
በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ በየቀልዶቻችንና በየዘፈኖቻችን የምናስተላልፈው አንድን ወገን የማስጠላትና የማክፋፋት ዘመቻ ማጣፊያው የሚያጥር ነው፡፡ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ የሚቀመጡት እነርሱ ናቸው፡፡ ልጆቻችን ስለዚያኛው ማኅበረሰብ የሚኖራቸውን አመለካከት የሚቀርጹት በነዚህ ጽሑፎች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነው፡፡ በሀገራችን አንድን ማኅበረሰብ የሚያጥላሉ ዘፈኖች ቦታ እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡፡ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያጠቁ የፕሮፓጋንዳ ቃላት ተፈጥረዋል፤ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያሸማቅቁ መግለጫዎች በባለሥልጣናት ደረጃ ተሰጥተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሌሎቹ ጋር እየተደመሩ የተጠቂነት ስሜት የሚሰማው፣ራሱን ወደመከላከል የሚገባ፣ሕልውናው አደጋ ላይ መድረሱን ያመነ ማኅበረሰብ ፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ያለው ማኅበረሰብ ሲፈጠር ደግሞ ከድልድይ ይልቅ ግንብ እየገነባ ከሌላው ጋር መራራቅንና መከለልን ይመርጣል፡፡
በአውሮፓ ከ16ኛው መክዘ በኋላ ለተስፋፋው የፀረ ሴማዊነት ስሜት የታላቁ ጸሐፌ ተውኔት የሼክስፒር ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር አስተዋጽዖ ማድረጉ ይነገራል፡፡ የቬነሱ ነጋዴ ዋና ገጸ ባሕርይ ሻይሎክ የተባለ ገብጋባ ይሁዲ ነው፡፡ ሻይሎክ የዕብራይስጥ ስም አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹ሳላን› ከተሰኘውና የሴም የልጅ ልጅ፣ የዔቦር አባት ከሆነው ሰው ስም የተቀዳ መሆኑ ይታመናል፡፡ የሻይሎክ ገብጋባነትና ጭካኔ ለከት የለውም፡፡ ከእርሱ ገንዘብ የተበደረው ክርስቲያኑ አንቶኒዮ መክፈል ቢያቅተው መያዣው ከአንቶኒዮ ሰውነት የሚቆረጥ አንድ ሙዳ ሥጋ ነው፡፡ አንቶኒዮ ብድሩን መክፈል አቃተው፡፡ ሻይሎክም ሙዳ ሥጋውን ከአንቶኒዮ ሰውነት ቆርጦ ለመውሰድ ተነሣ፡፡
ሼክስፒር ይህንን ድራማ የጻፈበት የኤልሳቤጥ ዘመን(Elizabethan Era – 1558-1605) የሚባለው ጊዜ እንግሊዞች በፀረ ሴማዊነት የተለከፉበት ዘመን ነበር፡፡ ከ1290 ጀምረው ከእንግሊዝ የተባረሩት አይሁድ ወደ እንግሊዝ ለመግባት አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ የድራማው መቼት በሆነው ቬነስ ደግሞ አይሁድ ይጠላሉ፤ ለጥቃት የሚያጋልጥ የተለየ የመለያ ልብስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ፡፡ በሼክስፒር ዘመን የነበሩ ድርሰቶች፣ ቀልዶች፣ ሥዕሎችና ድራማዎች አይሁድን ገብጋቦች፣ ክፉዎችና አጭበርባሪዎች አድርገው የሚስሉ ነበሩ፡፡ የሼክስፒርን ድርሰቶች ያጠኑ ሊቃውንትም ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር ‹የቬነሱ ይሁዲ› እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይገልጣሉ፡፡ ይህም ክሪስቶፈር ማርሎዊ ከደረሰው ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ጋር ያመሳስለዋል፡፡ በ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ውስጥ የሚገኘው ይሁዲው ባራባስ እንደ ሻይሎክ ክፉ ነው፡፡ የቬነሱ ነጋዴ የሚያልቀው ሻይሎክ ወደ ክርስትና ሲመለስ ነው፡፡
ይህ በሼክስፒር ድርስት ውስጥ የተሳለው ይሁዲ ገጸ ባሕርይ አይሁድ ቀድሞ ከተሳሉበት ገጽታ ጋር ተደምሮ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታዩበትን መነጽር አበላሸው፡፡ ስለ እነርሱ ክፉ መናገር፣ መጻፍና መቀለድ የተፈቀደ መሰለ፡፡ ለእነርሱ የሚከራከርም ጠፋ፡፡ በኋላ ዘመን በአይሁድ ላይ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ያመጡት እነዚህን የመሰሉ ድርሰቶች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነበሩ፡፡
ዛሬም እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁለቱም ወገን ልንርቅ ይገባናል፡፡ የሌላችሁን የማኅበረሰብ ውክልና ለሥልጣናችሁ፣ ጥቅማችሁና ለክብራችሁ ስትሉ የምታቀነቅኑ ተቆጠቡ፡፡ ማንም አልወከላችሁም፡፡ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤትም ይህንን አያረጋግጥላችሁም፡፡ ሕዝቡ ያላለውን በሕዝብ ስም አትናገሩ፡፡ እናንተ ስትጠግቡ ሕዝቡ እንደጠገበ አታስመስሉት፤ እናንተ ሲያማችሁም ሕዝቡ እንደታመመ አታስቃስቱት፡፡ እናንተ ስትራቡ ሕዝብ የተራበ አድርጋችሁ አትሳሉት፤ ዕዳችሁን ብቻችሁን ውሰዱ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ስለ አንድ ሕዝብ በጅምላ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች፣ ቀልዶች፣ ጽሑፎች፣ ዘፈኖች፣ ግለሰቦችን ጠቅመው ሕዝብን ይጎዳሉ፡፡ ይበልጥ ደግሞ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ ተቀርጸው እንደ ጊዜ ጠባቂ ቦንብ ይቀመጣሉ፡፡ ለሕዝብ ሲባል ግለሰቦችን መተው እንጂ ለግለሰቦች ሲባል ሕዝብን ማጥፋት ሕጋዊም ሞራላዊም አይደለም፡፡
Filed in: Amharic