በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያም “SBS” ራዲዩ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሰማሁት። የወ/ሮ ትርፉ ንግግር ፍፁም ያልተጠበቀ ከመሆኑ በተጨማሪ ህወሓት ውስጥ ያለውን ክፍፍል በግልፅ የሚጠቁም ነው። በእርግጥ ሴትየዋ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት እዚህ ግባ የሚባል የፖለቲካ ሆነ ዲፕሎማሲ ብቃትና ክህሎት ኖሯቸው አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ አንደኛ፡- የህወሓት ታጋይ በመሆናቸው፣ ሁለተኛ ደግሞ የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕረዜዳንት የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት በመሆናቸው ነው። በቃለ ምልልሱ የተናገሩት ነገርም ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርገውም ይሄ ነው። ስለዚህ የአምባሳደር ትርፉ ንግግር ምን ይጠቁማል፡-
አንደኛ፡- አምባሳደሯ በዶ/ር አብይ እየተወሰደ ላለው የለውጥ እርምጃ ድጋፋቸውን መግለፃቸው፣ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ በግልፅ ከማውገዛቸው በተጨማሪ የፀጥታ ኃይሉን ተጠያቂ ማድረጋቸው፣ እንዲሁም የለውጡን ሂደት የማይደግፉ ኪራይ ሰብሳቢዎች በፀጥታ ኃይሉ ውስጥ መሰግሰጋቸውንና ሊወገዱ እንደሚገባ መጥቀሳቸው የህወሓት መስራችን የሆኑ አንጋፋ የድርጅቱ አመራሮች፣ እንዲሁም በዶ/ር አብይ ከስልጣን የተወገዱ የቀድሞ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ከሚያራምዱት አቋምና አመለካከት ጋር ፍፁም የተለየ ነው። ይህ የሆነው ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የተለየ አቋምና አመለካከት ማራመድ እንደ ወንጀል በሚቆጠርበት ህወሓት ውስጥ መሆኑ በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል በግልፅ ይጠቁማል።
ሁለተኛ፡- አምባሳደር ትርፉ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ህወሓት ውስጥ በተደረገው የስልጣን ሹም ሽር ቅሬታ እንደነበራቸው ይታወቃል። ቅድም እንዳልኩት አምባሳደሯ በራሷ የተለየ አቋምና አመለካከት ስለነበራት ሳይሆን በዋናነት ባለቤቷ አቶ አባይ ወልዱ እና አጋሮቻቸው ከስልጣን የተገፉበት ሁኔታ ቅር አሰኝቷቸዋል። ሆኖም ግን፣ እሳቸውም ሆኑ የአቶ አባይ ወልዱ ቡድን አዲስ ወደ ስልጣን የመጡትን የህወሓት አመራሮች በአደባባይ ለመጋፈጥ አልቻሉም። ምክንያቱም ህወሓት የሃሳብና አመለካከት ልዩነትን ተቀብሎ የማስተናገድ ባህል የለውም። ከዚህ በተጨማሪ እነ አባይ ወልዱ ይህን ለማድረግ አቅምና ድጋፍ አልነበራቸውም።
ይሁን እንጂ፣ የአባይ ወልዱ ቡድን ከስልጣን ተገፍቶ ከመወገዱ በፊት ከእነ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በኦህዴድና ህወሓት መካከል የተፈጠረው የኃይል ሽኩቻ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። እነ አባይ ወልዱ በአቦይ ስብሃት ቡድን ያለ ርህራሄ ተጠራርገው ከስልጣን የተወገዱበት አንዱ ምክንያት ለእነ ለማ መገርሳ የተለሳለሰ አቋም በመያዛቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ዶ/ር አብይ አህመድ ጠ/ሚኒስትር ከሆነ በኋላ የአቦይ ሰብሃት ቡድንን ጠራርጎ እያስወገዳቸው እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት የእነ አባይ ስብሃትን ቡድን እየተዳከመ ሲሄድ የእነ አባይ ወልዱ ቡድን አንፃራዊ አቅምና ጥንካሬ እያገኘ መምጣቱ እሙን ነው። ከዚህ በተጨማሪ አክራሪ አቋም ያላቸው የእነ አቦይ ስብሃት ቡድን አባላት የሆኑ የህወሓት አመራሮች ከእነ ዶ/ር አብይ እና ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ወደ ለየለት ግጭት እየገቡ መሆናቸው ሰሞኑን ከሚሰጧቸው አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል። ይህ ደግሞ በእነ አቦይ ስብሃት ቡድን ለተገፋው የአባይ ወልዱ ቡድን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮለታል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በአምባሳደር ትርፉ ኪዳነማሪያም አማካኝነት ጥቃቱን ሰንዝሯል። በመሆኑም የአምባሳደሯ አስተያየት የግሏ ሳይሆን የእነ አባይ ወልዱ ቡድን የጋራ አቋምና ዕቅድ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። በአጠቃላይ በእነ አቦይ ስብሃት እና አባይ ወልዱ ቡድን መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል። በዚህ መሰረት ህወሓት በእነ አቦይ ስብሃት እና አባይ ወልዱ ቡድን ለሁለት መከፈሉ እርግጥ ሆኗል። (ከአምባሳደሯ ጋር የተደረገው ቃለ-ምልልስ በከፊል ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል)