ሕወሓት ይሻገር
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
የሕወሓት አመራር ዶ/ር አብይ አህመድን ከመምረጥ ሂደት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፤ ራሱን በለውጡ ባቡር ላይ ሙሉ በሙሉ መቀላቀል ተስኖት፤ በመጀመሪያ ደረጃ ለራሱ፥ ቀጥሎም ለሀገሪቱ አስቸጋሪ ፈተና እንዳይሆን በሚያስፈራበት ሁኔታ ላይ እያለ መሆኑ ለሁሉም ግልፅ ነው። አስተውሉ፥ የትግራይ ሕዝብ አላልኩም። ደግሞም ሕወሓት አላልኩም። የሕወሓት አመራር ነው ያልኩት።
የሕወሓት አመራር እስካሁን ለሁሉ መፍትሄ የሆነውን የዶ/ር አብይን የማሻገር ዕድል ሊገነዘቡት አልቻሉም። አሁንም ከተኙበት ነቅተው ከሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የለውጥ አራማጆች ለመሆን እንዲቀላቀሉና እንዲሻገሩ ሁላችንም በትዕግስት እየጠበቅናቸው ነው። የሆኖ ሆኖ የሕወሓት አመራሮች፤ ሕወሓትን ለጥፋት እንዳይዳርጉና የትግራይን ሕዝብ ትግል ታሪክ በዜሮ እንዳያስኬዱ፤ የትግራይ ወገኖቻችንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ድምፅ ተሻገሩ የሚል ድምፅ እናሰማቸው።
የሕወሓት አመራሮችም ራሳቸውን ከእልከኝነት አፅድተው፤ ድርጅታቸውን ለወጣት የለውጥ አራማጆች በመልቀቅ፤ የሕዝብን አንድነት እንዲጠብቁ አደራ እንላለን። መፅሀፉ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል እንደሚል፤ ይህንን ለማስተዋል እንዲችሉ ሁላችንም ላሰበንና ሊባርከን ለተነሳው ፈጣሪ በፀሎታችን እናቅርባቸው።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ጉዞ የተለመደው በደም የተለወሰ አብዮት አይደለም። ምናልባትም ለዓለም የመጀመሪያው የሆነና የአምላክ እጅ ያለበት የ “ፍቅር ያሸንፋል” የይቅርታና የመደመር ተዐምራዊ አካሄድ ነው። ታዲያ አሁንም የአምላክ እጅ በምህረት እንደተዘረጋ፤ በይቅርታና በፍቅር ተያይዘን እንድንዘልቅ ሁሉም ወደ ልቡ ይመለስ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፤ ይባርካታልም።
ኢሜል ethioStudy@gmail.com