>

የDeep State (ስውሩ መንግስት) አስከፊ ሴራ እንዳያወድመን!!! (ሀስማ ሀሰን)

የDeep State (ስውሩ መንግስት) አስከፊ ሴራ እንዳያወድመን!!!
ሀስማ ሀሰን
ከ6 አመታት በፊት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተለኮሰው የትግል ችቦ ቀስ በቀስ ወደ ተቀሩት የሀገራችን ሕዝቦች በመስፋፋት በቄሮ፣ በፋኖ፣ በዘርማ እና በሌሎች ትግል አካላት ደምቆ ዛሬ ላይ ላለንበት ደረጃ አድርሶናል፡፡
ይህ ለ6 አመታት የዘለቀው ሠላማዊው ሕዝባዊ ትግል በሕወሓት የበላይነት ሲሾፈር በነበረው በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ የለውጥ አካላትን ወደ ፊት ገፍቶ ማምጣት ችሏል፡፡ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር አብይ አሕመድ፣ አቶ ደመቀ መኮነን፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  እና … መሰል የሕዝብን ፍላጎት ማንፀባረቅ የቻሉ አካላት ጎልተው መውጣታቸው የዚህ ማሳያ ነው፡፡
 በተለይ ሕዝባዊውን ትግል ተከትሎ ዶ/ር አብይ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልተጠበቁ ፈጣን በጎ ለውጦች በመታየታቸው ሕዝብን ‹‹እፎይ›› አሰኝተዋል፡፡ ያልተገመቱ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው እና ከኤርትራ ጋር ያለማንም አሸማጋይነት በቀጥታ የተደረገው የሰላም ውይይት ከታዩት ለውጦች ውስጥ በጉልህ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሚዲያው በኩልም ቢሆን አስደናቂ ለውጦችን በመመልከት ላይ እንገኛለን፡፡ ወትሮም .. ‹‹ሰዓትን ካልሆን እውነትን ተናግሮ አያውቅም›› .. ተብሎ ሲነቀፍ የኖረውና በሕዝብ ዘንድ ጥላቻን ያተረፈው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፍፁም በሆነ መልኩ አክሮባት ሰርቶ በመቀልበስ የውሸት ዐመሉን ትቶ ሀቁን ሲዘግብ መመልከት አግራሞትን ይፈጥራል፡፡ እነዚህና መሰል በጎ ለውጦች ሕዝብን እጅግ ከማስደሰትም ባሻገር የአብዛኛውን ዜጋ ቀልብ በቀላሉ መማረክና መግዛት ችለዋል፡፡
ሆኖም ግን እነዚህ ሕዝባችንን በሐሴት የሞሉ በጎ ጅማሪዎች እየታዩ ባሉበት ወቅት ላይ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች ሕልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ክስተቶች እዚህም እዚያም ሲከሰቱ መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰኔ 16/2010 ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ላስመዘገቧቸው ለውጦች ዕውቅና እና ድጋፍ ለመቸር በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ በተገኘው በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ ላይ የተፈፀመው የቦምብ ጥቃት እና በሀገራችን በሚገኙ አንዳንድ ክልሎች ላይ የተቀሰቀሱት የእርስበእርስ ግጭቶች ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንዲህ አይነት ስውር ደባዎች ሲፈፀሙ ሀገራችን የመጀመሪያዋ አይደለችም፡፡ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መሰል የተንኮል ጥፋቶች ሲፈፀሙ ኖረዋል፡፡ ለእንዲህ አይነት አለመረጋጋት እና የሁከት ፈጠራ ሴራ ቅድሚያ ተሰላፊ የሚሆነው በዚህ ፅሑፍ ርዕስ ላይ እንዳሰፈርኩት Deep State የተባለው አካል እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ Deep State የሚለውን ቃል ወደኛ ስንለውጠው … //ስውር መንግስት፣ ጥልቅ መንግስት፣ ድብቅ መንግስት// … የሚል ትርጓሜ ሊሰጠን ይችላል፡፡
Deep State የሚለው ስያሜ ለዓለማችን የተዋወቀው ከ25 አመታት በፊት በባለፈው ምዕተ አመት እ.ኤ.አ. በ90ዎቹ ላይ በቱርክ ሀገር ነበር፡፡ ቱርክንና በርካታ የዓረብና የሙስሊም ሀገራትን በኸሊፋነት ሲያስተዳድር የነበረው የኦቶመን ተርኪ ኢምፓየር ከ95 አመታት በፊት ከወደቀ በኋላ ‹‹ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ›› ተብሎ በሚጠራው ቱርካዊ ወታደር የተመሰረተችው የዛሬይቷ ቱርክ ከሃይማኖት እንድትገለል ተደርጋ ነበር፡፡ ‹‹ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ›› በሀገሪቱ የነበሩ ኢስላማዊ መገለጫዎችን በስፋት የገፋና የተዋጋ ሲሆን፤ በወቅቱ ቱርካውያን ይፅፉበት የነበረው የዐረብኛ ፊደል በላቲን እንዲቀየር ከማድረጉም ባሻገር የሰላት አዛን ከዐረብኛ ወደ ቱርክኛ እንዲቀየርም አድርጎ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ለ80 አመታት ከዘለቀ ወዲህ ነበር የእነ ኤርዶጋን ፓርቲ እ.ኤ.አ. በ2002 በምርጫ አሸንፎ ሰፊ ማሻሻያዎችን ያደረገው፡፡
በባለፈው ምዕተ አመት እ.ኤ.አ. በ90ዎቹ ላይ በወቅቱ ከበስተጀርባ ሆኖ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረው የቱርክ ጦር፤ በአታቱርክ የተመሰረተችውን ቱርክ .. ‹‹ዓለማዊነቷን አስጠብቃለሁ›› .. የሚል አካሄድ ነበረው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህን ከሃይማኖት ነፃ የመሆነን ዓለማዊነት መርህ አደጋ ላይ ይጥላሉ ያላቸውን አካላት በሙሉ መጋፈጥ ጀመረ፡፡ ከዚያ ቀደም ሲልም ስልጣን የያዙትን ሳይቀር በመፈንቅለ መንግስት ሲያስወግድ ኖሯል፡፡ ጦሩ በሀገሪቷ መሪዎች ትዕዛዝ ስር በመተዳደር ፋንታ እና የሀገሪቱ መሪዎች ለሚቀርፁት ፖለቲካ ተገዥና ታዛዥ መሆን ሲገባው ነገር ግን ከመንግስት ፍቃድ ውጪ በማን አለብኝነት የሚፈፅመው እርምጃ ጦሩን ከመንግስት ስር የተሸሸገ ሌላ መንግስት አደረገው፡፡ ለዚህም ነበር … ‹‹ስውር መንግስት››  //ወይም Deep State// የተባለው፡፡
ይህ Deep State የተሰኘው አጠቃቀም በቱርክ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ሶቪየት ኅብረት ከፈራረሰች በኋላ ሩሲያ ላይም ጥቅም ላይ ውሎ ነበር፡፡ በአሜሪካም እንደዚሁ የሲ.አይ.ኤ ምስረታን እና ዎልእስትሪት ማርኬት መከፈትን ተከትሎ የተፈጠሩ ስውር ፈላጭ ቆራጮችን ለመግለፅ ተጠቅመውበት ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ የዛሬ 7 አመታት ገደማ የአረቡ ፀደይ አብዮት በተቀሰቀሰበት ወቅት በግብፅ የፕ/ት ሑስኒ ሙባረክ ስልጣን መውደቅን ተከትሎ ይህ Deep State የተሰኘው አገላለፅ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል ተመልክተናል፡፡
ከ7 አመት በፊት የቱኒዚያን አብዮት ተከትሎ የግብፅ ሕዝብም እንደዚሁ ፕ/ት ሑስኒ ሙባረክን ከስልጣን ካስወገደ በኋላ በሕዝብ ነፃ ምርጫ ተመርጠው ሥልጣን የያዙት ፕ/ት ዶ/ር ሙሀመድ ሙርሲ የዚህ የDeep State ((ስውር-መንግስት)) ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከሳቸው በፊት በሕዝብ ቁጣ ከስልጣን የተነሱት ፕ/ት ሑስኒ ሙባረክ ስልጣን ከመያዛቸው ቀደም ብሎ የግብፅ አየር ኃይል አዛዥ የነበሩ በመሆናቸው ተጠሪነታቸው ለሕዝቡ ከመሆኑ ይልቅ በጦር ሠራዊቱ በከፍተኛ አመራርነት ደረጃ ላይ ላሉ በዝባዥ ጀነራሎች እንደነበር ይነገራል፡፡  እሳቸውም የዚሁ ግሩፕ አካል የነበሩ በመሆናቸው ከጀነራሎች ጋር በመስማማት ነበር ግብፅን ከ30 አመታት በላይ የመዘበሩት፡፡
በግብፅ ጀነራሎች የሚመራው የሀገሪቱ ጦር ከተወሰነለት ሕገ-መንግስታዊ ድርሻ አፈንግጦ በመውጣት በሚዲያው፣ በኢኮኖሚው፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር እጁን በማስገባት በግብፅ መንግስት ስር የተጠለለ ሌላ መንግስት ለመምሰል በቅቷል፡፡ ከጦር መሳሪያ ጀምሮ እስከ የምግብ ትሪ እና መኮረኒ ድረስ በማምረት የሀገሪቱን 40 ከመቶ የሚሆነውን ኢኮኖሚ ጦሩ ብቻውን እንደሚፈነጭበት እና የግብፅን የግል ዘርፍ በማዳከም ሕዝቡን ችግር ላይ መጣሉ ዘውትር የሚነገር እውነታ ነው፡፡ ታዲያ፤ ይህ በሀገሪቱ ሕያውና ወሳኝ መዋቅሮች ውስጥ ካድሬዎቹን በስፋት የሰገሰገው ጦር ከመንግስት ስር ያለ ሌላ ስውር መንግስት ((Deep State)) በመሆኑ ነበር የሙርሲን መንግስት ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ በቀላሉ መጣል የቻለው፡፡
ከዛሬ 5 አመታት በፊት ዶ/ር ሙሐመድ ሙርሲ በግብፅ ፕሬዝደንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ የግብፅ ሕዝብ አይቶ የማያውቀውን ነፃነት አምቧቡለት፡፡ በፊት በነበረው አገዛዝ ሲሳደዱ የነበሩ አምደኞች፣ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች እንዳሻቸው መፃፍና ሐሳባቸውን መግለፅ ጀመሩ፡፡ ሕዝብ በፈለገው ወቅት እና ባሻው ቦታ ላይ መሰባሰብም ሆነ ሠላማዊ ሰለፍ ማድረግ እንዲችል ተፈቀደለት፡፡ ሆኖም በጦሩ ተፅዕኖ ስር የነበሩት ((የDeep State አካል የሆኑት))  ሚዲያዎች ለጊዜው የሙርሲን እንቅስቃሴ የደገፉ ለመምሰል ቢሞክሩም ሆኖም ግን ወዲያው ተገልብጠው የሙርሲን የለወጥ ጥረት ለማደናቀፍ ግን ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን ፕ/ት ሙርሲ ላይና ፓርቲያቸው ላይ መንዛት ጀመሩ፡፡ ሥውር መንግስት ወይም Deep State ብለን የጠራናቸው በየመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰጉ የጀነራሎቹ ቅጥረኞች ወመኔዎችን በገንዘብ በመግዛት ሁከት የተቀላቀለባቸው ሰልፎችና አመፆች እንዲደረጉ ገፋፉ፡፡ የDeep State አካል የሆኑት ሚዲያዎችም በእሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍን ተያያዙት፡፡ ገንዘብ ተከፍሏቸው ሙርሲን እንዲቃወሙ የተደረጉ ሰልፈኞች /ወመኔዎች/ በወቅቱ የሙርሲ መንግስት ካጎናፀፋቸው ነፃነት የተነሳ የቤተመንግስትን በር እስከማቃጠል ደረሱ፡፡
ይህ Deep State ((ስውሩ መንግስት)) ብለን የጠራነው አካል ሴራውን በዚህ አላበቃም ነበር፡፡ በሚዲያዎች የሐሰት እና የጥላቻ ዘገባዎችን በመስራት ከማቀጣጠል ባለፈ፤ ኤሌክትሪክን በሟቋረጥ የግብፅን ሕዝብ ፈተና ላይ ጣለው፡፡ ((ብዙሃኑ በፎቅ ላይ በሚኖርባቸው የግብፅ ከተሞች ኤሌክትሪክ የለም ማለት በሙቀት መለብለብን ያስከትላል፤ የውሃ አገልግሎት ይቋረጣል፤ የመፀዳጃ ቤቶች እንኳ ውሃ መልቀቅ አይችሉም)) በሀገሪቱ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት እጥረት እንዲኖርም ይህ Deep State ((ስውር መንግስት)) ሌት ተቀን ተጋ፡፡ በሙርሲ ላይ የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በሚኖሩ ወቅትም ይህ Deep State ፖሊሶች ከከተሞች እንዲሰወሩ በማድረግ ሰላም እንዳይከበር እና ሁከት እንዲነግስ አደረገ፡፡ ይህ ስውር መንግስት ((Deep State)) ይህን የሚያደርገው የሙርሲ መንግስት በኢኮኖሚያዊ አገልግሎት አሰጣጥም ሆነ ፀጥታን በማስጠበቅ ረገድ ሀገሪቱን መምራት የተሳነው አድርጎ ለሕዝብ ለማሳየት እና ሕዝቡ መልሶ የሙርሲ አገዛዝ ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ነበር፡፡
እናም በኤሌክትሪክ መቋረጥ፣ በነዳጅ እጥረት፣ ስርዓተ አልበኝነት በመንገሱ  እና … ወዘተ … የበገነው የግብፅ ሕዝብ ጎን ለጎን በሚዲያ የሚነዙት ፀረ-ሙርሲ ፕሮፓጋንዳዎች ብዥታ ፈጠሩበት፡፡ በዚህም የተነሳ ከፊሉ የግብፅ ሕዝብ በስውሩ መንግስት የሚነዙትን ፕሮፓጋንዳዎች ለመቀበል እና ሙርሲን ለመቃወም አላቅማም ነበር፡፡ ሕዝቡ በDeep State አሻጥር የተጋረጡበትን ችግሮች መቋቋም ባለመቻሉ እና ችግሮቹ ከሙባረክ አገዛዝ ዘመን በላይ እየከፉ እንዲመጡ በመደረጉ ምክንያት የDeep State ሚዲያዎች የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነ፡፡ ፕ/ት ሙርሲ ስልጣን ላይ በቆዩበት የአንድ አመት ጊዜ በሙሉ ስውሩ መንግስት ውስጥ ለውስጥ ሴራውን አላቋረጠም ነበር፡፡ ስውሩ መንግስት (Deep State) በውጭም ቢሆን የተወሰኑ አምባገነን ሀገራት ድጋፍም ነበረው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሰሞኑን ሀገራችንን የጎበኘው የኤሚሬትሱ (የአቡዳቢው) አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ዛይድ፤ እስራኤል እና የቀድሞው የሳውዲ ንጉሥ አብደላህ ለአብነት ያህል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ከፊሉ የግብፅ ሕዝብ መልሶ የሙርሲ አገዛዝ ላይ እንዲነሳ በማድረግ እና ከፍተኛ ሕዝባዊ ሰልፍ እንዲደረግ በማመቻቸት ይህን ሽፋን አድርጎ የግብፅ ጦር ፕ/ት ሙርሲ ላይ መፈንቅለመንግስት አካሄደ፡፡ ይህን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ትዕይንተ ሕዝብ ያደርጉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሙርሲ ደጋፊዎች በጠራራ ፀሐይ በምድርና በሄሊኮፕተር በተተኮሱ ጥይቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተረሸኑ፡፡ መፈንቅለ-መንግስቱን የመራው በአሁኑ ወቅት የግብፅ ፕሬዝደንት የሆነው ጀነራል አብዱልፈታሕ አልሲሲ ሲሆን፤ ከ5 አመታት በፊት በፕ/ት ሙርሲ አስተዳደር ዘመን ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትር ነበር፡፡
ወደ ሀገራችን መልሰን ስንመጣ በሀገራችንም ይህ የDeep State ((በሰሞንኛ አጠራር ደግሞ የቀን ጅቦች)) ሴራ እጅግ ያሰጋል፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት 27 አመታት ይህ Deep State ((ስውሩ መንግስት/የቀን ጅብ)) በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ መሰግሰጉ እሙን ነው፡፡ በጦር ሠራዊት፣ በደህንነት፣ በሚዲያ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ፣ በትምህርት ተቋማት እና ወዘተ ይህ Deep State የተሰገሰገ ሲሆን ሌላው ቀርቶ መጅሊስን የመሳሰሉ የሃይማኖት ተቋማትም ቢሆኑ ሃይማኖታዊ ተቋማት መሆናቸው እስኪያጠራጥር ድረስ የDeep State ቀኝ እጅ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ወደ ክፍለከተማ፣ ወረዳ እና ቀበሌ ስንወረድም ይህ ስውር መንግስት በሁሉም ክፍተቶች ውስጥ ተወሽቆ እናገኘዋለን፡፡ አንድ-ለ-አምስት የተሰኘው ጥርነፋ ለዚህ ቀላሉ ማሳያ ነው፡፡
በዚህ መልኩ በስውሩ መንግስት (በDeep State/በቀንጅቦች) የተወረረችው /የተበከለችው/ ውዷ ሀገራችን የወደፊት ሰላሟ አደጋ ላይ እንደማይወድቅ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በእነዚህ የመንግስት እና የሕዝብ ተቋማት ውስጥ በተቻለ አቅም የመለየትና የማጥራት ስራ እስካልተሰራ ድረስ አሁንም አደጋው ፊታችን ላይ እንደተደቀነ ይገኛል፡፡ ሀገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ ከመደናቀፍ ለመታደግና ካሰብንበት ለመድረስ ሜዳውን ከስውሩ መንግስት ((ከቀን ጅቦች)) ማፅዳት ተገቢ ነው፡፡ ሁኔታዎች እየከፉ ከመሄዳቸው በፊት ቅድሚያ ለሚሰጠው መዋቅር ቅድሚያ በመስጠት አፋጣኝ የሆነ የመለየት እና የማጥራት ስራ በሁሉም መዋቅሮች ውስጥ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ መጅሊስን የመሳሰሉ በDeep State ((በቀን ጅቦች)) የተሞሉ በሙስናና በሌብነት የተጨማለቁ ተቋማትም ዳግም መንግስትንና ሕዝብን ለማጋጨት መንስኤ በመሆን ወደ አለመረጋጋት እንድናመራ ሊያደርጉን ስለሚችሉ ጉዳያቸው በአስቸኳይ እልባት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡
Deep State በባሕሪው በዋነኛነት የሚጠቀምበት ስልት መልካም ለውጦች እንዳይታዩ አዲሱን አስተዳደር ማጨናገፍ ነው፡፡ ከላይ ግብፅን በምሳሌነት እንዳየነው ኤሌክትሪክን በተደጋጋሚ በማቋረጥና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ የሆኑ የመንግስት ድርጅቶች ሕዝብን እንዲያጉላሉና እንዲያማርሩ በማድረግ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መቃቃርን ለመፍጠር ይተጋል፡፡ አላቂ ዕቃዎች በቀላሉ ወደ ሕብረተሰቡ እንዳይደርሱ በማድረግ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት እንዲንሰራፋ አሻጥር ይሰራል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ግጭቶችን እና ሁከቶችን በመፍጠር በሀገሪቱ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ከማድረግም አይቦዝንም፡፡ ይህን ሲያደረግ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን አልሞ ነው፡- አንደኛ አዲሱ አስተዳደር ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ ያልቻለ ደካማ አስተዳደር መሆኑን ለማሳየት ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሚፈጠሩትን ሁከቶች ለማብረድ ሲል አዲሱ አስተዳደር በሚወስዳቸው የኃይል እርምጃዎች ምክንያት ቀደም ሲል በሕዝብና በአዲሱ አስተዳደር መካከል የተፈጠሩት መናበቦች እና ፍቅሮች ወደ ኩርፊያ፣ ወደ ጥላቻ እና ወደ ፀብ እንዲያመሩ በማድረግ ሕዝቡ መልሶ ከአዲሱ አስተዳደር ጋር ቁርሾ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ነው፡፡ ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ገና ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በአንዳንድ ክልሎች የታዩትን የብሔር ግጭቶች አቀናባሪው እና ጠንሳሹ ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ በየመንግስት መዋቅሮች ተሰግስጎ የሚገኘው Deep State ((የቀን ጅብ)) መሆኑን ለመረዳት ነብይ መሆን አይጠበቅም፡፡ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ ላይ የደረሰው አሳዛኙ የቦምብ ጥቃትም የዚሁ ሴራ አንዱ መገለጫ ነው፡፡
ከ3 ወራት ገደማ ጀምሮ በክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ በኩል እያየናቸው የሚገኙ እጅግ አበረታችና መልካም እርምጃዎች መላውን ሕዝባችንን ውስጡን በተስፋ ሞልተውታል፡፡ በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱ ዜጋ ለራሱ ደህንነት የሚጨነቀውን ያህል ለጠ/ሚኒስትሩም ደህንነት ዘወትር መጨነቅና ማሰብ ጀምሯል፡፡ እሳቸው ለሕዝብ ፍቅርን እንደቸሩ ሁሉ በአንፃሩ እሳቸውም እጥፍ ድርብ የሆነን ፍቅር ከሕዝብ መቀበል ይዘዋል፡፡ የለውጡ ፋና ወጊ እሳቸው እንደመሆናቸው የሀገራችን መረጋጋት እና ሕልውና እሳቸው ይዘው በመጡት ለውጥ ላይ የተመሰረተ ሆኗል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀን ጅቦቹ እሳቸውን ለማክሸፍ  በክፋት መንፈስ አድብተው እየተጠባበቁ መሆኑ በገሀድ የሚስተዋል ሀቅ ነው፡፡ እሳቸው ላይ እንዳች ነገር ቢከሰት በሀገሪቱ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ በመሆኑም ይህ የለውጥ ጉዞ በሳቸው የመኖርና ያለመኖር ሕልውና ላይ ተመስርቶ እንዳይቀር ክቡር ጠ/ሚ/ሩ ይህን ለውጥ ሊሸከምና ሊያስቀጥል የሚችልን ስርዓት ከላይ ጀምሮ እስከታች ድረስ መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ይህን ማሳካት በጠ/ሚ/ሩ አቅም ብቻ የሚሰራ ሳይሆን የሁላችንንም ርብርብ የሚሻና ከፍተኛ ጥረትን፣ ሰፊ ጊዜን እና ታላቅ ትዕግስትን የሚጠይቅ ቢሆንም በሀገራችን በቋሚነት መረጋጋትን ለማስፈን ግን ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረንም፡፡ ኃላፍትና የሚሰማውን እና የሕዝብን አደራ መሸከም የሚችልን ስርዓት ከላይ እስከ ታች ድረስ መዘርጋት ሲቻል ብቻ ነው የሀገራችንን ሰላምና ዴሞክራሲ በአስተማማኝ ሁኔታ እና በዘላቂነት ማስጠበቅ ምንችለው፡፡
ጤንነትን እና ስኬትን ለጠ/ሚ/ሩ እመኛለሁ!
ውዷ ሀገራችንን ኢትዮጵያን አላህ ይባርካት!
Filed in: Amharic