>

የጠላትን አቅም አሳንሶ ማየት ዋጋ ያስከፍላል!!! (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የጠላትን አቅም አሳንሶ ማየት ዋጋ ያስከፍላል!!!
ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን
* በረከት ስምዖን ጎንደር ምን እየዶለተ እንዳለ ይታወቃል!!
 
* ሳሞራ የኑስ ጋምቤላ መግባቱን ተከትሎ   ለህዝቡ የተደገሰለት እልቂት እንዳለ እሙን ነው!!
 
* የኢንሳው ዳይሬክተር በይፋ ጦርነት አውጇል!!!
 
* የህወሀት የጥፋት ሰዎች ሜዳ ላይ ተለቀው ሀገር ይረጋጋል ማለት ዘበት ነው!!!
 
 የድንቁርናው ወሰን የትየለሌ ነው። ዕውቀት የነጠፈበት፡ ብስለት የራቀው እንደሆነ ባልንጀሮቹ ሳይቀሩ በአደባባይ የሚናገሩት ሀቅ ነው። እንዲህ ዓይነት ከዕውቀት ጋር የተጣላ ሰው ደፋር ለመሆን የመቻል እድሉ ሰፊ ነው። ድንቁርና የወለደው ድፍረቱ ለከት የለውም። ሰማይን በጣቱ ለመንካት ይንጠራራል። ደረቱን ገልብጦ: በከረባት ታንቆ: በመነፅሩ ቂጥ እያየ ሲያወራ እውቀት እንደጭነት በዝቶበት የሚሰቃይ ነው የሚመስለው። አንደበቱ አልተገራም። ከዚያች ሚጢጢ አእምሮው የሚፈልቀውን ግልብ አስተሳሰብ እንዳለ እንደወረደ ለመትፋት የሚከለክል ህሊና የሚባል ትንሹ ፈጣሪ በውስጡ አልተፈጠረበትም። ወይም እንደብዙዎቹ የህወሀት መሪዎች ተከዜን ሲሻገር በእንዶድ ታጥቦ አስወግዶታል።
ታዲያ ስለዚህ ሰውዬ አንድ ታሪክ ይወሳል። በረሃ እያለ ነው አሉ። ስለህወሀት ጠላቶች ትንታኔ መስጠቱ ነው። ህወሀት ሶስት ጠላቶች አሏት አለ። አንደኛው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊስት፡ ሁለተኛው የአማራ ትምክህት ሃይል፡ ሶስተኛው ደግሞ ወ/ሮ ብሪቱ ናቸው አለና አረፈው። ወ/ሮ ብሪቱ የሰውዬው እንጀራ እናት ነበሩ። ክፉ ናቸው:: በዚህ ክፋታቸው ሰፈር መንደሩ የሚጠቋቆምባቸው ናቸው:: ሰውዬውን ልጅ እያለ ያሰቃዩት ነበር አሉ:: እናም ወ/ሮ ብሪቱ ሶስተኛዋ የህወሀት ጠላት ሆነው በሰውዬው ዘንድ ተጠቀሱ። በ1997 ዓም በአጋዚ ጦር ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉ ጊዜ ”ለምንስ ወታደሮቹ ወደ ሰማይ አይተኩሱም?” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ”ዋይ! በሰማይ ምን ሰው አለ?” በማለት ምላሽ መስጠቱን ከውስጥ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ድንቁርና ለከት ሲያጣ ከዚህም በላይ ያደርጋል።
ሰውዬው በ40 ዓመቱ አንደኛ ክፍል እንደገባ ይነገራል። በሁለት ዓመት ውስጥ 12ኛ ክፍል ጨርሶ ለዩኒቨርስቲ እንደበቃም ይታወቃል። አሁን ዶክተር የሚል ማዕረግ ተሸክሟል። ስሙን በእንግሊዘኛ አስተካክሎ ለመጻፍ ዳገት የሚሆንበት ሰው ነው እንግዲህ ሶስተኛውን ዲግሪ ሰርቷል ተብሎ ዶክተር የምትል ማንጠልጠያ ከስሙ በፊት የተደነቀረለት። በእርግጥ የጫነው ስም ከብዶታል። የጭነቱ ብዛት የማሰብ አቅሙን ዝቅ ሲያደርገው ይታያል:: ለነገሩ የብዙዎቹ የህወሀት መሪዎች መገለጫቸው ይሄው ነው:: በስተርጅና ጥይት እየቆጠሩ የሂሳብ መደመርና መቀነስ ከመማር ውጭ ከእውቀት ጋር የተጣሉ፡ ሀገርን በጨበጣ ለመምራት በድፍረት ቤተመንግስት የገቡ በዚህም ባለፉት 27 ዓመታት መቀመቅ ከተውን ለአሁኑ ሀገራዊ አደጋ ያበቁን የትውልድ እርግማን ናቸው።
ሰውዬው ከፍተኛውን የደህንነት መስሪያ ቤት በዳይሬክተርነት መርቷል። የብሄራዊ ደህንነት መረብ ኤጀንሲ በሚባል መስሪያ ቤት ፈላጭ ቆራጭ ነበር። በውትድርናው የሜጄር ጄነራልነትን ማዕረግ አግኝቷል። በትምህርቱ የዶክተሬት ደረጃ መድረሱ ያስደነግጣል። የግዢ ማዕረግ በቀላሉ የትም ስለሚገኝ ላያስገርም ይችል ይሆናል። ” ሜጄር ጄነራል ዶክተር ተክለብርሃን ወልደአረጋይ”
የጭንቅላቱ አድማስ ከትግራይ አልተሻገረም። ኢትዮጵያን በጠባቡ የትግራይ መነጽር የሚመልከት መሆኑን በአደባባይ ለመናገር ቅንጣት ታክል አያፍርም። አይፈራም። ”የኢትዮጵያ” የሚል ስም በያዘው የመረጃና መረብ ኤጀንሲ ውስጥ ዳይሬክተር ሆኖ ስለትግራይ ብቻ የሚጨነቅ፡ ስለትግራይ ብቻ የሚሰራ መሆኑን ከዚህ ቀደም በሰጠው ቃለመጠይቅ ገልጿል፡-
ትግራይን እንዴት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እናበለጽጋታለን፡ 
ትግራይ በኢኮኖሚ ተፈላጊ እንድትሆን ምን ማድረግ አለብን፡ 
ትግራይ የቴክኖሎጂ መሪ እንድትሆን ምን ልናደርግ እንችላለን፡ 
ትግራይ…ትግራይ….ትግራይ….ብቻ ነበር ወሬው።
ይህን ቃለመጠይቅ ሲሰጥ የትግራይ የአንድ ቢሮ ሃላፊ ሆኖ አልነበረም። ወይም መቀሌ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር በሚል ስልጣንም አልነበረም። የኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት መረብ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄነራል ሆኖ እንጂ። መንደርተኝነት የተጣባው፡ በአካል እንጂ በአስተሳሰብ ተከዜን መሻገር ያቃተው ግለሰብ ነው ሰውዬው።
ሰሞኑን የሰጠው ማራቶን ቃለመጠይቅ መነጋገሪያ ሆኗል። ብዙ ብሏል። እነስዩም መስፍን ከፎከሩት፡ ሳሞራ ካቅራራው፡ አንዳንድ የአረና ሰዎች ያዙኝ ልቀቁኝ ካሉት ይልቅ የዚህ ሰው ማስፈራሪያ ከረር ያለ ነው። በፓርቲ ውስጥ ስልጣን እንደሌለው፡ አባልም እንዳልሆነ ይናገራል። በዶ/ር አብይ ላይ የግል ቂም እንደሌለው ይናገርና፡ ጠላት ብሎ ይፈርጃቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማጣጣል የሄደበት ርቀት በእግር ቢጓዙት አዝለፍልፎ የሚጥል ነው። ”ህዝብ” ለሰውዬው ማን እንደሆነ ግራ እስኪገባ ድረስ ዶ/ር አብይን የህዝብ ጠላት አድርጎ ይፈርጅና እንዋጋቸዋለን ብሎ ይደነፋል። የኢንሳ ሃላፊ በነበረ ጊዜ በስራ አጋጣሚ ያገኛቸውን የስራ ሚስጢሮች በየመድረኩ መዘርገፉ ዲሲፕሊን የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። FBIን የሚበልጥ የምርመራ ተቋም ገንብተናል ብሎ ያለቅጥ ሲንጠራራ መስማት ጆሮን ያሳምማል። በእርግጥ ለሰውዬው ረዥም ዲስኩር ምላሽ መስጠት እንደሰውዬው መውረድ ስለሚሆን መተው ይመረጣል። ነገር ግን በአንድ ጉዳይ የተናገርውን ማለፍ አልቻልኩም። ስለዶ/ር አብይ።
ሰውዬው እንደሚለው ዶ/ር አብይ ከሱ በታች ያለ የሬዲዮ ኦፕሬተር ነው። ከስራ ያሰናበተው እሱ መሆኑን በገደምዳሜ ይናገርና ምክንያቱን ሲገልጽ “እንደ አስተሳሰብ ባህሪይ መጠን የአብይ አስተሳሰብና ባህሪይ ለተቋማችን ሥራዎች የሚጎዳ ስለነበር ከኛ ጋር መቀጠል አልቻለም። ከሥራ ውጣ አልነው ። ወጣ። ከወጣ በኋላ ድርጅቱ ምንም ዓይነት ሥጋት የለውም ማለት ነው። ከድርጅቱ ጋር ፍቺ ፈፀመ ማለት ነው። ስለዚህ ችግሩ የግል ችግር ሳይሆን አብይ ከድርጅታችን ተልዕኮ ጋር የማይጣጣም ባህሪይ ስለነበረው ነው።”
እንግዲህ ዶ/ር አብይ ለረጅም ጊዜ በትግል ውስጥ እንደነበሩ ሰውዬው ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው። የዶ/ር አብይ ተራማጅ አስተሳሰብ፡ በህወሀት ጥብቆ ያልተቀፈደደ አመለካከት የነበረው ከቀድሞ ጀምሮ ለመሆኑ በአስረጂነት የሚቀርብ ነው። ሰውዬው ዋጋ ለማሳጣት የሄደበት መንገድ ለዶ/ር አብይ ተጨማሪ ነጥብ እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። ውስጣዊ ትግሉ ትላንት የተጀመረ፡ ሳይሆን የቆየና የከረመ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። ከዚህ ያለፈ የሰውዬው ዲስኩር ተራ ቀረርቶ ነው። ህወሀት አፈር ልሶ ይነሳ ዘንድ ከመናፈቅ በቀር ገለባ ነው። ህወሀት ከእንግዲህ አራት ኪሎ ቤተመንግስት የመግባቱ ነገር አክትሞለታል። የጥፋት ሃይል ሆኖ በየቦታው እሳት የማቀጣጠል አቅሙ ግን አሁንም ጠንካራ ነው። ይህ ሰው የሚፈራገጠው በሞተ ባለቀለት ጉዳይ ነው። አቅምን ያለማወቅ በሽታ በእርግጥ ብዙዎቹን የህወሀት ሰዎች ያጠቃቸዋል።
ዶ/ር አብይ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ይጠበቃል። ህወሀት በተአምር የሚለወጥ አይደለም። ተሰብባሮ፡ አክርካሪው ተመቶ፡ እስከወዲያኛው መወገድ ያለበት ድርጅት ነው። ዶ/ር አብይ ህወሀትን ማጥፋት ባይችሉ እንኳን በየአቅጣጫው የተለቀቀውን የህወሀት ጂኒ ወደ ጠርሙሱ የማስገባት ውሳኔ ጊዜ ሊሰጡበት አይገባም። ለሀገር ደህንነት ሲባል ከፍቅር በመለስ ቅጣት ያስፈልጋል። ፈጣሪም የፍቅር አምላክ ብቻ አይደለም። ይቀጣል። የህወሀት የጥፋት ሰዎች ሜዳ ላይ ተለቀው ሀገር ይረጋጋል ማለት ዘበት ነው።
በረከት ስምዖን ጎንደር ምን እየዶለተ እንዳለ ይታወቃል። ሳሞራ የኑስ ጋምቤላ መግባቱም በስፋት ይወራል። ለጋምቤላ የተደገሰ ነገር ሊኖር ይችላል። በድምጸ ወያኔ ላይ እየደነፋ ያለው የኢንሳው የቀድሞ ዳይሬክተር በይፋ ጦርነት አውጇል። እነዚህ ሰዎች ሜዳውም ፈረሱም ተለቆላቸው ኢትዮጵያ ትረጋጋለች ማለት ቀልድ ነው። ስለሀገር ሲባል መረር ያለ ውሳኔ ከዶ/ር አብይ ይጠበቃል። ጂኒውን ወደ ጠርሙሱ ያስገቡ። ህወሀት ሰው ከማይደርስበት ቦታ ርቆ እንዲቀመጥ ማድረግ የወቅቱ ወሳኝ እርምጃ ነው። እየዶለቱ ያሉ የህወሀት ሰዎች መታሰር አለባችው። ይህን በማድረግ የሚከፈል ዋጋ ካለ ከህዝቡ ጋር ሆኖ መክፈል እንደሚቻል ዶ/ር አብይ ሊረዱት ይገባል። ከሚያደርሱት ጥፋት አንጻር የሚከፈለው ዋጋ ኢምንት እንደሚሆን አልጠራጠርም። እናም ዶ/ር አብይ ይፍጠኑ!
Filed in: Amharic