>

የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ከጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝቶ ተወያየ!

አብዱል ከሪም መሀመድ
የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ከጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝቶ ተወያየ!
 
* በከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ የመጅሊሱ አመራር አባላት በተገኙበት ውይይቱ ቀጥሏል!
 
* ምርጫ መደረግ እንዳለበት ውሳኔ ላይ ተደርሷል!
 
* ከኮሚቴው ሦስት ሰዎችን ጨምሮ 9 አባላት ያሉት ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሟል!
 
* ኮሚቴው ምርጫውን አስመልክቶ አስፈላጊውን ጥናት አድርጎ መፍትሔዎችን ያቀርባል!
በዛሬው እለት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በቀረበለት አስቸኳይ ጥሪ መሠረት በቤተመንግስት ተገኝቶ ሰፊ ውይይት አደረገ፡፡ 15 የኮሚቴው አባላት በተገኙበት በዚህ ስብሰባ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ኮሚቴው የህዝበ ሙስሊሙን ችግሮች አስመልክቶ ጥያቄዎቹን ያቀረበ ሲሆን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም በችግሮቹ ዙሪያ በሰፊው ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ የከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ የመጅሊሱ አመራር አባላት ውይይቱን እንዲቀላቀሉ የተደረገ ሲሆን ከሰፊ ውይይት በኋላ መጅሊሱ ሕዝበ ሙስሊሙን በተገቢው መልኩ የሚወክል መሪ ተቋም መሆን እንዳለበት እና ለዚህም ምርጫ መደረጉ አስፈላጊ እንደሆነ አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ምርጫውን ለማመቻቸትም ገለልተኛ አካል መቋቋም እንዳለበት በተያያዥነት ተወስኗል፡፡
በዚሁ መሠረት ከሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ 3 ሰው (ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ የታሪክ ምሑር አሕመዲን ጀበል እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ)፣ ከመጅሊስ 3 ሰው (ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር፣ የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሐጂ ሙሐመድ አሚን እና ሐጂ ከድር)፣ ከምሑራን እና ሽማግሌዎች ደግሞ 3 ሰው (ዶ/ር ኢድሪስ ሙሐመድ፣ ዶ/ር ሙሐመድ ሀቢብ እና ሸኽ ሙሐመድ ጀማል አጎናፍር) በገለልተኛ ኮሚቴነት ተመርጠዋል፡፡
ዘጠኙ አባላት የተካተቱበት ይኸው ኮሚቴ የተቋሙ ችግሮች የሚፈቱበትን እና ምርጫው በተሳካ ሁኔታ የሚካሄድበትን መንገድ በዝርዝር አጥንቶ ለመንግስት የሚያቀርብ ሲሆን መንግስትም ችግሮቹን ለመፍታት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ፣ ለገለልተኛ ኮሚቴው ሙሉ እውቅና እንደሚሰጥ እና ኮሚቴውን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ግላዊም ሆኑ መንግስታዊ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤትና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መሀከል ላለው አለመግባባት ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት የተቋቋመ የጋራ ኮሚቴ ተመስርቶ እርቅ መውረዱን አስመልክቶ የተሰጠ የውይይቱ ሙሉ መግለጫ

 

 

Filed in: Amharic