>

"ገራፊዬ ዳኛ ሆኖ መጣ በሱ አልዳኝም በማለቴ  9 ወር ቀጡኝ።"  (አበበ ካሴ)

“ገራፊዬ ዳኛ ሆኖ መጣ በሱ አልዳኝም በማለቴ  9 ወር ቀጡኝ።”
አበበ ካሴ 
የአማራ ቴሊቪዥን ያቀረበውን ሁለተኛውን ክፍል ዛሬም ተመለከትኩት ። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በሂትለር ጄስታፖወች ከኦሽዊትዝ ካምፕ ተርፈው  ቃለምልልስ የሰጡ አይሁዳውያንን ዶኪመንተሪ ከዩቲዩብ አውርጄ የምመለከት ነው የመሰለኝ ።
የትናንቱ ሁለተኛው ክፍል እንደ መጀመሪያው ክፍል ብዙ ግፎች የተሰሙበት መሆኑ ያመሳስለዋል ። ነገር ግን ክፍል ሁለት ከክፍል 1 የሚለይበት አንድ ነገር አለ ።
በዚህ በሁለተኛው ክፍል   ከመጀመሪያ ክፍል የበለጠ  የአቢይ አህመድን መንግስት የዳኝነት ክንፍ የደረመሰ አንድ መብረቅ የሆነ እውነታ ተጋልጧል።
የኢፌድሪ ህገመንግስት የዚህ መንግስት ፒለር ከሚላቸው  3 ምሰሶዎች ማለትም ከስራ አስፈፃሚውና ፣ ከህግ አውጭው በተጨማሪ 3ኛው የመንግስት አካል የሆነው Judicary ው(የዳኝነቱ አካል) በታሪክ ተሰምቶም ታይቶም  በማይታወቅ  ሁኔታ መበስበሱ የተረጋገጠበት ቃለምልልስ ነበር። ይሄ የዳኝነት አካል መታደስ ሳይሆን ፈርሶ መሰራት እንዳለበት ያረጋገጠ ቃለምልልስ ነበር።
በዚህ ፕሮግራም ሰቆቃ ከተፈፀመባቸው አንዱ የሆነው  አበበ ካሴ እንደ መብረቅ የሚያስደነግጠውን እውነታ እንደሚከተለው አፈረጠው:
“ሬንጄር ለብሶ ማዕከላዊ ላይ ሲገርፈኝ የነበረ ሰው ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ ካባ ለብሶ ጠበቀኝ። ሊዳኘኝ እንደማይችል ስናገር ችሎት በማደናቀፍ በሚል 9 ወር ቀጡኝ።” ይላል።
ይሄ እጅግ አሳፋሪ ተግባር በአለምም ላይ ተሰምቶም የማያውቅ አገራችን ላይ የተፈጠረ እውነታ ነው።
ለዚህ አሳፋሪ ተግባር ጠቅላይ ሚ/ር አቢይ አህመድ ከመተንፈሳቸው በፊት   የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ዳኜ ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው።
እንደሚታወሰው ከዚህ በፊትም አንድ እስረኛ ፍርድቤት ችሎት ፊት በመቅረብ
 << የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ አቶ መለስ አለም ማታ ማታ እየመጣ ይገርፈኛል” ማለቱ አይዘነጋም።  በነገራችን ላይ ይሄ ጉዳይ ፈፅሞ መዘንጋት የለበትም።
መቼም ዶ/ር አቢይ አህመድ ይሄን ጉድ ባይሰማው ነው እንጅ ይሄን የመአከላዊ ገራፊ ቃለአቀባይ አድርጎ  በየሄደበት እየተከተለ መግለጫ እንድሰጥ አያደርገውም። አሁንም ለጠ/ሚ አቢይ አህመድ የምመክረው የቃል አቀባዩን የአቶ መለስ አለምን ጉድ Human Right Watch በአመታዊ መግለጫው አውጥቶ ለአለም ከማሳወቁ በፊት ከስራው እንድያግደው እጠይቃለሁኝ ። ምክንያቱም የጠ/ሚሩ ቃለአቀባይ የቶርቼር ስፔሻሊስት ነው ተብሎ በአንድ የውጭ ጋዜጣ ከወጣበት ሊጠግነው የማይችል የስም ማጠልሸት ሊደርስበት ይችላል።
በመጨረሻ አንድ ቁምነገር ተናግሬ ላብቃ ። በየትኛውም የነፃነትና የደሞክረሲ ትግል ውስጥ ከባዱ ነገር ጭንቅላትን አንጎልን ነፃ ማውጣት ነው እንጅ መሬትና ህዝብን ነፃ ማውጣት አይደለም። አለምን የቀየረው የፈረንሳይ አቢዮት ከመፈንዳቱ በፊት የፈረንሳይ ፈላስፎች እነ ሩሶ የህዝቡን አንጎል ነፃ ለማውጣት ብዙ ሺህ ኩባያ የብእር ቀለምና  በ10ሺዎች የሚቆጠሩ  ወረቀቶች ፈጅቶባቸዋል። የአማራ ቴሌቪዥን በዚህ ጠቃሚ ፕሮግራሙ  በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ጭንቅላቶችን ስለወያኔ ትግሬ ከነበራቸው  የተንሻፈፈ አመለካከት ነፃ አውጥቷቸዋል እኛንም እነሱን ለማስረዳት የምንጨርሰውን መቅኒያችንን ለሌላ ተግባር እንድናውለው አድርጎናልና ክብርና ምስጋና ለአማራ ቴሌቪዥን ይሁንልኝ ። ከአዘጋጁ ጀምሮ ለኤዲተሩ ለካሜራ ባለሙያውና ለሁሉም ጋዜጠኞች ምስጋናየ ላቅ ያለ ነው።

https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=738506659657664&id=118697174971952

Filed in: Amharic