>
5:18 pm - Sunday June 15, 2155

አማራ-ጠል ደዌ የህወሃት ብቻ ህመም አይደለም!!!! (መስከረም አበራ)

አማራ-ጠል ደዌ የህወሃት ብቻ ህመም አይደለም!!!!
መስከረም አበራ
ዛሬ እግሯ ገደል የገባው ህወሃት ከተፈጠረች ጀምሮ በተቆራኛት አማራ-ጠል ደዌ ስትሰቃይ የኖረች ንኡስ ፍጡር ነች፡፡ይህ በሽታ ግን ህወሃትን ብቻ የሚያሰቃይ አይደለም፡፡ይልቅስ ፈውስ በሌለው የዘረኝነት ልክፍት የተለከፉ ፖለቲከኞችን ሁሉ የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ የሞት አፋፍ ላይ ያለችውን ህወሃት ከሞት ሊመመልሳት ባይችል እንኳን በጣር የመፈራገጧ ጊዜ እንዲረዝም የሚያስችሏትም የእነዚሁ የበሽታ ተጋሪቿ እርዳታ ይመስለኛል፡፡
የአማራ ጥላቻ በብዙ መንገድ ይገለፃል፡፡ ለምሳሌ የህወሃት ባስልጣናት  እና የአረና አክቲቪስቶች የወንዛቸው ልጆች መሳሪያ ተደግፈው ከተቀመጡበት ወንበር  በአፍጢማቸው የደፋቸው የኦቦ ለማ እና የጠ/ሚ/ር አብይ ኦህዴድ ሆኖ ሳለ አምርረው እየወቀሱ ያሉት በስንት ግፊያ መላወስ የጀመረውን አማራውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን እና “አለ ሞቷል?” እያልን ስንወራረድበት የኖርነውን ፓርቲያቸውን ብአዴንን ነው፡፡ የኢንሳው ሰውየ እንደውም “የኦህዴድ እና የኦሮሞዎች ችግር ስስ ነው የብአዴን እና የአማሮች ችግር ነው የደደረው” ብለው መቃብር ብቻ የሚለየውን አማራን ሁልጊዜ የመጥላት በሽታቸውን አስመሰከሩ፡፡
 “ስለፃፍኩት ተፀፀትኩ” ላሉት ህገ-መንግስት ጠበቃ መሆን ….
ይህ በሽታ የህወሃቶች እና ትግሬ አክቲቪስቶች ብቻ ስላልሆነ ባለፈው ሳምንት ዶ/ር አወል ቃሲም (ምክንያታዊ ይመስለኝ ነበር) በሃገሩ ላይ ከተደረገው ሰልፍ ሁሉ የባህርዳሩ ሰልፍ ላይ ተይዞ የተወጣው ባንዲራ የአሮጌውን አብሮነት ምልክት አየሁበት ብሎ ተብሰለሰለ፡፡ አዛውንቱ ዶ/ር ነጋሶ ደግሞ ዛሬ የሆነ መፅሄት ላይ ቀርበው ባደረጉት ቃለ ምልልስ የባህር ዳሩ ሰልፍ የለየለት የህገ-መንግስት ጥሰት ነው ሲሉ “ስለፃፍኩት ተፀፀትኩ” ላሉት ህገ-መንግስት ጠበቃ ሆነው ብቅ አሉ፡፡ በዚህ ቃለ ምልልስ ከዶ/ር ነጋሶ ጋር የተገናኘው ሰውየ ጋዜጠኛ መሆኑን እጠራጠራለሁ! ዶ/ር ነጋሶን ያገኛቸው የእውነት ጋዜጠኛ ቢሆን ኖሮ ስንት ነገር ማንሳት ይቻል ነበር፤ ምን ያደርጋል!
ለማንኛውም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ይህን ሲናገሩ የሚንጣቸው የህግ ማስከበር ነገር ሳይሆን ውስጣቸው የከተመው ከወደ አማራ ክልል የሚመጣን ነገር ሁሉ በጥርጣሬ፣በጥላቻ የማየት እና የማሳጣት አባዜ ነው! ይህን ያስባለኝን ምክንያቴን ላስረዳ …
1. ልሙጡ ባንዲራ የታየው ባህርዳር ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎች ከተሞች ባንዲራው መያዙን በተመለከተ ተጠይቀው ነጋሶ የመለሱት መልስ ነው የልብ የኩላሊታቸውን የሚያሳብቀው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ  የአዲስ አበባውን ሰልፍ የባህርዳሩን ሰልፍ በወቀሱበት ህገ-መንግስትን የመጣስ በደል የማይወቅሱበትን ምክንያት ሲናገሩ ‘በአዲስ አበባው ሰልፍ ከልሙጡ ባንዲራ በተጨማሪ ሌሎች ባንዲራዎችም ተይዘው ነበር በባህርዳር ግን የክልሉን ባንዲራ እንኳን አላየንም ሁሉም ሰው የያዘው ልሙጡን ባንዲራ በመሆኑ ህገ-መንግስታዊ አይደለም’ ይላሉ፡፡ በሌላ አባባል ከልሙጡ ባንዲራ ጋር  ሌሎች ባንዲራዎችን መያዝ ህገ-መንግስታዊ ሲሆን በወጥነት ልሙጡን ባንዲራ መያዙ ግን ህገመንግስታዊ አይደለም፡፡ በዶ/ር ነጋሶ ፍርድቤት ላለመከሰስ የባህርዳር ሰው ከአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራ በተጨማሪ የተለያዩ ጨርቃ ጨርቆችን ይዞ መውጣት አለበት ማለት ነው፡፡
2. የዶ/ር ነጋሶ ህገ-መንግስት የሚፈቅደው ባንዲራ ባለኮከቡን ሲሆን ከባህርዳሩ ሰልፍ በኋላ በዶ/ር ነጋሶ  የትውልድ መንደር (ነቀምት) የተውለበለበው ባንዲራ ይታወቃል፡፡ ይህ ለዶ/ር ነጋሶ ችግር የለውም፡፡ ለምን ቢባል ባህርዳር ላይ በአማሮች አልተደረገማ! በተመሳሳይ ቦንጋ ላይ የአንበሳው ምልክት ያለው ባንዲራ ተይዟል ይሄም ችግር አይደለም፡፡ ምነው ቢባል አማራ ያላደረገው ነገር ህገ-መንግስታዊም ሆነ አልሆነ ችግር የለውም፡፡
3. በመጨረሻም ባለ ኮከቡ ባንዲራም ሆነ ዶ/ር ነጋሶ በአዛውንት ጉልበታቸው ዘብ ቆሜ ልደርለት የሚሉት ህገ-መንግስት የአማራን ህዝብ አይወክልም፡፡ አለቀ !!!!
Filed in: Amharic