አሰፋ ሀይሉ
ገና ብዙ እንደምናይ፣ ገና ብዙ ርቀት አብረን እንደምንዘልቅ፣ ገና በፍቅራችን ሀገር ምድሩን እንደምናዳርስ አጥብቀን እናምናለን! “ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ፀብ ካወራን ተሣስተናል… የመጣነው መንገድ ያሣዝናል!”፡፡ አሁን የፀብን መንገድ ትተን… የፍቅርን መንገድ ጀመርን፡፡
ኤርትራ በኢትዮጵያ ልብ ውስጥ አለች፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ ልብ ውስጥ አለች፡፡ ያንድ እናት ልጆች… ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን.. በፍቅር እና በፍቅር ኃይል ብቻ… ዳግም ይዋሀዳሉ! ገና ብዙ እናያለን! የሚሆነው ነገር ከሆነው እጅጉን ይበልጣል! የሁለታችንን ወዳጅነት የሚጠራጠሩ.. የሚፈሩትን ሁሉ.. ገና በተባበረ የፍቅር ኃይል እንደምራቸዋለን!!!! ወንድማማች ሀበሾችን.. ከተጠፋፉበት የፍራቻና ሥጋት ምድረ በዳ አውጥቶ.. ዳግም በፍቅር የሚያገናኝ የፍቅር አምላክ.. ስለ ድንቅ ሥራው.. የተመሰገነ ይሁን!
አምላክ መላውን የሀበሾች ህዝቦች ሁሉ – ከትውልድ እስከ ትውልድ – አብዝቶ፣ አብዝቶ ይባርክ፡፡ ዘወትር የምንጠራው… የሁለት ፈሪሀ-እግዜር ያላቸው ጀግና ሕዝቦች አምላክ… አንድዬ ፈጣሪ… የተመሰገነ ይሁን!! እምዬ ኢትዮጵያ – በልጆቿ ፍቅር፣ ፅናት፣ ሠላም፣ ኅብር ደምቃ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡
አዲሱን የፍቅር ምዕራፍ በታላቅ የፍቅር እርምጃ ለመጪው ትውልድ ከፍተው… ሕዝባቸውን ወደማያባራ የፍቅርና የብልፅግና ሙላት ለማድረስ ታላቁን የፍቅር እርምጃ… በታላቅ ቆራጥነት ላሣዩን… ለሁለቱ ምርጥ ልባም የሀበሻ ልጆች… ፍቅርን በመካከላችን ለማምጣት ላልፈሩት፣ ላልሰጉት፣ ወደኋላም ዝንፍ ላላሉት…. የፍቅርን አሸናፊነት በተግባር ሊያሣዩን ልባቸውን ላጀገኑት… ለሁለቱ የፍቅር ጀግኖች…. ለውድ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለውድ ፕሬዚደንት ኢሣያስ አፈወርቂ…ምስጋናችን ወደር የለውም!
ለውድ አብይ አህመድ እና ለውድ ኢሣያስ አፈወርቂ…“ፍቅረይ ተለመነይ.. ፍቅረይ ተለመኒ… ብሠንሠለት ፍቅሪ ታሠርኩኒ…!” የሚለውን የተክሌ ተስፋዝጊን ቆየት ያለ ዘፈን… እና… የቴዲ አፍሮን “ፊዮሪና… ጋራው ቢከልለን ያ ተራራ…፤. አትወጪም ከሐሳቤ ጓል አስመራ”…. የሚለውን በፍቅር ከተነካ ልብ… ሁለቱን ጥዑመ ዜማዎች ጮክ ብዬ እያዜምኩ – እና – በተራ በተራ ባሉበት በአስመራ ከተማ.. ዛፉን ተራራውን.. ወንዙን በረሃውን አቋርጦ ይደርሣቸው ዘንድ ከልብ እየተመኘሁ – እና – እንዲህ በፍቅር ስሜት ቅልልልጥ ማለቴ እያስታወቀብኝ – በአክብሮት ተሰናብቼ – ተለየሁ፡፡
ፍ ቅ ር ያ ሸ ን ፋ ል ! መልካም ዕለተ ሰንበት፡፡️