>
5:26 pm - Sunday September 17, 6705

ከሚከተሉት መካከል ለምን ተከተሉ? ጎዳናው!!! (ታምሩ ተመስገን)

ከሚከተሉት መካከል ለምን ተከተሉ? ጎዳናው!!!
ታምሩ ተመስገን
…… ሜክሲኮ ሸበሌ አካባቢ ጫማየን እያስጠረኩ ነው፡፡ ኑሮ ሳይፎርሽ እንደቀለደባቸው ፊታቸው የሚናገር አንድ አልፎሂያጅ ሽማግሌ ቤንዚን የፈሰሰበት አቧራማ መንገድ የመሰለ እግራቸውን እየጎተቱ መጡና “የብር ላስቲክ ይኖርሃል?” በሰለለ ድምፅ ጫማ ጠራጊውን ጠየቁት
ዞር ብሎ ገመገማቸውና “ብር ሳይኖርዎት ላስቲኩን ምን ሊያደርጉት ነው?” ጠየቃቸው፡፡
“ግዴለህም ከድፍድፉ ላይ ድርሻየ ሲሰጠኝ አስርበታለሁ፡፡”
“እንደሱ ከሆነማ ለምን ያኔ አይገዙም?”
“የኛን ሀገር ነጋዴ ማን ያምናል የኔ ልጅ፡፡  አንዲት ነገር ኮሽ ባለች ቁጥር ዋጋ ከመጨመር የማይሰስተውን የኛን ሀገር ነጋዴ ማን ያምነዋል!  እንግዲህ ነገ ጠቅላያችን ነዳጁን ሸጠው የየድርሻችንን ሲሰጡን ደግሞ የብር መቋጠሪያው ላስቲኩን እንደማያስወደዱብን ዋስትና የለንም፡፡”
“እሺ ስንት ልስጥዎት?”
“በርግጥ እሳታሁን ድፍድፍ ማውጣት መጀመራቸውን እንጅ ተሸጦ ስንት ስንት እንደሚደርሰን አልነገሩንም፡፡ እንግዲህ ጠቅላያችን በየቀኑ በሰርፕራይዝ ሲጥ አድርገው ካልገደሉን…  ለማንኛውም የአምስት ብር በርከት አድርገህ ስጠኝ” አሉትና አብዝታ ከመተሻሸቷ የተነሳ 1 እና 0 ቦታ የተቀያየሩባት 10 ብር አቀበሉት፡፡
“አባት መልስ የለኝም” የአምስት ብር ላስቲኮች እያቀበላቸው
“ግዴለም ጫማየን አስጠርግበታለሁ፡፡” አሉና ከጎኔ ተቀመጡ
“ግሽጣ ….ግሽጣ ግሽጣ ጣፋጭ ግሽጣ በ25 ብር” የሚል ወጣት ነጋዴ አንዳች ፍራፍሬ በባሬላ እየገፋ ሲያልፍ አየሁና
ምንድን ነው ያለው? ጠየኳቸው ሽማግሌውን
“ግሽጣ ነው የሚለው፡፡ ግሽጣ፡፡ ሆሆ ጉድ ነው መቼም ዘንድሮ…. ያኔ ጀሶና ሰጋቱራ አብልተውን ፍሬምና ችፑድ ሲያስቀምጠን ሰነበተ፡፡ ይሄው ጊዜ ደጉ አሁን ደግሞ ስድብ ያበሉን ጀመር፡፡ ግሽጣ ብሎ ምግብ ይታይህ እንግዲህ፡፡ አቤት የዚህ ህዝብ ጫንቃ የቻለው ጉድ…” ፈጣሪን ፍለጋ ይመስል ወደ ሰማይ አንጋጠጡ
አሁንማ ፀሀይ እየወጣለት ነው  እኮ አባባ…
“የምን ፀሀይ….?”
ለሽማግሌው መልስ ሳልሰጣቸው በፊት 2 ፖሊሶች በንፋስ ድጋፍ የሚፈረጥጥን አንድ ከሳዋ ወጣት ሲያሯሩጡ መጡ፡፡ ትኩረቴ ተመነተፈ፡፡ ክስተቱን የተመለከቱ ሌሎች ከፖሊሶቹ ኋላ ግር ብለው ይሮጡ ጀመር፡፡ ፖሊሶቹ ማሯሯጡ አልሳካ ሲላቸው ጊዜ ዘለው እግሩን ነከሱት፡፡
ወጣቱ “ኧረ እግሬን በሉኝ” ብሎ ወደቀ፡፡
 ሰው ለጉድ ተሰበሰበ፡፡ ዘግይተው የመጡት ደግሞ ስኳርና ዘይት እየተሰጠ ስለመሰላቸው ከከበባው ዳር ሰለፍ ሰርተው የሸማቾች መታወቂያቸውን በእጃቸው አደረጉ፡፡ ኋላ ወሬ ስለጠማኝ ጭምር ወጣቱ ወደ ወደቀበት ሄድኩኝና ከከበቡት መካከል ያገኘኋቸውን አንዲትን አሮጊት ስለሁኔታው ጠየኳቸው፡፡
ምን አጥፍቶ ነው?
“ዳኛው አብይ ሰላም ብሎ ብቻውን ያለ ፀጥታ ሀይሎች ድጋፍ ሲዳኝ ከፍርድ ቤት አምልጦት ነው፡፡”
ከየትኛው ፍርድ ቤት ነው አምልጧቸው?
“ከልደታ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው አምልጦ የመጣው፡፡”
እስረኛ ነበር?
“በርግጥ እስረኛ እንኳን አልነበረም፡፡ ብቻ ለምስክርነት ተጠርቶ ሲቀርብ ከመመስከሩ በፊት የሚናገረው ሁሉ እውነት ለመሆኑ ዳኛው መፅሃፍ ቅዱስ አልያም ቅዱስ ቁራን ይዞ እንዲምል ሲጠይቁት ነው ነገር የተበላሸው፡፡”
እኮ እንዴት?
“እኔ ሀይማኖት የለኝም ግና መማልህ ግድ ካላችሁኝ እመነቴ በሴት ልጅ ዘንዳ ነውና የአቃቢ ህጓን ጡት ይዤ ልማል፡፡” በማለቱ ዳኛው ተበሳጭተው ፍርድ ቤቱን አስገድዶ በመድፈር ሁለት ዓመት ፈረዱበት፡፡
ይቻላል እንዴ?
“እሱን እንግዲህ ዳኛውን ብትጠይቃቸው የተሻለ ማብራሪያ ይሰጡሃል ባይ ነኝ፡፡” ሲሉኝ ፖሊሶችም ወጣቱን አፋፍሰው ሲወስዱት እኩል ሆነ፡፡ እኛም ተበተንን፡፡
Filed in: Amharic