ፋሲል የኔአለም
ውዷ አገራችን በፖለቲካው መስክ እያሳየችው ላለው አወንታዊ ለውጥ ከፍተኛ መስዋትነት እየከፈላችሁ የምትገኙ ወጣቶች፣ ህወሃትና አጋሮቹ ለውጡን ለመቀልበስ የተለያዩ ስልቶችን ነድፈው እንደሚንቀሳቀሱ በደንብ ታውቃለችሁ።
ቀሪው የትግል ጊዜ ያማረ እንዲሆን የህወሃትንና አጋሮቹን እቅድ አውቆ መንቀሳቀስ ተገቢ በመሆኑ፣ በእኔ በኩል ያሉኝን መረጃዎች እንደሚከተለው አካፍላችሁዋለሁ። ቀልባሾች የምላቸው ህወሃትንና አጋሮቹን መሆኑን ተረዱልኝ።
ቀልባሾቹ ዋና ኢላማ ያደረጉዋቸው የአማራንና የኦሮምያ ክልልን በድርጅት ደግሞ ብአዴንንና ኦህዴድን ነው። በእነዚህ ክልሎች አለመረጋጋት በመፍጠር ለለውጡ የተነሳው አመራር ትኩረቱን ለውጡ ላይ እንዳያደርግ የማደናቀፍ ስራ እየሰሩ ነው። ይህን ለማስፈጸም ከነደፉዋቸው ስልቶች መካከል-
በአማራ ክልል በኩል
አንደኛ፡–
ግጭት መፍጠር- በአማራ ክልል ከሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ግጭት ማስነሳት። በዚህ ረገድ ሰሞኑን የመከላከያ ዋና አመራሮችና መሪዎች መክረውበታል። እልባት ያገኛል የሚል እምነት አለኝ።
ሁለተኛ:–
የብአዴን አመራር እርስ በርሱ እንዲጠራጠርና የለውጡ ሃይሉ በአንድነት እንዳይቆም ወሬ ማስወራት። እነ በረከት ” ከዚህ ወረዳ ባለስልጣን ጋር ተገናኙ፣ እንዲህ እና እንዲያ መከሩ” የሚሉ ወሬዎችን በመንዛት የለውጡ አመራር በአንድነት እንዳይቆም ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ከፍኖተሰላም፣ ከደብረማርቆስ አስተዳደሪዎች ጋር በተያያዘ የተወሩት ወሬዎች ሆን ተብሎ የተነዙ ናቸው። ከወጣቱ የለውጥ አራማጅ የብአዴን አመራር ከሆነው ምግባሩ ከበደ ጋር በተያያዘ የተወራውም ወሬ ሃሰት ነው። ምግባሩ በችሎታውና ፖለቲካውን ቀድሞ በመረዳት በሚሰጠው ትንተና ስለሚበልጣቸው እንዲሁም በረከት በድርጅቱ ውስጥ ተሰሚነት እንዳይኖረው ያደረገው ወሳኝ የብአዴን ሰው ስለሆነ ብቻ ምግባሩን ከሌላው አመራር ለመለየትና ለመምታት የነደፉት ስልት ነው። ወሬው ለውጡን ለሚያራምዱ የብአዴን አመራሮች ሆን ብሎ እንዲደርስ በማድረግና አመራሩ ይህን ሲያጣራ በማዋል ጊዜውን እንዲያጠፋም እየተደረገ ነው። ወጣቱ የወሬው ሰለባ መሆን የለበትም። እስካሁን ባለው መረጃ፣ እነ በረከት ወደ ቅማንትና ሰሜን ወሎ ያደረጉት ጉዞ ትክክል ሲሆን፣ እንቅስቃሴያቸውም በደንብ ይታወቃል።
ሶስተኛ:-
የክልሉን ህዝብ ማወናበድ። ህዝቡ ትኩረቱን ለውጡ ላይ እንዳያደርግ እና እርስ በርሱ እንዲጠራጠር የሚያደርግ ስልት እየተጠቀሙ ነው። ህዝቡ ስራ እንዳይሰራ፣ “እገሌ እዚህ ታዬ፣ እገሌ ከእነ እንትና ጋር መከረ” እያለ ጊዜውን ባልባሌ እንዲያጠፋ እንዲሁም እርስ በርስ እንዲጠራጠርና እንዲጋጭ ስልት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። ህዝቡ በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ፣ የሚወሩ ወሬዎችን በጥንቃቄ ማየት ይገባዋል።
አራተኛ”–
ቀልባሾቹ ቅማንት፣ አገውን እና የቤንሻንጉል ብሄረሰቦችን አካተው አንድ የኩሽ መንግስት እንመሰርታለን በማለት የአካባቢው ህዝብ አብሮአቸው እንዲሰለፍ እየሰሩ ነው። በዚህ በኩል የአገው፣ የቅማንትና ሌሎችን ብሄረሰቦች በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።
አምስተኛ:-
የተለያዩ የፍንዳታ ሙከራዎችን ማድረግ። ቀልባሾቹ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ በኢኮኖሚ አቅማቸው ድሃ የሆኑት ወጣቶችን አሰልጥነው ወደተለያዩ አካባቢዎች ልከዋቸዋል። ከትግራይ ያመጡዋቸውን ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ያሰባሰቡዋቸውን ወደ አማራ ወዘተ አዝምተው ፍንዳታ ለማድረስና እርስ በርስ እንዲጠራጠር ለማድረግ ሞክረዋል። የአማራ ክልል ደህንነቶች በዚህ በኩል ጥሩ ስራዎችን እየሰሩ ነው። እስካሁን ድረስ ወደ 61 የሚጠጉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ከዚህ በሁዋላም ቢሆን የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለፖሊስ ሃይሎች በቻ ማሳወቅ እንጅ የግል ወይም የቡድን እርምጃ አለመውሰድ።
ስድስተኛ:–
በአማራው ላይ ጥቃት እንዲደርስ ማድረግ። በዚህ በኩል ቤንሻንጉል ጉሙዝ ዋና ኢላማ ሲሆን፣ ሰሞኑን የህወሃት የልኡካን ቡድን የጠነሰሰው ሴራ መረጃው አስቀድሞ በመውጣቱ ሊከሽፍ ችሎአል። ተመሳሳይ ከትትሎች እየተደረጉ በመሆኑ ቀልባሾች የወጠኑት ውጥን ይሳካል የሚል እምነት የለኝም።
ሰባተኛ–
በአማራ ክልል አዊ ዞን፣ ከዋናው አመራር ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ያልታወቀ የኦነግ ሃይል ገብቶ ጥቃት እንዲያደርስ ተደርጓል። ይህም ቢሆን በቁጥጥር ስር ውሎአል። ቢሆንም የአካባቢው ወጣቶች በዚህ አቅጣጫ የተነደፈ ስልት ስላለ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።
ስምንተኛ –
በድንበር አካባቢ በተለይም ከትግራይ ድንበር ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ህወሃቶች ትርምስ መፍጠር የለውጡን እንቅስቃሴ ለማክሸፍ አይነተኛ ስልት መሆኑን ተረድተዋል።
ኦሮምያ ክልል
በኦሮምያ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ ክልሉን ወደ ብጥብጥ ለማስገባት ሙከራ እየተደረገ ነው። ህወሃትና ግብረአበሮቹ ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል፦
አንደኛ– “ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ቄሮን እና የኦሮሞን ህዝብ ለማናገር ፍላጎት የለውም፣ ጥያቄዎችን አልመለሰም” የሚል ወሬ ማስወራትና የኦህዴድ አመራር በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ማድረግ።
ሁለተኛ– ታች ያለውን የኦነግ ሴል በተዘዋዋሪ መንገድ በገንዘብ በመደገፍ የተለያዩ ጥቃቶችን ሰንዝሮ ህዝቡ ወደ ብጥብጥ እንዲገባ ማድረግ። በነገራችን ላይ ራሳቸውን ያደራጁ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱና አስመራ ያለው ኦነግ በቀጥታ የማይቆጣጠራቸው ሃይሎች መኖራቸው ትክክል ነው። እነዚህ ሃይሎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁት የህወሃት ገንዘብ እየቀረበላቸው መጠቀሚያ እየሆኑ ነው።
ህወሃት መከላከያውን ተጠቅሞ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አልፏል። አብዛኛው የመከላከያ አባላት የለውጡን እርምጃ ደግፈው በመቆማቸው በዚህ በኩል ያለው ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። አሁን ህወሃት የተለያዩ ወሬዎችን በመንዛትና መለስተኛ ግጭቶችን በማስነሳት ለውጡን ለመቀልበስ እየሰራ መሆኑን አውቀን፣ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ብንከተል ፣ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀፍ ማድረግ እንችላለን።