>

አብዮቶቻችን በትናንሽ ስህተቶች ነው የተጨናገፉት -  አዲሱ ትውልድ ያንን ሊደግም አይገባም!!! (ፋሲል የኔአለም)

አብዮቶቻችን በትናንሽ ስህተቶች ነው የተጨናገፉት –  አዲሱ ትውልድ ያንን ሊደግም አይገባም!!!
ፋሲል የኔአለም
 
አንዳንዴ ለትልቁ አላማ ሲባል ትንንሽ ነገሮችን አይቶ የማለፍ ልምድ ላናዳብር ይገባል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “በክልላችን ለሚፈጠር ችግር ሁሉ ተጠያቂዎች እኛ እንጅ ህወሃት ወይም የቀድሞው የብአዴን አመራር መሆን የለብትም” ብለው በመናገራቸው ትችት እየደረሰባቸው ነው። መተቸታቸው ችግር የለውም። ግን አንዳንዴ  ፈጥኖ “ኪቦርድ” ከመንካት በፊት  እንዲህ እንዲናገሩ ያስገደዳቸው ገፊ ምክንያት ምንድነው ብሎ መመርመር ተገቢ ነው። ምንም ይሁን ምን ይህ ለውጥ በስርዓት ተመርቶ ከታሰበበት ቦታ እንዲደረስ አቶ ገዱ ያስፈልጉናል። ገዱ ክልሉንም ሆነ አገሪቱን ወደ ዲሞከራሲያዊ ስርዓት ለመለወጥ የማያወላዳ አቋም እንዳላቸው አውቃለሁ። በክልሉ ውስጥ ማን ምን እንደሚያደርግ በደንብ ያውቃሉ።  ነገር ግን የተቀመጡበት ወንበር የፈለጉትን እንዲተነፍሱ አያደርጋቸውም።  እንኳን እሳቸው  እኔም እንደልቤ የማውቀውን ሁሉ አልተነፍስም። ገዱ “ህወሃትን ተጠያቄ አናድርግ” ሲሉ  ህወሃት ከደሙ ንጹህ ነው እያሉ እንዳልሆነ ያውቃሉ። በክልሉ ውስጥ በህወሃት እያሳበቡ ለራሳቸው የግል ጥቅም ብቻ በማሰብ ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ ያሉ ሃይሎች የመኖራቸውን ያክል፣ ህወሃት ሆን ብሎ አንዳንድ ሰዎችን እየላከ ክልሉ እንዳይረጋጋ፣ አመራሩና ህዝቡ ትርምስ ውስጥ እንዲገባ የሚጠቀምበትንም ስልት ያውቃሉ፤  ያንን ሴራ ለማክሸፍ የተናገሩት እንደሆነ አስባለሁ።  የኢህአዴግ አባል ሆነው ህወሃትን በአደባባይ ተጠያቂ ሊያደርጉትም አይችሉም። በኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ግን ህወሃትን በግምገማ አላላውስ ከሚሉት ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸው  ሁሉም የሚያውቀው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ነባሩ አመራር “ህዝቡ በእኛና በቤተሰቦቻችን ላይ ጥቃት ሲያደርስብን አዲሱ አመራር የደህንነት ከለላ አልሰጠንም” የሚል ስሞታና ተማጽኖ እያቀረቡ እንደሆነ ይሰማል። ” እኛ ተሸንፈን ቦታውን  ብንለቅ እንኳን በሰላም መቀመጥ አንችልም፣ ሊደርስብን የሚችለውን ጉዳት ተመልከቱት” እያሉ አቤቱታ በማሰማት ጊዜያቸውን እያጠፉ ነው።  ስለዚህ  አቶ  ገዱ ለእነዚህ ሰዎች የደህንነት ዋስትና በመስጠት በሰላም ቦታውን እንዲለቁ   የተናገሩት እንደሆነ ይሰማኛል።
 አሁንም ይህ ለውጥ በስርዓት እንዲመራ የሚፈልጉ ሃይሎች ፣ ትግላቸውን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲያደርጉ ማስታወስ እፈልጋለሁ። ለረጅም ጊዜ ከገዱና ከሌሎችም የኢህአዴግ አመራሮች ጋር ትግል ተካሂዷል። ህዝቡ ባደረገው ተጋድሎ አብይ፣ ለማ፣ ገዱና ደመቀን ጨምሮ አብዛኛው የኢህአዴግ አመራር ከለውጡ ጎን ቆሟል። ከእንግዲህ ከእነዚህ ሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ብልጠት የተሞላበት ሊሆን ይገባል። አንዳንዴ ከመስወር ወጣ ያሉ ቢመስለን እንኳ ትንሽ እድል እንስጣቸው ማለት ይገባናል።  እነዚህ ሃይሎች ከለውጡ ጋር አብረው እንዲዘልቁ የአገራችንን ዲሞክራሲ የምንመኝ ዜጎች ሁሉ በምንናገረውም ሆነ በድርጊታችን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። አይተን ማለፍ ባለብን ሰዓት ማለፍ፣ ማለፍ በሌለብን ሰዓት ደግሞ ፊት ለፊት መናገር መልመድ አለብን። እነሱን አምርረን የምንቃወማቸው ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር ለመግባት ማፈግፈግ ሲጀመሩ ብቻ ነው። እስካሁን ያንን ምልክት ልናይ ቀርቶ፣ እየወሰዱት ባለው ፈጣን እርምጃ “ዋው” እያስባሉን ነው። እርምጃው እንዲቀጥል ግን ለአንድም ሰከንድ ቢሆን አይናችንን መጨፈን የለብንም።  የኢትዮጵያ አብዮቶች በትናንሽ ስህተቶች ነው የተጨናገፉት። ይህ ትውልድ ያንን ሊደግም አይገባም። ለዚህ ነው ከእኔ የተለዬ የፖለቲካ ፍልስፍና ሲከተሉ የነበሩ ሰዎችን ” ነጻነትን እናሰፍናለን” ብለው ቃል ስለገቡ ብቻ የምደግፋቸው።
Filed in: Amharic