>
5:13 pm - Thursday April 18, 2041

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሉ አቶ አብዲ በአቶ ጌታቸው ላይ ያቀረቡትን ክስ ኢህአዴግ እንደማያውቀው ገለፀ

BBC SOMALI

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር የሆኑት አቶ አብዲ ሞሃመድ ከክልላቸው የመገናኘ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሯቸው ነገሮች አነጋጋሪ ሆኗል።

አቶ አብዲ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን የመጀመሪያዎቹን 100 ቀናት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ የለውጥ ውሳኔዎች እንደሚደግፉ ገልጸው፤ ”ባለፉት ዓመታት ለክልሉ ህዝብ ልማት የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተናል። በሥራዎችችን ውስጥ ደግሞ ስህተት ፈጽመናል። ጊዜው የይቅርታ ነው። ስለዚህ ስለሰራነው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን። ስህተትን የማይቀበል ሴጣን ብቻ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከአቶ አብዲ መግለጫ ውስጥ የበርካቶችን ትኩረት የሳበው የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን በሚመለከት የሰጡት አስተያየት ነው። ”ጌታቸው ሙሰኛ፣ ሌባ እና ራሰ ወዳድ ነው” ሲሉ አቶ አብዲ ተደምጠዋል።

• “ከሞቱት አንለይም” የሶማሌ ክልል እስረኞች

• የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ከሥልጣናቸው ተነሱ

አቶ አብዲ ”የክልል አስተዳዳሪ ሆኜ ወደ ጌታቸው ቢሮ መግባት የቻልኩት ከ10 ዓመታት በኋላ ነው። አቶ ጌታቸው ለላፉት 27 ዓመታት ለምን ከሚዲያው ተደብቆ ቆየ? የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሃላፊ እንኳ ህዝብ ፊት ወጥቶ መግለጫ ይሰጣል። እሱ ተንኮል እየሰራ ካልሆነ በቀር ለምን ተደበቀ?” ብለዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ላይ ህዳር 29/2006 ዓ.ም በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ጅግጅጋ እንዳይሄዱ የከለከለው አቶ ጌታቸው ነው በማለት አቶ አብዲ ተናግረዋል።

”አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ የክልል መስተዳድሮችን ይሾማል” ያሉት አቶ አብዲ ”አቶ ጌታቸው አሁን ለመጣው ለውጥ እንቅፋት ይሆናል” ሲሉም ተደምጠዋል።

የአቶ አብዲ ክስ አሁን ለምን?

አቶ አብዲ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በርካቶች ተጠያቂ ያደርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለእሳቸው ተጠሪ በሆነው በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ለሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች አቶ አብዲ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ሂዩማን ራይስት ዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ያሳስባሉ።

በቅርቡ ሂውማን ራይትስ ዎች ”ዊ አር ላይክ ዘ ዴድ” (ከሞቱት አንለይም) በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት በሶማሌ ክልል የሚገኙ እስረኞች የዘፈቀደ እስራት፣ ድብደባ፣ መደፈርና የሰው ልጅ ማሰብ ከሚችለው በላይ እንግልት እንደሚደርስባቸው አትቷል።

በሪፖርቱ መሰረት ይህንን ሲፈፅሙ የነበሩት የእስር ቤቱ ኃላፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ናቸውም ብሏል።

አቶ አብዲ በቅርቡ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርነት እንዲነሱ የተደረጉትን አቶ ጌታቸው አሰፋን በከፍተኛ ደረጃ መውቀስ ለምን አስፈለጋቸው? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።

የሶማሌ ክልል የፖለቲካ ምህዳር እና የአቶ አብዲን አስተዳደር ጠንቅቄ አውቃለው የሚሉት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አቶ ሙስጠፋ ኡመር ሁለት ምክንያቶችን በዋናነት ያስቀምጣሉ።

እንደ አቶ ሙስጠፋ ከሆነ አቶ አብዲ ይህን መሰል ወቀሳን መሰንዘር ያስፈለጋቸው፤ “የአዲሱ የፖለቲካ ለውጥ አካል ሆነው ስልጣን ላይ መቆየት ስለሚፈልጉ ነው። አቶ ጌታቸው እና ሌሎች ግለሰቦች ይፈጽሙ የነበሩትን በይፋ ማውጣት ‘ታዓማኒነትን ያተርፍልኛል’ የሚል ስሌትን በመያዝ ያደረጉት ነገር ነው” ይላሉ።

”ከቀናት በፊት የክልሉ ምክር ቤት ተሰብስቦ ባለበት ሰዓት አቶ አብዲ አንድ ጥቁር ቦርሳ ይዘው መጡ። ከዚያም ‘በዚህ ሻንጣ ውስጥ በርካታ ሚስጥሮች አሉኝ። የክልሉ ባለስልጣናት እና የፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት ሚስጥር እዚህ ውስጥ አለ። ገንዘብ የከፍልኳቸው ባለስልጣናት አሉ። እኔን ቢነኩ ይህን ሚስጥር አወጣለሁ’ በማለት ሲያስፈራሩ ነበር” በማለት ተናግረዋል።

የአቶ ሙስጠፋ ሌላኛው ምክንያት ”አቶ ጌታቸው አቶ አብዲን ከስልጣናቸው በተደጋጋሚ ለማንሳት ሙከራ አድርጓል። ይህንንም ለመበቀል ያደረገው ሊሆን ይችላል” በማለት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

አቶ አብዲ በቴሌቪዥኝ በተላለፈው መግለጫቸው ላይ ‘አብዲ ጌታቸው ከተባረረ በኋላ ነው ስለሱ የሚያወረው ሊለኝ የሚችል አመራር የለም። ለሁሉም የኢህአዴግ ማዕከላዊ የኮሚቴ አባላት አቤት ብያለው” ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኮሚኬሽን ኃላፊ ሆኑትን አቶ ሳዳት ጠይቀን ነበር። ”አቶ አብዲ የሰጡትን መግለጫ ተመልክቻለሁ። አቶ አብዲ በጽሁፍም ሆነ በስብሰባዎች ላይ ይፋ በሆነ መልኩ ያቀረቡት ጥያቄ ስለመኖሩ የምናውቀው ነገር የለም። ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ያላቸውን ቅሬታ አንስተው ሊሆን ይችላል። በጽ/ቤት ደረጃ ግን የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበርና የኢህዴግድ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርም ”ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም። ለእኔም በግሌ የነገረኝ ነገር የለም፤ ሊነግረኝም አይችልም። እንዲህ አይነት ቅሬታም ካለ ህግ እና ሥርዓትን በመከተል ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማቅረብ ነው ያለባቸው። ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። ይህ አይነት አቤቱታ ለማዕከላዊ ኮሚቴ የሚቀርብ አይደልም። የማውቀው ነገር የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ ማናቸው?

አቶ ጌታቸው አሰፋ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ለበርካታ ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ይምሩት እንጂ ስለማነነታቸው እና ሥራቸው በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

ትውልዳቸው መቀሌ ከተማ ስለመሆኑ እና በወጣትነት ዘመናቸው ዊንጌት ስለመማራቸው በስፋት ይነገር እንጂ ይህም ቢሆን እውነትነቱ የተረጋጋጠ አይደለም።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከቦታቸው እንዲነሱ ከተደረጉ ግለሰቦች መካከል አቶ ጌታቸው አንዱ መሆናቸው ይታወሳል። ከሳምንታት በፊት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ባውጣው መግለጫ ጄነራል አደም መሃመድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው አቶ ጌታቸውን ተክተዋል

Filed in: Amharic