>

ወቅታዊ መረጃ - ያሬድ ሹመቴ

~የአቶ ኢሳያስ መምጣት እስከ አሁን በይፋ አልተገለፀም
~ቴዲ አፍሮ አይዘፍንም
~ዝግጅቱ ሚሊንየም አዳራሽ እንጂ ቤተ መንግስት አይደለም
ያሬድ ሹመቴ
የፊታችን ቅዳሜ ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች አቀባበል ለማድረግ እሁድ ምሽት በሚሊንየም አዳራሽ ስለሚካሔደው የሙዚቃ ዝግጅት የሚመለከት መረጃ እነሆ።
በዚህ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ከታዋቂ አንጋፋ እና ወጣት የሀገራችን ድምጻዊያን ጋር ስራዎቹን ያቀርባል። ከነዚህም መሐል የትዝታው ንጉስ ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ፤ አንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ፤ ድምጻዊ ንዋይ ደበበ፤ ድምጻዊ ፀጋዬ እሸቱ፤ ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽ፤ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ፤ ድምፃዊ አብርሐም ገብረ መድህን፤ ድምጻዊ ታደለ ገመቹ፤ ድምጻዊ ዮሴፍ ገብሬ /ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ/፤ ድምጻዊ ፀጋዬ ስሜ፤ ድምጻዊ ሚዛን ተስፋዬ፤ ይገኙበታል (ከዚህም በላይ ድምጻዊያን ሊጨምር ይችላል)
በባህላዊ ሙዚቃ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ቴአትርን ጨምሮ፤ ራስ ቴአትር፤ የማዘጋጃ ቴአትር አዳራሽ፤ የኦሮሞ ባህል ማዕከል፤ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር እንዲሁም የሀገር ፍቅር ቴአትር በጋራ በመሆን፤ ከሁሉም የተውጣጡ አንጋፋ እና ወጣት የሀገራችን የባህል ድምጻዊያን በጋሽ አበራ ሞላ /ስለሺ ደምሴ/ ፊታውራሪነት የባህላዊ ሙዚቃ ዝግጅታቸውን ለማቅረብ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ በልምምድ ላይ ይገኛሉ።
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ጉዳይ ከሁለቱም መንግስታት እሰከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በይፋ የተገለፀ ነገር የለም፤ ምን አልባት ከደህንነት አንጻር መረጃው ለግዜው ተይዟል የሚል ግምት ቢኖርም የተጨበጠ ይፋዊ መረጃ ግን እስከ አሁን ድረስ አልወጣም።
ድምጻዊ ቴውድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ካለፈው ፋሲካ እለት አንስቶ የሙዚቃ ዝግጅቱን በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ለማቅረብ አቅንቶ እስከ አሁን ድረስ እዚያ የሚገኝ ሲሆን፤ በቀናት ውስጥ ወደ ሀገሩ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ቴዲ አፍሮ በዚህ ዝግጅት ላይ እንዲዘፍን በቀጥታ የደረሰው ምንም ጥያቄ የሌለ ሲሆን፤ ከአሜሪካም የሚመለሰው የሙዚቃ ቡድኑን አባላት ይዞ ሳይሆን ብቻውን በመሆኑ በእለቱ የሚያቀርበው የመድረክ ዝግጅት እንደማይኖር መረጃ አግኝቻለሁ። የሆነ ሆኖ ድምጻዊ ቴውድሮስ ካሳሁን የረዥም ግዜ ህልሙ የሆነው የሁለቱ አገራት እርቅ እውን በመሆኑ በእለቱ አዲስ አበባ ከደረሰ ዝግጅቱን በእንግድነት እንደሚታደም ይጠበቃል።
Filed in: Amharic