>
5:18 pm - Sunday June 16, 6154

ፖለቲከኛው ነብይ (ዳንኤል በላይነህ)

ፖለቲከኛው ነብይ
ዳንኤል በላይነህ
ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን ተዓምር ከማንም በላይ ከነቢይነት ባልተናነሰ የፖለቲካ ትንታኔ የተነበየ ሰው ቢኖር ያሬድ ጥበቡ ነው ብል በፍፁም የተሳሳተ አስተያየት አይመስለኝም። በኔ ዕምነት የእኚህን ታላቅ የፖለቲካ ሊቅ ያህል ማንም የኢትዮጵያን የአርባ ሰባት ዓመታት ምስቅልቅል የተረዳ፣ ማስረዳት የቻለ፣ የነበረውንና ይልቁንም ሊሆን ያለውን (በበጐም ሆነ በክፉ) መኖሩን በሚያጠራጥር ዓይነት፣ የእሳቸው ብቻ በሆነ ብቃት የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እና የታለፈውን ውጣ ውረድ እጅግ ባማረ ቋንቋ በዚህ መጽሐፍ አቅርበውልናል። ማንም ይህንን መጽሐፍ ሳያነብ ስለ ኢሕአዴግና የህወሃት ተፈጥሮ፣ ስለ ኢሕዴን/ብአዴን፣ ኦሕዴድ፣ መኢሶን፣ ኢሕአፓ፣ “ቦናፓርቲዝም” ስለሚባል ነገር፣ ስለባለታሪክ ኢትዮጵያውያን እና በትልቁም ኢትዮጵያችን ተደግኖባት ስለነበረው አደጋና ስለታለፈው ሤራ ለመናገር ባይሞክር ይሻላል። እንደኔ ዕምነት የያሬድ ጥበቡን ያህል አብጠርጥሮ የሚያውቀው የእርሳቸውንም ያህል አሳምሮ ሊተርከው የሚችል ሌላ ሰው ያለ አይመስለኝም።
በመሆኑም በኔ ደረጃ የመጽሐፉን ይዘት፣ ያሬድ ጥበቡ ለሃያ አምስት ዓመታት በየዘመኑ ተፈጥረው በነበሩ አስጊ፣ ተስፋ ሰጪ፣ አስደንጋጭ እና ወሳኝ ሃገራዊ ሁነቶች ላይ የሰጧቸውን ቃለ-መጠይቆች ለመተንተን አልደፍርም። አስደናቂ የፖለቲካ ነቢይነታቸው በግልፅ የሚታይና የማያከራክር ሆኖም ግን፣ እንደማንኛውም ነቢይ ትንቢቶቻቸው መቶ በመቶ ልክ ይዘውላቸዋል ማለት አይቻልም። እንደውም አንዳንድ ጊዜ ግምቶቻቸው አጠቃላይ ትንተናቸውን በአደገኛ መልክ ሊያዛቡ ይችሉ በነበረበት ዓይነት የሚስቱባቸው ሁኔታዎች አሉ። ያንን እሳቸውም አይክዱትም፣ ለምን 100/100 አላመጡም ብሎ መጠየቅም አጉል ድፍረት ከመሆን አልፎ ሞኛ-ሞኝነትም ይሆናል። አንዳንድ ቦታ የግምቶቻቸው ውል መሳት በአንዳንድ በትጥቅ ትግሉ አብረዋቸው በነበሩ ግለሰቦች ላይ ከነበራቸው የተጋነነ ዕምነት የተነሳ ሲሆን፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ በተለይ ስለመለስ ዜናዊ ያ’ላቸው የሚመስለው አድናቆትና ርግጠኝነት የፈጠሯቸው ይመስለኛል። ነገሩ ትንሽ የዋህነት የማያጣው ቢመስልም፣ እያንዳንዱን ጉዳይ በተለይ ጉዳዩ በሆነበት ዘመን ከነበሩት ሁነቶች አንፃር መመልከት ከተቻለ፣ አንዳንድ የተሳሳቱባቸው ግምቶች የእሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የብዙ ሌሎች ተንታኞችም ስለሆኑ “የዋህነቱን” መጋራት እና የጋራ ኃላፊነትም መውሰድ የግድ ነው።
በተለይ የትግል ጓዶቼ በሚሏቸው በረከት ስምዖን እና አዲሱ ለገሠ ላይ በነበራቸው ዕምነትና ርግጠኝነት ምክኒያት እዛ ላይ በመመርኮዝ አስቀምጠዋቸው የነበሩት በርካታ ተስፋዎችና ትንቢቶች ወደበኋላ እንዳልሆነ ሲሆኑ ትንተናዎቻቸውን ማዛባት ብቻ ሳይሆን ተስፋቸውንም በማጨለም እንዴት እንዳቆሰሏቸው መረዳት ይቻላል። እሳቸውም  ይኼው ሰዎች ላይ የነበራቸው መተማመን በተግባር እንዳልነበረ ሲሆን “አልቅሼ ዝም ከምል” በሚል በ1997 በወጣ ጽሑፋቸው  “ምን ሁነህ ነው የምታለቅስ? ብሎ በጎንደር አማርኛ የሚጠይቀኝ ካለ፣ መልሴ ብዙም የተራቀቀ አይደለም። ጓደኞቼን ቀብሬ ነው። ትላንት የተገደሉትን የአዲስ አበባን ሰማዕታት ማለቴ ሳይሆን በአዲሱ ለገሠ እና በበረከት ስምዖን ሞት የተነሳ ነው ለቅሶዬ።” ብለው ዕምነታቸውን ገለባብጠው በደንደሳቸው ስለጣሏቸውና ወሽመጣቸውን ብጥስ ስላደረጉት ጓዶቻቸው የዕንባቸው ርጥበት እስኪሰማ ድረስ አምርረው ያለቅሳሉ። ይህ ሁሉ ሆኖም፤  ምናልባት እንደሳቸው ዓይነት የረቀቀ የፖለቲካ ትንተና ብቃት ያለው ሰው ግምቶች ሲሳሳቱ የሚሰጡት ስሜት የበለጠ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ዕውነት ለመናገር በጽሑፎቻቸውም ሆነ ባለፉት 27 ዓመታት ከሰጧቸው ቃለመጠይቆች (ዐቢይ ከመጣ በኋላ የሰጡትን ሁሉ ጨምሮ) ተናግረው ካልያዙላቸው ጥቂት ትንበያዎች በበለጠ፣ እንቅጩን የተነበዩባቸው በርካታ ሁነቶች ዕውን ሆነዋል።
ገጽ 108 ላይ እንዲህ ይላሉ…
“አቶ መለስ የተሰጣቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የማስከበርና የማስጠበቅ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እንደሌሎች ከፊልና ሙሉ ኤርትራውያን ሁሉ አሰብ የኤርትራ ናት የሚል ክርክር ከመላው ‘ሕዝባቸው’ ጋር ገጥመዋል። የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ለሰባት ዓመታት ከሕዝብ ከነጠለው አፍቃሪ ሻዕቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዕምነት ጋር በመንጐድ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ ይቆማል ብሎ ለመገመት አዳጋች ነው። አመራሩ ከሕወሃት/ኢሕ አዴግ የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ በላይ የአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ይቀድማል ብሎ በመወሰን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የ ዐሥር ዓመታት አገዛዝ ምዕራፍ ሊዘጋ ይችላል ብሎ መገመት የሚቻል ይመስለኛል። የነገ ሰው ይበለን።”
ከዛ ደግሞ ስለመለስ ዜናዊ ያ’ላቸውን/የነበራቸውን አድናቆት በሚያሳይ ዓይነት እንዲህ ይላሉ…
“…ይበልጥ [ከግንቦት 97 እስከ ነሐሴ 04] ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከበረሃ ጓዶቻቸው በላይ ልቀው የወጡበት፣ በዙሪያቸው አቤት ባይ ባይ እንጂ ‘ሃይ! ቶሽ!” የሚል ያልነበረበት ስለሆነም ግላዊ ስልጣናቸውን ለአገራቸው ላላቸው ራዕይ ተግባራዊ ያደረጉበት ዘመን ነበር። ከሩቅም እንደምገምተውና አንዳንድ መረጃዎችን ሳያይዝ ከማየው፣ አቶ መለስ [ወደ ጥናትና ምርምር አዘንብለው] የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግ ይታትሩ የነበረበትና ከኢትዮጵያ እውነታ ጋር ሲጋጭ ያለውን ውጤት ይሞክሩ የነበረበት ዘመን ነው። [ከ 97 ምርጫ በኋላ] ሱሪያቸውን አራግፈው የተነሱበት፣ የልማት አቅጣጫዎችን የተለሙበት፣ ከጊዜ ጋር ጥድፊያ የያዙበት ወቅት ነበር። የዲሞክራሲ መድረኮችን ማጥበብ፣ የሚዲያ ነፃነትን መገደብ፣ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል፣ በመከላከያና ፓርቲ መካከል፣ በደኅንነት አውታሩና ፓርቲ መካከል ውሕደትን በማካሄድ በአንድ ማዕከል የሚቀሳቀስ አገር የማዘመን ተልዕኮ የተያያዙበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መድረክ ነበር።” – ገጽ 167
አንዴ ደግሞ፣ መለስ ዜናዊ የጎርባቾቭ ብሩህነት የተላበሱ ብቻ ሳይሆን የሶቪየቱ መሪ የጐደላቸውን “የፖለቲካ ብልጠት” ያሟሉ ባለራዕይ ሊሆኑ እንደሚችሉ በነበራቸው ትንበያ…
“…አቶ መለስ ‘የትግራይ ዘመን ዘንድሮ ነው’ የሚሉ ኃይሎች ላይ የጀመሩት “የተሐድሶ” ዘመቻ ባለፉት ዐሥር ዓመታት የተገነባውን አስከፊ አድሏዊ ሥርዓት ማንበርከክ ላይ የሚጫወተው ሚና በመኖር፣ እንፋሎቱን እሲጨርስ ባቡሩ እንዲያዘግም መተው የሚለው ስሜት ይፈታተነኛል። አቶ መለስ አሁን በያዙት ፍጥነት ከቀጠሉ ባለፉት ዐሥር ዓመታት የገነቡትን የትግራይ አድሏዊ ሥርዓት የሚያፈርሱ ጎርባቾቭ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ጎርባቾቭ ብሩህ እንደሆኑየተመሰከረላቸው ሲሆን፣ የፖለቲካ ብልጠት ግን ‘ይጎድላቸው’ ነበር” ብለው፣ መለስ ሁለቱን ሊያሟላ ይችላል ከሚል ዕምነት ተነስተው ትንሣዔን ከመለስ የመጠበቅ ተስፋ ያንፀባርቃሉ።
ከዛ ደግሞ …
“ተቃዋሚው ኃይል ብስለትንና ጥንካሬን እያካበተ፣ ርዕዩ እየሰመረ፣ ሕዝቡ መሪዎቹን እያወቃቸው ይሂድ እንጂ፣ ኢሕአዴግ ከትግራይ አድሏዊ አሽክላው ራሱን እያፀዳ ለመሄድ ከተገደደ ዛሬውኑ ሥልጣን ከኢሕአዴግ ባለማፈትለኩ ማዘን ያለብን አይመስለኝም። ብዙዎቻችን በስደት እንዳለን የጡረታ ዕድሜያችን ይደርስ ይሆናል፤ የኢትዮጵያ ተስፋ ግን ይጨልማል ብሎ መከራከር አዳጋች ነው” ብለው እንቅጯን ይተነብያሉ።
ይቀጥሉና…
“[የኢሕአዴግ መሪዎች] ል[ጆቻ]ቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ አገራቸውን የታደጉ እየመሰላቸው ዛሬ በዝምታ ወይም በጭብጨባ የሚያሳልፉት ፍጻሜ፣ ነገ እነሱንም ጭዳ የሚያደርግ ሒደት መሆኑን ከወዲሁ ማወቅ አለባቸው። ለኢሕአዴግ መሪዎች ማን መካሪ አደረገህ የሚሉ ሃያሲያን ደስተኛ እንደማይሆኑ አውቃለሁ። እኔ ግን በሰው ልጆች ላይ ተስፋ አልቆርጥም። ቀናውን መንገድ ካሳየናቸው ለመከተል ይከጅላሉ የሚል ዕምነት አለኝ። የደቡብ አፍሪካ ዘረኞችን በውስጣቸው የተዳፈነው ሰብዕናቸው ካሸነፋቸው፣ የኢሕ አዴግንም መሪዎች ሰብዕና ማንቃት ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ሕይወታቸውን ለመስዋዕትነት የሰጡ ሰዎች ስለነበሩ፣ ሐቁን እንዲይዩ ብንረዳቸው የጨለማው ዘመን እንዲያጥር ይረዳል ብዬ አስባለሁ። የወያኔ አገዛዝ እንዲያከትም ከተፈለገ የክልሉን መሪዎች፣ እንወክልሃለን ከሚባሉት ሕዝብ ጋር እያጋጨ የሚጠቀምባቸውን ወያኔን እንዲነጠሉት ማድረግ ተገቢ ነው።” ብለው ከ17 ዓመታት በፊት ስለዘንድሮ ይመክራሉ።
ከስድስት ዓመታት በፊት ደግሞ… 
“እንደ እኔ እንደ እኔ ከአሁን በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ስንመርጥ ቃለ-መሐላ የሚፈጽምበት ዕለት ስመ-ሥልጣን ወይም የሥልጣን ስም የሚመረጥበትም ቀን ቢሆን ደስ ይለኛል። … ስለሆነም ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያለኝ መልዕክት ከካድሬ ቋንቋ ራቁ፣ የራስዎትን ድምጽ ፈልገው ያግኙ፣ ሰው ሰው ሽተቱ፣ ሆደ-ሰፊ ይሁኑ የሚል ነው።” ብለው፤ ያንን ካሉ ከዓመታት ዐቢይ አሕመድ እንደሚከሰት ቀድመው እንዳወቁ ዓይነት አስቀድመው ለራሱ የጻፉለት የሚመስል ትንቢታዊ  ደብዳቤ ያስነብቡናል።
የዘውዴ ረታ መጽሐፍ ላይ ባቀረቡት ግምገማ ላይ ደግሞ… 
“… እኔ በግሌ የተማርኩት ነገር ቢኖር፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ገባር ጫንቃዬን ከበደኝ፣ መሸከም አልቻልኩም፣ ‘እኔም በሰብአዊነቴ ከፈጣሪዬ ጋር የምጋራቸው የማይ[’]ነኩ መብቶች አሉኝ’ ብሎ እምቢኝ! አሻፈኝ! እስካላለ ድረስ፣ ሕልመኞች እርስ በርስ ይተላለቃሉ፣ አገሪቱም በኋላ ማርሽ ቁልቁል ትወርዳለች። ወይ ገባሮቿ ተነስተው ዜግነታቸውን ይጠይቃሉ፣ አሊያም፣ የሞት ሽረት ሚዛን ላይ እንዳቃሰተች የወሮበሎች የጦር አውድማ ትሆናለች። ወንድሞቼ! እህቶቼ! ገባሮቿ ዜግነታቸውን እንዲጠይቁ የሚረዳቸውን ሁሉ ለማድረግ አንስነፍ።እንጻፍ፣ እንግጠም፣ እንቀኝ፣ እንሸልል፣ እንተውን፣ እናጥና፣ ከሁሉም በላይ ግን ሁላችንም የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች በመሆናችን እንከባበር፣ እንመካከር፣ እንደማመጥ፣ እንተማመን። ብለው ዐቢይ አሕመድ ከመከሰቱ 6 ዓመታት በፊት በዐቢይ አሕመድ ልሣን ይማፀናሉ።
እንዳላቸከው ብዬ ነው እንጂ ዕውነት የሆኑ ትንቢቶቻቸውን በሙሉ እዚህ ላይ ብዘረዝራቸው ቦታ አይበቃኝም። በዛ ላይ ዓላማዬ መጽሐፉ ያሳደረብኝን አድናቆት ለማካፈልና ማንበብ የሚችል፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩ የሆነች ሰው ሁሉ እንዲያነበው አበክሬ ለመወትወት እንጂ መጽሐፉን አሳጥሬ ለማቅረብ ስላልሆነ፣ ቢበቃኝ ይሻላል። በአጠቃላይ ግን፣ ራሱን ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና አስተዳደር ላይ የተሠማራ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህንን መጽሐፍ እንደ ቴክስት ቡክ ካላነበበው፣ ለሥራው ብቁነት ኮምፐልሳሪ ኮርስ ስላልወሰደ ለመመረቅ እንዳላሟላ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑ ነው ብዬ አምናለሁ። በነገራችን ላይ ያሬድ ጥበቡ ስለ አምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ ባቀረቡት ግምገማ ላይ መጽሐፉ ያሳደረባቸውን አድናቆትና ታሪካዊ ፋይዳውን አጠቃለው ሲገልፁት እንዲህ ይላሉ…
“እኔ የኢሕአዴግ አመራር አባል ብሆን የድርጅቱ መሠረታዊ ህዋሳት በሙሉ በዚህ ታሪካዊ መጽሐፍ ላይ የወራት ጥናት እንዲያደርጉ መመሪያ እልክ ነበር።፡ምክኒያቱም ላለንበት ዘመን ያለው ተፈላጊነት ታላቅ ነውና።”
እኔ ደሞ ስለ “ወጥቼ አልወጣሁም” መጽሐፍ እንዲህ እላለሁ…
በኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር ላይ ላሉ የፖለቲካ አካላትና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ለሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን የያሬድ ጥበቡን ታሪካዊ መጽሐፍ ማንበብና በመጽሐፉ ላይ መወያየት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ኮምፐልሰሪ ነው!
በመጨረሻ ይህንን በማለት ላብቃ፤ እንደዚህ ዓይነት ወደር የሌለው የፖለቲካ ተንታኝ፣ ታሪክ ነጋሪ፣ ብቃቱ ሊጠየቅ የማይቻል ባለተሞክሮ እና አስገራሚ ነቢይ፣ አሁን ላለንበት ዓይነት እጅግ ታላቅ የትራንስፎርሜሽን ሂደት ለኛም፣ ለዐቢይም፣ በተለይም ለኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምትክ በሌለው ዓይነት ያስፈልጋል። እናም እባክዎ ውድ ያሬድ ጥበቡ፣ በሚያምኑት አምላክ እንለምንዎታለን፤ ባገኙት መንገድ ሁሉ፣ አገርዎ መግባትን ጨምሮም ቢሆን፣ የታሪኩ አካል ይሁኑ! እንደሱ እንዲሆን ከዚህ የተሻለ ዘመን፣ ከዚህ ጊዜ የተሻለ አጋጣሚና ከዚህ ወቅት የተሻለ ዕድል ያለዎትም፣ ያለንም አይመስለኝም።
ምንም ተስፋ ቆርጠንበት የነበረው ‘የዛ ትውልድ’ አባል፣ ስታሊኒስት ታጋይ የነበሩ ቢሆን፣ ምንም የኢሕአፓ/ኢሕዴን መሥራች የነበሩ ቢሆንም፤ በተሞክሮ፣ በዕድሜ፣ በብስለት እና በስደት ሰብዓዊነትዎ አሸንፎ የተስፋችን ማንሰራራት ነፀብራቅ ሆነውልናልና በእኛ ትውልድ እንደሚ’ገባዎ ላናከብርዎ አንችልም። በዕውነትም፣ በዓሉ ግርማ እንዳለው፤ “በሰው ልጅ ተስፋ አትቁረጥ፤ ምናልባት የመጨረሻው ተስፋ እሱ ነው።”
እንኳንም ኢትዮጵያችን እርስዎን አፈራች! ፈጣሪ እርስዎንም፣ ቤተሰብዎንም እና የሚወዷትን ኢትዮጵያ ይባርክ፤ ዕድሜና ጤናም አብዝቶ ይስጥልን፣ እንደሠይፍ የሰላውን አዕምሮዎንም እንደሰላ ያቆይልን!
Filed in: Amharic