>

ታሪክ ራሷን ደገመች!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

ታሪክ ራሷን ደገመች!!! 
ቬሮኒካ መላኩ
ታሪክ ራሱን ይደግማል ወይስ አይደግምም የሚሉ ክርክሮች በታሪክ ባለሙያዎች ፣ በፈላስፎች እና በፖለቲከኞች መካከል ለብዙ ዘመናት ሲያሟግት ኖሮ አሁንም ንጥር ያለ መልስ አላገኘም።
እነ ቶይንቤ እና አሜሪካዊው ፖለቲከኛ  ኪስንጀር ” ታሪክ ራሱን ይደግማል ”  ብለው ሲከራከሩ ። ሌሎች ፈላስፎች በተቃራኒው “ታሪክ ራሱን አይደግምም ባይሆን በአዲስ መልክ ይከሰታል ” ይላሉ።
ዲዲሮ የተባለው  ፈላስፋ ደሞ ይሄን በምሳሌ ሲገልፅ << በአንድ ጅረት ውስጥ ሁለት ጊዜ አትታጠብም ። የታጠብክበት ውሃ አልፎ ወርዷል ። እንደገና የምትታጠበው በአዲስ ውሃ ነው ። ታሪክም እንደ ወራጅ ጅረት ውሃ ስለሆነ ዝም ብሎ መፍሰስ ነው እንጅ ራሱን አይደግምም >> ይላል ።
እኔ  በበኩሌ ከሁለቱ ሙግቶች ውስጥ ” ታሪክ ራሱን ይደግማል ” የሚለውን ከተቀበልኩ ቆይቻለሁኝ።
ይሄው “ታሪክ ራሱን ይደግማል ” ለሚለው የፈላስፎች አባባል ተጨማሪ ምስክር ይሆን ዘንድ ትናንት ሃዋሳ ላይ በቲቪ ስክሪን ታሪክ ራሱን ሲደግም በአይኔ በብረቱ አየሁት በጆሮዬ ሰማሁት ።።
የሀዋሳውን ክስተት ስመለከት  አንጎሌ በአንድ ወቅት የጋሼ አሰፋ ጫቦ” የትዝታ ፈለግ ” መፅሀፍ ላይ ሳነብ ያከማቸውን ክስተት በርብሮ ማስታወስና ማጠንጠን  ጀመረ።
ይሄ ክስተት ምንድነው ? መፅሀፉ እንደማስታውሰው እንደሚከተለው ይላል ” በ 1980ዎቹ አጋማሽ በሽግግር መንግስት ምስረታ ወቅት የኤርትራው ፕሬዚደንት  ኢሳያስ አፈወርቂ  አዲስአበባ በውይይቱ ለመካፈል ይመጣል ። በዚህ ትልቅ ጉባኤና ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች  ፣ምሁራን ፣ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በተገኙበት አዳራሽ ውስጥ መድረክ ላይ ፕሬዚደንት ኢሳያስ ንግግር ሊያደርግ ወደ መድረክ ይወጣል ። ኢሳያስ ንግግሩን በትግሪኛ ሲያደርግ ወደ አማርኛ እንድመልስለት  ፕሮፌሰር በረከተ አብ ሃብተስላሴን ወደ መድረክ ይዞት ይወጣል። ኢሳያስ ይናገራል በረከተአብ ወደአማርኛ ለህዝቡ ይረረጉማል ።
በመሀል ኢሳያስ በረከተአብን ትርጉም አትችልም ብሎ አባረረው ።  ኢሳያስ ፕ/ሮ በረከተአብን ከመድረክ ካስወገደ  በኋላ ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አዳራሹ ፊት ለፊት ገትሮ መለስን ወደ አማርኛ አስተርጓሚ አደረገው  🙂 እንደ አገር ሲታሰብ ዊርድ ነገር ነው።
አዋሳ ላይ ታሪክ ራሷን ደገመች ። ኢሳያስ አፈወርቂ ከ25 አመታት በኋላ ሌላውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መድረክ ላይ ገትሮ አስተርጓሚ ሲሆነው ተመለከትኩኝ። በጣም ገረመኝ። አይኔንም ማመን አቃተኝ ። በዚህ ጉብኝት በተደጋጋሚ ፕሮቶኮል ሲደረመስ ተመልክቻለሁ ።
ነገሩ ትንሽ አስቂኝ ቢሆንም ኢሳያስ የኢትዮጵያን መሪዎች እንደ አስተርጓሚ መጠቀሙ ፈፅሞ ምቾት አልሰጠኝም።
በመሰረቱ በብሄራዊ ቤተመንግስት ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ  የኤሪትራውን ፕረዚደንት ኢሳያስን በአማርኛ እንድናገር መድረክ ላይ ሙግት አይነት ነገር መግጠም አልነበረበትም። እሱኛው Scene ( ትእይንት ) ትንሽ ዊርድ ነገር አለበት።
 የእኔ አመለካከት እስካሁን የማከብረውን እና ለአገሬ ተአምር ይሰራል ብየ የማስበውን መሪ ከእነ ሙሉ ክብሩ እንዲገኝ እፈልጋለሁኝ ።  ፕሬዚደንት ኢሳያስ እንደዛ ተጠይቆ እየከበደው ዋናው መድረክ ላይ አማርኛ ማውራቱ ለእኔ ምንም ትርጉም አይሰጠኝም ። እውነት ለመናገር ኢሳያስ  በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ሳይሆን በጉትጎታ ማውራቱ እንደውም ተገቢም አይደለም ፣መጠየቅም አልነበረበትም ።  ሰውየውም እንደተባለው አማርኛ በደንብ የሚችል አይመስለኝም ወይም ጠፍቶበታል ። የዚህን ምልክት ትናንት አይቻለሁኝ። በተረፈ የኢትዮ ኤርትሪያ ግንኙነት እጅግ የሚያስደስት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ  በመርህ ላይ የተመሰረተና ጥንቃቄም የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን መጠቆም እፈልጋለሁኝ።
Filed in: Amharic