>

የዛሬዋን ቀን በትንቢት መነጽር አሻግሮ በማየቱ በዘመኑ ዞምቢዎች የታገደው "ማኔ ቴቄል"!!!

የዛሬዋን ቀን በትንቢት መነጽር አሻግሮ በማየቱ በዘመኑ ዞምቢዎች የታገደው “ማኔ ቴቄል”!!!
ዮቶር አብ
ዛሬ በካርቶን ታሽገው የመደርደሪያ ያለህ የሚሉትን መፃህፍት በማየት እያነሳሁ እየጣልኩ የሚገረቡትንም መገረብ ፈለኩ ይህንን የማደርገው ደግሞ ፊዮሪና እና እነዛ የናቅፋ ተራሮች በህሊናየ ሲመላለሱ ኦሮማይን ለማንበብ ነበር በካርቶን ውስጥ ተቀምጠው የዘመናት ጩኽት የሚያስተጋቡትን መፅሃፍት የምመለከተው ። ታድያ በዚህ ሰዓት አንድ መፅሃፍ እጀ ላይ ገባ መፅሃፋ በትንቢት የተፃፈ ይመስላል የኢትዮጵያና የኤርትራን አንድነት ፍቅር ይናገራል ገብያ ላይ በዘመኑ ዞምቤዎች እንዲነሳ ተደርጓል ። ብታነቡት ትደመመለችሁ ደረሲው ለምን ዝምታን እንደመረጠ አልገባኝም።  ርዕሱ #ማኔ_ቴቄል ይሰኛል።አሁን ለዛሬ በደስታ ከቤት የማያስወጣኝን የክረምት ትጥቅ የታጠኩ ይመስለኛል።  የመፅሀፉን መግቢያ ለእናንተ እንዲመች እንዲህ ላካፍላችሁ ።
ኔቴቄል የመጀመርያ እትም ሐምሌ 2008
ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ
መግቢያ
የንፋሱ አውታር እያስገመገመ ያገኘውን እየጠራረገ ደከም ያሉ የቆርቆሮ ቤቶችን እየገነጣጠለ የአመጽ መጀመርን ሟርት ነጋሪ መስሏል..ይህ ያለንበት ዘመን ጭንቀት፣ጩኽት፣ፍርሃት የነገሠበት ጊዜ የታሪክ መፍለስ የነገሮች እርስ በእርሣቸው መቃወስ የሃገር መበታተን ማንነትን የመዘንጋት አባዜ በትውልዱ ላይ የታየበት ጊዜ..
ህዝቡ የተረጨውን አዚም ባያውቅም አፍንጫውን አውዶ በል በል እያለ የሚገፋፋው ነገር ቢኖር የአውሬነት ባህሬ ተላብሶ እርስ በእርስ መተራረድ፣መጨፋጨፍ፣መገዳደልን የሚናፍቅ ፣ነፋሻው ንፋስ የሚያናፍሠው ዓየር ቢኖር ቀባሪ ያጣ የአስከሬን ሽታ ፣ታዳጊ ያጣ ትውልድ ፣አፋሽ ያጣ ደም፣የአኬልዳማ ጩኽት..
ነገሩ ከወዲሁ የገባቸው እንስሳት ይህን ክፉ ወቅት ላለማየት በዋሻው የተደበቁ ቢኖሩም አብዛኛወቹ ደግሞ የሠው ሳይበቃ ጭራሽኑ ከሀገር የሚሰደዱበት ጊዜ፣ጨረቃ በፍርሃት የተደበቀችበት፣ሠማይ በቁጣ በደረቅ ነጎድጓድ ያስገመገመበት ፣የሞት ጥላ በሀገሪቱ ዙሪያውን ያጣለበት ወንድም ከወንድሙ፣እናት ከልጇ በዋይታና በለቅሶ የተለያዩበት፣አብሮ አደግ በሀዘን ከንፈር የመጠጠበት ባለትዳሮች ፍቅረኞች በመሪር እንባ መራጨት የተለያዩበት የምፅዓት ቀን…
የንጥቂያ ጊዜ..ረግቶ የማያውቅ ለይምሰል የቆመ በየጊዜው የሚለዋወጥ ግራ የገባው ፖለቲካ፣ህልም የሌለው ከራዕይ የራቀ የማያስተውል፣በህዝቡ ጭንቀትና ሠላም ማጣት የሚደሠት መንግስት የጨለማ ዘመን ፣ግራ የገባው ፖለቲካ ከራእይ የራቀ ፈች ያጣ፣ በቅዠት የተሞላ ህልም፣ግን ይህች ሀገር መች ይሆን ህዝቧ በአንድነቱ አምኖ ፣በአራቱ አቅጣጫ የሚኖረው ነዋሪ በሠላም ተረጋግቶ፣ለአንድነቱና ለሀገሩ ተቆርቋሪ ዜጋ ሆኖ የሚኖረው ..
በፖለቲካው አለም የሚኖሩት ዜጎች ሁሌ በውጥረት ፣በወንበር ጥማት በግዞት በምቀኝነት፣በእርስ በርስ ጦርነት፣በብሔር፣በቋንቋ በቀለም፣በዘር ክፍፍል…ዳግማዊት ባቢሎን..በይምሠል መኖር፣ጉራ ብቻ…የእፍኝት ሽንት፣የራስ እዳ ለራስ ቀሎ መገኘት…በቃ ይህ ነው የዜጎቿ ጩኽት፣ይህ ነው ዝማሬአቸው..የመጣ የሄደው ሲተካካ አጨብጭቦ መቀበል..
ወኔውንና ማንነቱን የተነጠቀ ህዝብ፣ታሪክ አጥፊ ትውልድ፣በአጉል ሙገሣ የሚኖር፣ራሱን እየዋሸ እየሸነገለ የሚኖር አስመሳይ ትውልድ፣በቃ..ይህ ነው የሀገሪቱ እጣ ፋንታ..ሁሌ ጦርነት፣ሁሌ የልጆቿን ደም የምትጠጣ ምድር፣ሠላም የናፈቀች ሀገር..ለነገሩ በዚያ የበኩር ልጅሽ የቤትሽ ዋልታ፣ዋስ ጠበቃሽ በሆነው ብቸኛው አሣቢሽ የኃይሉ ልጅ ፣የታጠቅ ጌታ የነበረው የካሣ ሀዘንና ርግማን ገና ሌላ ያሣይሻል..እውነቱን ነው ንብረትሽን ሊሠበስብ፣ልጆችሽን ሊያፋቅር፣የአንድነት መዝሙር ሊያዘምር፣ከጎረቤትሽ በላይ ሊያደርግሽ፣ከብሮ ሊያስከብርሽ፣ከአያቶቹ በአደራ የተረከበውን ድንበርሽን ከልሎ ሊታደግሽ፣ኮርቶ ሊያኮራሽ፣ባሠበ፣መገነጣጠልን ኮንኖ ስለ አንድነትሽ ባዜመ፣ለህዝቡም ባስተማረ፣ጭንቅ የወረሳቸውና ስጋት ውስጥ የገቡት የውጭ ሃይሎች ፊት ለፊት ከእርሱ መቅረብ ቢፈሩ በወንድሙ ገቡበት የይሁዳ ታሪክ በወንድሙ ተፈፀመ.. ይሁዳስ ጌታውን ቢሸጥ በገንዘብ ነው፣
ካሣ አልደራደር ያለው ግን መሣሪያውን መስሪያ እንጅ የተሠራውን መቀበል ኮንኖ ነው…
ወንድሙ ግን እርሱ በኮነነው ብረት አሣልፎ ሸጠው..
ሁለቱ ቢያልፉም ታሪክ ያወድሳል ታሪክ ያስወቅሣል..የታጠቅ ጌታ ግን ሁሌም ለክብርሽ ነዋሪ ነውና ወንድሙ በሠራው ግፍ አዝኖ፣የመጭውን ትውልድ የዘር ሃረግ አምርሮ ረግሞ፣ስሜቱን ተናግሮ ፍቅሩን ሊገልፅልሽ ፣ክብርሽን አሳልፎ ከሚሠጥ ህይወቱን ሠጠልሽ፣በደሙ ከብሮ አስከበረሽ ..
በጭንቅላቱ ላይ የሰደደው ጥይት በንፁህ ሰው ላይ ስላረፈ ዜማውን እያዜመ ሁሌም በላይሽ ላይ ያንዣብባል..
የደሙ ጩኽትም ሳያቋርጥ ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋል ..እርሱን መሣይ እስክታገኝ ድረስ የራስሽ ጠላት የራስሽ ልጅ ሆኖ ይነሣብሻል..እርስ በእርስ መገዳደል፣እርስ በእርስ በመጨራረስ የሄደ የመጣው ሌላ ጩኽት የሌለው በመሆኑ ምክንያት ያለሽን ሀብት እንኳ ዜጎችሽ መጠቀም ስላልቻሉ በስደት አለምን ሞልተዋታል ..
በዚህ ዘመን እንኳ የተፈጥሮ ሀብትሽን አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስብ ዜጋ ታሪክ ሠርቶ ለማለፍ የሚያስብ አንድም ሰው ይጥፋ..ይህ ትውልድ ዝማሬው ባርነት፣ስደት፣ራሱን ረስቶ ሌሎችን መምሰል ርካታና ደስታ የሚሰጠው፣ውርደትን መጎናፀፊያው ያደረገ ፣በወሬና በጉራ፣በንጥቂያና በዝርፊያ የተሞላ ብቻ…
ያም መጣ ነገሠ ተቀያየረ ከ 20 አመት በላይ ሲገዛ ትውልዱን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ ቂምና በቀልን ከማስተማር ውጭ ወረቀት ላይ ከከተበው የቃላት ድርደርራ ውጭ የአንድነት ዝማሬ ያዜመበት ገጠመኝ የለውም..
እርሱንም የሚጥለው እስኪያገኝ ድረስ ዜማውና ቅኝቱ በወንድሙ ላይ ስለ ተቀዳጀው ድል ..አይ አንች ሀገር መጨረሻሽ ምን ይሆን…
Filed in: Amharic