>

ኦህዴድና ብአዴን በኋላ አልሰማንም እንዳትሉ "የፖለቲካ ሽብልቅ" በጣም አስፈላጊ ነው!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

ኦህዴድና ብአዴን በኋላ አልሰማንም እንዳትሉ “የፖለቲካ ሽብልቅ” በጣም አስፈላጊ ነው!!!
ቬሮኒካ መላኩ
ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ጉዞ ምክንያታዊ ደጋፊ እንደመሆኔ የሚከተለው የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ እንድደረግ እመክራለሁኝ።
የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ፣ የህውሃት መአከላዊና ፖሊት ቢሮ አባል ገብሩ አስራት ብዙ የህውሃትን ነውር እና እውነት የተዘከዘከበት ግብዴ  መፅሀፍ  ያነበበ  ማንኛውም ሰው ለምን የህውሃትን  ወደ ኢሳያስ አፈወርቂ ቀረብ ቀረብ  ማለትና  መጠጋጋት አጥብቄ እንደምቃወም ይገባዋል ።
የገብሩ አስራትን መፅሀፍ ከገፅ 1 እስከ ገፅ 200 አካባቢ የተፃፈውን  በጥቂት መስመር አሳጥሬ ስከልሰው እንደዚህ ይላል ።
 ” ከ 1983 ጀምሮ  እስከ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት አብቅቶ ህውሃት ለሁለት እስከሚሰነጠቅበት ድረስ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ አገር የሚያደርጉትን ድርድር የሚወስኑት ህውሃትና ሸአቢያ በፓርቲ  ደረጃ ብቻ ተሰብስበው በወሰኑት ውሳኔ መሰረት ተደርጎ ነበር ። በዚህ ወቅት ብአዴንም ፣ ኦህዴድም ሆነ ዴኢህዴን ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ጦርነት እንኳን ሲታዎጅ መጀመሪያ የተወሰነው በህውሃት ብቻ ነበር ። ሌሎቹ ፓርቲዎች ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እኩል ነበር የሰሙት ።”  ይላል።
ትናንት ደብረፂዮን ተሹለክልኮ ገብቶ ለደቂቃ  አቻዊ ያልሆነ   የመጀመሪያ ሙከራ አድርጓል ።  እርግጥ አሁን የኢህአድግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዳይናሚክስ ተቀይሯል ። ነገር ግን አንድ ሁሌም መሰመር ያለበት ጉዳይ አለ። ይሄውም
ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው ማንኛውም ግንኙነት በጣም ፍሬ የሚያፈራውና ለሁለቱም አገሮች ጥቅም የሚያስገኘው በTPLF እና በ EPLF መካከል የሚለያይና ፓርቲ ለፓርቲ እንዳይገናኙ ሀይለኛ  የፖለቲካ ሽብልቅ መሀል ላይ ከቀረቀርክ ብቻ ነው ።
 አቢይ ይሄን ስትራቴጅ ካለተከተለና ሌላውን በፍቅር እንደሚደምረው ሁለቱን ፓርቲዎች ተደማመሩ ብሎ ከተዋቸው ውጤቱ አደገኛ ነው።  ይሄ ምክር ለአቢይ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው ።
በተረፈ ከአሁን በኋላ   ድንበር የሚባል አያስፈልገንም ፣  የሚለው ነገር ብዙም አያስማማኝም። አንዱን ሽብልቅ የምታስቀምጠው ችካል ተቸክሎ ሁለቱን አገሮች የሚለየው ድንበር ድማርኬት ሲደረግ ብቻ ነው።  በተረፈ ገብሩ በመፅሀፉ እንደነገረን ኢሳያስ በሳምንት  ሁለት ቀን ላንድሮቨሩን ራሱ እያሽከረከረ መቀሌ ከች ይልና ከህውሃቶች ጋር ተሰብስቦ ኢትዮጵያን በተመለከተ ብዙ ስምምነቶችን ፈፅሞ  በተግባር ውለዋል።
በመጨረሻ ዶ/ር አቢይ ፣ኦህዴድ ፣ ብአዴን በኋላ አልሰማንም እንዳትሉኝ የፖለቲካ ሽብልቅ በጣም አስፈላጊ ነው።
Filed in: Amharic