>

አፄ ሚኒሊክ እና ጡት... (በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

አፄ ሚኒሊክ እና ጡት…
በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
አፄ ምኒልክ ደም መፈሰስን እናስቀር ብለው ንጉሥ ጦናን ለመኑት። ንጉሥ ጦና ግን ሉን አሟጦ መዋጋት ስለመረጠ በምኒልክ ሠራዊት ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰ። በመጨረሻ ግን ቆሰለና ተማረከ። ዳግማዊ ምኒልክ ጦናን አይቀጡ ቅጣት ከመቅጣትና መንግስቱንም አሽቀንጥረው ጥለው ሥልጣኑን ለጦር መሪዎቻቸው ከመስጠት ይልቅ ደግነት የተሞላበት ምህረት አድርገውለት እንደሚገብርላቸው ቃል ካስገቡት በኃላ ወደ ሥልጣኑ መለሱት። ምኒልክ ተበቃይ አልነበሩም። ይቅር ባይ፣ በተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሰረተ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የነበራቸው እና ራሳቸውን እነደ ጥሩ ክርስቲያን የሚያዩ ሰው ነበሩ። በጦርነት ላይ የሴት ልጅ ጡት መቁረጥ ፍጹም ከባሕሪያቸው ውጪ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ውንጀላ መሰረተ―ቢስ እና ከተንኮለኞች የመነጨ ነው።
የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አምጸው ጦርነት አነሱና ቆስለው ተማረኩ። ምኒልክ የቆሰለውን ምርኮኛ ገድሎ በመጨረስ ፈንታ ቁስላቸውን ራሳቸው አክመው ፣ አጠገባቸው አስቀምጠው አብረዋቸው እንዲመገቡ በማድረግ ፍቅር ነው ያሳዪአቸው። ሥልጣናቸውንም አልወሰዱባቸው፤ ያለማመንታት መልሰውላቸዋል። በርግጥ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሩኅሩኅ ነበሩ። አገራቸውን ለመውረር የመጡ ምርኮኞች ጣልያኖችን እንኳ በርኅራኄና በደግ አያያዝ ነበር የያዟቸው። እኝህን ሰው ጡት ቆርጠዋል/አስቆርጠዋል ብሎ መፈረጅ አግባብነት የሌለው ትንሽ የፓለቲካ ጠቀሜታ ለማግኘት የሚነዛ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ነው። ምኒልክን ጡት ቆርጠዋል ብለው ለማስጠላት ሀውልት ያቆሙ አካላት በድርጊታቸው ማፈር እና ያንን አሳፋሪ ሀውልትም ማፍረስ ይገባቸዋል። ምኒልክ በግላቸው እንደዚያ ዓይነት ተግባር ጨርሶ አይፈጽሙም።
የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
ገፅ፦ 152 – 153
Filed in: Amharic