>
5:21 pm - Tuesday July 21, 7643

ለአማራ የሚጠቅመው የሚኒስትር ብዛት ወይስ ጥራት?  (ቹቹ አለባቸው)

ለአማራ የሚጠቅመው የሚኒስትር ብዛት ወይስ ጥራት? 
ቹቹ አለባቸው
አሁን አሁን ወዳልሆነ ነገር እንዳንገባ እፈራለሁ። ኦህዴድ ስልጣኑን ጠቀለለው; ብአዴን አሰበላን ወዘተ…። እውነት ነው ኦህዴድ ቲንሽ ሆድ የማስፋት ነገር ታይቶበታል። አንድ ነገረ ግን ተስፋ አለኝ; ብአዴን ኦህዴድን ነገሯን እንካፈላት ካለዉ ኦህዴድ እንደ ህውሀት አያስቸግርም። ኦህዴድም እስኪ ቆምም ብለህ እየው። ያም ሆነ ይህ አማራና ኦሮሞ በስልጣን መጣላት የለብንም; ለሁለቱ ህዝቦች ነውር ነው።
ሰለሆነም እኔ እንደማምነው;
1. አማራ በቁመናው ልክ አዲስ አበባን ጨምሮ ውክልና ማግኘት አለበት የሚለው ጭብጥ ለክርክር አይቀርብም።
2. የአማራ ጥቅም የሚረጋገጠው ጥራት ያለዉ ድርጅትና ብቁ ካቢኔወች ሲኖሩት እንጅ 100 ካቢኔ ስላለዉ አይደለም። በትምህርት ስርአቱ አማራ እንዲያ ሲጠቃ ሚኒስትሮቹ እነማን ነበሩ? አማራን ከሱዳን የለየዉ ካርታ ስራ ላይ ሲዉል እነማን ነበሩ? የወልቃይት ኮሚቴ ሰሚ ሲያጣ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሀላፊ እነማን ነበሩ? ከዚህ ምን እንማራለን?  ” መቶ ቢወለድ መቶ ነዉ ጉዱ የነፍጠኛ ልጅ ይበቃል አንዱ” የምትለዉን ነጥብ ጠበቅ እናድርጋት።
3. አዲስ አበባ የማን ናት? አ.አ የአዲስ አበቤወች ነበረች ግን አልሆነችም። ሽኩቻ በዝቶባታል። ባለቤቱ ህዝብም ሌሎች በሱ ላይ ሲያላግጡ እያየ በትዝብት ይመለከታል። ኢህአዴግን ሊበቀልም ቀን እየጠበቀ ነዉ። አዲስ በቀጣዩ ምርጫ ከኢህአዴግ እጅ ወጥታ በነዋሪወቿ እጅ ትወድቃለች። ከዚያ በሁዋላ ከኦሮሚያ ;  ከትግራይ ; ከአማራ; ከደቡብ ዘማች እያመጡ አዲስን  መግዛትና ማስገዛት ያቆማል።
4.  አማራ ቁልፍ ቦታ አጣ የሚባል ነገርም እሰማለሁ። ይህ ነገር በተለይም ጠሚ ከመሆን እና የአዲስ ከንቲባ ከመሆን ጋር ይያያዛል። እኔ ደግሞ የአማራ ወንድም እህቶቸ የፈለገ ተቆጡኝ እንጅ በአሁኑ ወቅት አማራ የጠሚ እና የአዲስ ከንቲባ እንዲሆን በፍጹም አልፈልግም። ዶ/ር አንባቸው የአዲስ ከንቲባ ቢሆን ኖሮ ከሱ ጋር ሁኜ የጀመረኝ የጨጓራ በሽታ ይብስብኝ ነበር። ወገኖቸ በአሁኑ ወቅት እነዚህን ሁለት ቦታወች ለአማራ አትመኟቸዉ። ቦታውን ከያዙት በሁዋላ ችግር አለ። በዚህ አጋጣሚ ወንድሜ ዶ/ ር አንባቸዉ መኮንን እንኳን ከተወራብህ መከራ አተረፈህ  እልሀለሁ።
ሁላችንም እንደምናውቀዉ እኛ  አማራወች  ገና የዉስጥ የቤት ስራ አለብን ቅድምያ ውስጣችንን እናጠንክር ። እስኪ ቅድምያ የተሟላ ቁመና ያለዉ; አማራን የሚመስል  የክልል አመራር ይኑረን። እስኪ መጀመሪያ መላ የአማራ ወጣቶች የሚሳሱላቸዉ ከ5-10 ብርቅየ አመራሮች ይኑሩን።
ሳጠቃልል—- አማራ ተገቢ ዉክልና እንዲኖረዉ የኔም ፍላጎት ነው። ነገር ግን የአማራን እዉነተኛ ዉክልና አመላካቹ የካቢኔ ምናምን ቁጥር መብዛት ሳይሆን የተወካዮቻችን ቅመም ወይም ዱባ የመሆን ጉዳይ ነዉ። አማራ  20 ዱባ ተወካይ ከሚኖረው 2 ቅመም ተወካይ ቢኖረዉ አመርጣለሁ”። ነገሮችን እንዲህ እንያቸዉ።
የአዲስ ነገር ህግ እየተረጋገጠ ሲመጣ ለባለቤቱ ትሰግዳለች። እስከዛ ግን ያለዉን ተቀብለን ይልቁንስ ቡዙ የሚሰራ ስራ ስላለ እንወቅበት። አንዳንዴም አንድን ነገር ከምታገኘዉ ባታገኘዉ እንደሚሻል ማሰብ ጥሩ ነዉ።
መቸም ይህ ሰውየ ዛሬ አብዷል ነው የምትሉኝ። እኔ ግን ከምሬ ነው። አማራ በአሁኑ ወቅት ጠሚና የአ.አ ከንቲባ ባለመሆኑ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ፋሲሲል ደሞዝ ምኑ ታይቶት ነዉ”  ዘንድሮ አለ ነገር ” ሲል ያዜመው ? እኔስ አሁን ላይ ደርሽ አማራ ጠሚ እና የአ.አ ከንቲባ ቦታን አለመያዙ መገፋት ሳይሆን መታደል ነዉ የምለዉ ለምንድን ነው?
 እናስተውልና የቤት ስራችንን እንስራ። ቡዙ ያልከወናቸዉ ነገሮች አሉ።
Filed in: Amharic