>

አባ ኮስትር በላይ!!! (አሰፋ ሀይሉ)

አባ ኮስትር በላይ!!!
አሰፋ ሀይሉ
* ‹‹በመኺናው መንገድ፥ መኺናው ዘለቀ፤
አሁንም ቅደምም፥ ያ በላይ ዘለቀ!!!››
— ዜማ-ስንኝ፡- ትዕግሥት ሽባባው፤ የእጅጋየሁ ሽባባው (የጂጂ) እህት
* ‹‹ከዓለሙ ሁሉ መሐል ፥ የሀገሩን ታሪክ ለይቶ የማያውቅ፣  ከብዙ ሴቶች መሐል፥ የገዛ እናቱን መለየት እንደሚያቅተው ሕጻን ነው፡፡››
— የካቴድራሉ የታሪክ-ምሁር፣ ወዳጄ ቴዎድሮስ አካሉ
እነሆ አባ ኮስትር በላይ በ6 ነጥብ
1) ቤተሰብን ማጣት፣ ልጅን መቀማት — ስለ ሀገር፡-
‹‹…በላይ ዘለቀ ሊወጋቸው የመጣውን የኢጣሊያ ጦር ከመመከት አልፈው ድልን በድል መቀናጀት ዋናው መለያቸው እየሆነ መጣ። ሁሌም አሸናፊ ሆኑ። የኢጣሊያ ጦር ሁሌም እየተሸነፈ በመሄዱ ተስፋ በመቁረጥ የበላይ ዘለቀን ባለቤት ወ/ሮ ሸክሚቱ አለማየሁን እና የባለቤታቸውን እህት ወ/ሮ ዘውዲቱ አለማየሁን ገድሎ ልጃቸው ወ/ት የሻሽወርቅ በላይን ማርኮ ሄደ። ከዚህ በኋላም የበላይ ዘለቀ እልህም እያየለ በመምጣት ብዙ ባንዳዎችን እና የኢጣሊያ ወታደሮችን ድል አደረጉ።
2) የደብዳቤ ልውውጥ — ልጅን ካገተ ጠላት ጋር፡-
‹‹በመጨረሻም የኢጣልያ ገዢ ከበላይ ዘለቀ ጋር ታርቆ፣ ሠላም ፈጥሮ መኖር ፈለገና የሚከተለውን መልዕክት ላከላቸው።
‹‹ “ይድረስ ለልጅ በላይ ዘለቀ። ለኢጣሊያ መንግስት ብትገባ ጥቅም እንጂ ጉዳት አያገኝህም። ጐጃምን በእንደራሴነት ይሰጥሃል። ስለዚህ በሰላም ግባ የኢጣሊያ መንግስት መሀሪ ነውና በአጠቃላይ ሙሉ ምህረት ያደርግልሃል” የሚል ነበር። በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ይህንን የኢጣሊያ ደብዳቤ በሰሙ ጊዜ ለተፃፈው ደብዳቤ መልስ ሲፅፉ እንዲህ አሉ፡-
‹‹ “ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፣ ከሁሉ አስቀድሜ ሁልጊዜ ሰላም ላንተ ይሁን እያልኩ የማክበር ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ከሰላምታዬ ቀጥዬ የምገልፅልህ ነገር ቢኖር ከኢጣሊያ መንግሥት የተፃፈልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል። በአክብሮት ተቀብያለሁ። ተመልክቸዋለሁ። በደብዳቤው ላይ ያለውን ቁም ነገር ያዘለ ቃል ስመለከተው እጅግ በጣም የሚያስደስት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ልጄን ከመለስክልኝ ጐጃምን ያህል ሀገር በእንደራሴነት ከሰጠኸኝ ከዚህ የበለጠ ሌላ ምን እፈልጋለሁ። ስለዚህ የኢጣሊያ መንግስት የሚያምናቸውን ታማኞቹን ይላክልኝና በእነሱ አማካኝነት አገባለሁ” የሚል ደብዳቤ መልሰው ፃፉለት።
3) ክዳትን ያነገቡ ሽማግሌዎች — የአርበኛ ኃጥያት ስለ ሀገር
‹‹በዚህን ጊዜ የኢጣሊያን መንግስት የበላይ ዘለቀን ደብዳቤ እንደደረሰው ሲመለከተው አስደሳች ሆኖ ስለአገኘው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታሎ በእጁ ለማስገባት የዘወትር ምኞቱ ስለነበር በጉጉት ይጠብቀው የነበረው ሃሳብ የተሳካ መስሎት የራሱ የፍርድ ቤት ዳኞች ሆነው በታማኝነት ሲያገለግሉት የነበሩትን፣ በኢትዮጵያዊያን ወገናቸው በአርበኛው ላይ ይሰቀል ይገረፍ እያሉ ሲፈርዱና አርበኛ ያለበትን ቦታ ሲጠቁሙና መርተው በማሳየት ይረዱ የነበሩትን ታማኞችን እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማንና እነ ቀኛዝማች አደራው የተባሉትን ከነ አስተርጓሚ ጭምር ሆነው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታለውና አባብለው በእጁ እንዲያስገቡለት ላካቸው።
‹‹…በአስታራቂነት የመጡት እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ አትፍረድ ይፈረድብሃል እንደተባለው ሁሉ እነሱ በሌላ ሲፈርዱ ኖረው በእነሱ ላይ ይግባኝ የሌለው የአርበኛ ፍርድ በማግኘት ፅዋው ስለደረሳቸው በጥይት ተረሽነው በዛፍ ላይ ተሰቀሉ።
4) ልጅን ያህል ነገር ‹‹ያሻህን አድርጋት፣ እዝጌር አላት!›› — ስለ ሀገር
‹‹ከዚያም በኋላ ጀግናው በላይ ዘለቀም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢጣሊያ መንግሥት ፃፈ፡-
‹‹ “ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ የላክልኝን እንግዶች እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማን በአክብሮት ተቀብዬ በማስተናገድ ሥፍራ ወይም ቦታ ሰጥቻቸዋለሁ። ላንተ ግን ትርጁማን (አስተርጓሚ) ብለህ የላከውን ሌላ ቦታ ስትልክ እንዳይቸግርህ ልኬልሃለሁ። ልጅህን እመልስልሃለሁ ለምትለው ለአንድ ልጅ ብዬ እናት ሀገሬን ኢትዮጵያን ከድቼ ከአንተ ጋር በእርቅ መልክ አልደራደርም። ከዛሬ ጀምረህ በእኔ በኩል ያለውን ምኞትህን አንሳ። እኔን ፈልገህ ማጥፋት እንጂ አንዲት ልጅ ወስዶ ማስጨነቅና ማጉላላት ደስ የሚልህ ከሆነ እንደፈለክ አድርጋት። ሲሆን ለሷም የፈጠራት አምላክ እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ ከአንተው እጅ ላመጣት እችል ይሆናል። ጐጃምን በእንደራሴነት ልስጥህ ለምትለው አንተ የሰው ሀገር ሰው ከምትሰጠኝ እኔው ሀገሬን በሥሬ አድርጌ አስተዳድረው የለም ወይ? ስለዚህ የፖለቲካ ወሬህን ከምትነዛና የኢትዮጵያን አርበኛ እየቆማመጠ ለአሞራ በመስጠት በየዱር ገደሉ ወድቀህ ከመቅረት በመጣህበት መንገድ አገርህ ከመግባት በስተቀር አማራጭ የሌለህ መሆንህን በዚህ አጋጣሚ ልነግርህ እወዳለሁ”
‹‹ሲሉ በላይ ዘለቀ ለኢጣሊያ መንግሥት ደብዳቤ ልከዋል። ….ኋላም የተማረከችውን ልጃቸውን የሻሽወርቅን እንደገና ተዋግተው ከኢጣሊያኖች እጅ ከነህይወቷ ለመማረክ ችለዋል።››
5) ቀን ሲጎድል ‹‹ሰው ማለት!›› — የአርበኞች ግጥሞች — ስለ ሀገር፡-
‹‹… በላይ ዘለቀ ታማኝ አሽከሮቻቸውን ይዘው አባይ ለአባይ እየተዘዋወሩ በሚዋጉበት ጊዜ አብረዋቸው ያሉ አሽከሮቻቸው አርበኛውን ከድተው ለጣሊያን በገቡት ጓደኞቻቸው ላይ እንዲህ ሲሉ የእንጉርጉሮ ግጥም ገጠሙላቸው፡-
‹‹ይህንን አንበሳ ጀግናውን ከድታችሁ
ኧረ ተምን ግዜው ለጣሊያን ገባችሁ
በጣም ያሳዝናል ባንዳ መባላችሁ
ከከዳችሁ አይቀር ጀግናውን ከድታችሁ
እምትወዱት ጣሊያን እሱ ካዋጣችሁ
ልቅምቅም አድሮርጐ ከነጫጩታችሁ
እትውልድ ሀገሩ
እሮም ይውሰዳችሁ።
‹‹እኛ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ባንዲራ
እንታገላለን በጭብጥ ሸንኮራ።
አባይ ከጨረቻው ወድቀን እንደ ገሣ
አንድ ጭብጥ ጥሬ ይዘን በኪስ ቦርሣ
ይኸው አሁን አለን ሳንጠቁር ሳንከሣ።
‹‹ጥንት ባባቶቻችን ታፍራና ተከብራ
እንዴት በኛ ጊዜ ይውረራት አሞራ
ይህ ነጭ አሞራ ቢሽኮበኮብ ቢያልፍ
አንሰጥም ኢትዮጵያን ህይወታችን ቢያልፍ፡፡››  እያሉ ተስፋቸውን ባለመቁረጥ ትግላቸውን ቀጠሉ።
6) ስንብት — ‹‹ሕብስት ላበደረ እበት፣ 
ልጅን ላበደረ ስዕለት›› — ስለ ጀግና ሰው ክብር፡-
‹‹…በመጨረሻም በማጎንበስ ሳይሆን እንደ አንበሳ ደረቱን በመንፋት፤ ከፍ ባለ የስነልቦና የበላይነት፤ እንደ ንስር አይን በሚወጉ አይኖቹ ዙሪያ ገባውን እየቃኘ በፉከራና በቀረርቶ ወደ ተዘጋጀለት ገመድ አመራ፤ “አንች አገር ወንድ ልጅ አይብቀልብሽ!!!” ብሎ የወንድ ቁናው በላይ ዘለቀ ከወንድሙ እጅጉና ከሌሎች አርበኞች ጋር በጥር 4 ቀን 1938 ዓም አዲስ ከተማ ላይ ተሰቀለ።››
— ምንጭ (እጅግ ከከበረ ልባዊ ምስጋና ጋር)፡-
•‹አባ ኮስትር›፤ በአበራ ጀምበሬ፤ ኩራዝ አሣታሚ
Filed in: Amharic