>

አጀንዳ በተወረወረልን ቁጥር መንጫጫቱ አይረባንም !!! (በፍቃዱ ሞረዳ)

አጀንዳ በተወረወረልን ቁጥር መንጫጫቱ አይረባንም !!!
በፍቃዱ ሞረዳ
መንግሥት ሆኖ ኢትዮጵያን እየገዛ ያለዉ ‹‹ኢሕአዴግ ›› የሚባል ፓርቲ (ድርጅት) ነዉ፡፡ ‹‹ ሕዝቡ ሥልጣን ሠጥቶኛል፤100% መርጦኛል›› ብሎ፡፡ እና ‹‹ ኢሕአዴግን ከዉድቀት አድነዋለሁ፤ጥገናዊ ለዉጥ አድርጌ እንደገና ሕይወት እዘራበታለሁ›› ያሉት የፓርቲዉ ሊቀመንበር ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ የድርጅቴን ፍላጎት ያስፈፅምልኛል፤ ጥቅማችንን ያስጠብቅልናል…›› ብለዉ የሚያምኑበትን ሰዉ ቢሾሙ እኔ ምን ጨነቀኝ?
   ሰዉ ጨርሶ በኢሕአዴግ አገዛዝ ሥር መሆኑን ረስቶት ይሆን በገብርዔል? ወይስ እኒህ አብይ የሚባሉት ጉደኛ ሰዉ ሀገሩን በሙሉ በኢሕአዴጋዊ ጠበል ጠምቀዉት አረፉ?
  ‹‹ ኢሕአዴጉን አስታጥቄን፣ ኢሕአዴጉን ዘበርጋን፣ ኢሕአዴጉን ሀጎስን፣ ኢሕአዴጉን ጆኒን (ጭሱን አዲስ አበቤ) …መሾም ሲገባህ ለምን ኢሕአዴጉን ታከለ ኡማን ትሾማለህ? ›› ተብሎ ነዉ እየተጠየቀ ያለዉ?
  እንዲያዉ ያልተረዳሁት ነገር ከሌለ በስተቀር እስከሚቀጥለዉ ምርጫ ድረስ ገዥዉ ኢሕአዴግ ነዉ፡፡ ወደድንም ጠላንም፡፡ ይልቁንስ ‹‹ ሜዳዉን ለሁሉም ነፃ አድርግልን፤ የሚበጀንን የመምረጥ መብታችንን ጠብቅልን፤ በመረጥነዉም ለመተዳደር እንችል ዘንድ ምቀኛ አትሁንብን …እስከዚያ ግን የፈለከዉን ሹም ፣ ያልፈለከዉን ሻር›› እያሉ መደራጀትና መዘጋጀት ነዉ የሚሻለዉ? ወይስ  ለኢሕአዴግ ሹም መራጭ እየሆኑ ጉንጭ ማልፋት፣ጊዜ ማጥፋት፣ ከበሮ መደለቅ፣ በሂሮ ( ቄሮ ለማለት ፈልጌ አይደለም) መደነቅ ነዉ ደጉ?
  ነፃ ምርጫ ተካሂዶ ያኔ ኢሕአዴግን የምንመርጥ ከሆነም አገልጋያችን ነዉና፣ ‹‹ እንዲህ ለምን አደረግህ?››ብለን ለመገሰፅ ሥልጣንም፣ ሞራልም ይኖረናል፡፡
    ስለሀገሩ መጪ ዕድል የሚጨነቅ ዜጋ ሁሉ ከዚህ ሆሆሆይታ ስካር ወጥቶ የተረጋጋ ሥራ መሥራት ቢችል ይሻለዋል፡፡ በዲሞክራሲ የምናምን ከሆነ ስለዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታና መጠናከር መሠራት ያለበትን ሥራ አሁን መጀመር ግዴታችን ነዉ፡፡ እንደዜጋም በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ዉስጥ ተሳታፊ መሆን የምንፈልግ ከሆነ በመደራጀትና ማደራጀት ሥራ ላይ ማተኮር መቻል አለበት፡፡በተፈጠረዉ አጋጣሚና ቀዳዳ ተጠቅሞ፡፡
     የአንድ ሀገር ሕዝብ የፖለቲካ ጉዳዮች ብቻ አይደለም ደንታዉ፡፡ ስለኢኮኖሚ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ስለማኅበራዊ ጉዳዮች መስራት የግድ ይላል፡፡
   እርግጥ አደባባይ ላይ ወጥተዉ የማይለፈልፉ፣ በመሬት ላይ የሚታይ ሥራ በመሥራት ላይ የተሰለፉ አያሌ ዜጎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ግን የጫጫታዉ ካምፕ ‹‹ጢም! ›› ብሎ የሞላ ይመስላል፡፡በእርግጥ እኔም ከገበያዉ መሀል ነኝ፡፡ እገዛዉ፣ እሸጠዉ ባይኖረኝም፡፡
 ከጫጫታዉ መቀነስ ፣ ወደሁሉን ተኮር ኅሊናዊና ቁሳዊ ግንባታ መቀልበስ ይበጃል፡፡ ከጫጫታዉ ትርፍ የሚያገኝ ካለ ግን እዚያዉ ይፅና፡፡ ከትርፉም ያካፍለን፡፡
 ለማንኛዉም ‹‹ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› ያለዉ የግርክ ፈላስፋ ማነዉ?
Filed in: Amharic