ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
የሰሜን ሱዳን የቆዳ ስፋት 1,886,068sq kms ነው፡፡ ይሄም ማለት የእኛን ማለትም 1,221,900sq kms የሆነውን የሀገራችንን የቆዳ ስፋት አንድ ከግማሽ የሚያክል ማለት ነው፡፡
የሕዝቧ ቁጥር ደግሞ 41.51 ሚልዮን ነው፡፡ ይሄም ማለት ከእኛ ማለትም 100 ሚሊዮን ከሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር ከግማሽ በታች ያነሰ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ይታያቹህ ከእኛ ከግማሽ በታች የሆነ አነስተኛ ሕዝብ ይዛ ከእኛ ሀገር የቆዳ ስፋት በእጅጉ የሚልቅ ሰፊ ሀገር ይዛ እኛን በሕዝብ ብዛት የተጨናነቅነውን ሀገር “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል!” እንዲሉ ከከሀዲው ከወያኔ ጋር ተስማምታና ሰፊ መሬታችንን ተቀብላ ወገኖቻችንን እያፈናቀለች እያሳደደች እየገደለች አላሳርስ አላስገባ አላስወጣ ካለች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ሱዳን ውኃችንን በነጻ መጠጣቷ ሳይከብዳትና ጥቂት እንኳ ይሉኝታ ሳይሰማት መሬታችንንም ለመንጠቅ ጥረት ማድረጓ ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና በአባቶቻችን ዘመን ጀግኖች አባቶቻችን ግብጽንና ሱዳንን ለሚጠጡትና ለሚያዘምሩበት የዓባይ ውኃ በየዓመቱ በርካታ የወርቅና ብር ግብር እንዲከፍሉ ያደርጓቸው ነበረ፡፡ የዛሬው የወያኔ አገዛዝ ደግሞ እንኳንና ለውኃችን ሊያስከፍል ይቅርና ጭራሽ መሬቷን አሳልፎ በመስጠት የሀገር ክህደት ፈጽሞብናል፡፡
በቦታው ያለው ወገናችን እስከ አሁንም ተነግሮ የማያልቅ መሥዋዕትነት እየከፈለ የወሰዱትን መሬት ተረጋግተው እንዳይጠቀሙበትና የራሳቸው አድርገውት እንዳይቀሩ ማድረግ ቢችልም የያዘው መሣሪያ ቀላል መሣሪያ በመሆኑ ከባባድ የጦር መሣሪያ የያዘውን በሜካናይዝድ የተደራጀውን የሱዳንን ሠራውት ማስለቀቅ አልቻለም፡፡
የወያኔ አገዛዝ መሬቱን የሰጣቸው እሱ ራሱ በመሆኑ ያስለቅቃቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አሁን ግን እነዐቢይ እነገዱ ወያኔንና የፈጸማቸውን ክህደቶች እየኮነኑ በመሆኑ በቦታው ያለው ወገናችን ያለበትን ችግርና የድንበር መደፈር እያወቁና እየሰሙ እንዳላወቁና እንዳልሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውን ብናውቅም ማስጨረስ ይኖርብናልና የሚሉት ነገር እውነት ከሆነ ሱዳን እሽ ብትል ውኃችንን በነጻ መጠጣቷን በማስገንዘብ፣ ይህ ድርጊታቸው ለወደፊቱ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነትና ለራሳቸው ጥቅም ፈጽሞ የማይጠቅማቸውን የደንቆሮ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን በማስገንዘብ፣ የሀገራችን መንግሥታት መዳከም ተከትሎ ያቋረጡትን ግብር ክፈሉ ቢባሉ ሊኖርባቸው የሚችለውን የዕዳ ቁልል በማሰብ ትንኮሳዋን እንድታቆምና መሬታችንን እንድትለቅ በዲፕሎማሲ (በአቅንኦተ ግንኙነት) ካልተቻለና ይሉኝታና ውለታቢስ ከሆኑ፣ አዙሮ ማየትና አርቆ ማሰብ የማይችሉ ከሆኑ ደግሞ በሚገባቸው ቋንቋ በማናገር እነዐቢይ እነገዱ በሱዳን ጦር አሳሩን እያየ ያለውን ወገናችንን በመታደግ ዳር ድንበራችንን በማስከበር ከወያኔ ከህደት የተለዩ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ፣ ይሄንን የሕዝብና የሀገር ግዴታ መወጣት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ፈጽሞ ሕዝብን የሚወክሉ ሀገርን የሚጠብቁ አይደሉምና ሥልጣንን ለሕዝብ እንዲያስረክቡ በታላላቅ ሰልፎች ጭምር መጠየቅ ይኖርብናልና ለዚህ እንትጋ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!