>

ጂጂ ና የሀገር ፍቅሯ!!! (ተወልደ በየነ - (ተቦርነ)

ጂጂ ና የሀገር ፍቅሯ!!!
ከተወልደ በየነ (ተቦርነ)
ስለ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)  አስተዳደግ ያካባቢዋ ልጅ ሆኜ መመልከት ባልችልም በ “ናፈቀኝ” ዘፈኗ የልጅነት ሕይወቷን መቃኘት አልቸገርም ።አንዷ አክስቷ አንድ ስም ሲያወጡላት ፣ሌላኛዋ በሌላ ሲጠሯት ፣አንድ ስም ሳይኖራት ማደጔን፣ቤታቸው ድግስ ሲደገስ ዘመዶቿ እነቄስ ሞገሴ ሲመጡ፣… ያለውን ስዕል በዚሁ “ናፈቀኝ” ዘፈኗ በቃላት ምናባዊ ጉዞ ምልከታዋን ታስዳስሰናለች፥
                    “ናፈቀኝ አያ ታዴ ሆዴ
                      የሸበል አቧራ.. ….አይችልም ገላዬ
                       የኔማ ታዴዋ.. …….ና ቁም ከኃላዬ
        እያለ ሲዘፍን ትዝታው ገደለኝ “
በሀገሯ ከነበራት ሕይወት ወጥታ የአሜሪካን ኑሮን ስትጀምር እዛ ያለው ማህበረሰብ ግለኝነት የሰፈነበት ፣ከጎረቤት ጋር መገናኘት የሚከብድበት ፣ብቸኝነት የሚያጠቃበት ፣ለራስ ብቻ መኖር የተመረጠበት መሆኑን ስትገልፅ ደግሞ ፦
          “=====እያለ ሲዘፍን ትዝታው ገደለኝ
           ዛሬ በሰው ሀገር የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ ——-ትላለች “የሰው ከብት “በምን ይገለፃል ቢሉ ለሆዱ ባደረ!  እኔ እስከሚገባኝ ጂጂ የሰው ልጅ መገለጫው ያደገበት ማህበረሰብ ፍቅርና መተሳሰብ ነው ብላ የደመደመች ይመስላል ።ጂጂ በተለያዩ ዘፈኖቿ ስለ ሀገሯ፣ ስለህዝቧ ፣ስለ ማህበረሰቧ ያላትን ናፍቆት ና ጭንቀት ገልፃለች ።
ጂጂ የሀገሯ ነገር ሁሌም ሕመሟ ነው ፣እንቅልፍ ይነሳታል ፤እህ—-ህ–ህ ያሰኛታል ።ለዚህም ነው “እህ—ህ—-“ብላ ስሜቷን የምታጋራን።
ጎጃም ያረሰውን ለጎንደር ካልሸጠ
ገንደር ያረሰውን ለኅጃም ካልሸጠ
የሽዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ
የሐረር ነጋዴ ወለጋ ካልሸጠ
ፍቅር ወዴት ወዴት ——ወዴት ዘመም ዘመም
ሀገርማ አለችኝ ሀገር የኔ ሕመም
ውሉ እንዳይፈታ መቋጠሪያው ደሙ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ “
አገር ከዳር ዳር ሳይነጋገር ጂጂ ዓባይን ከአፈጣጠሩ ተነስታ ፣መልክዐምድራዊ እና ፖለቲካዊ እንደምታውን በመቃኘት የውሃ ፖለቲካ መጨረሻ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ሳይቀር በዘፈኗ ጠቁማለች ። ጂጂ እንዳብዛኛው ኢትዩጵያዊ ድምፃዊያንም ዓባይን አልተራገመችም ወይም መቀጣጠሪያም አላደረገችውም ።
ምሳሌ ፦1-“ዓባይም ቢሞላ ——–መሻገሪያው ሌላ “
             2″-የዓባይ ዳር ጉማሬ ወጥቶ አደረ ዛሬ “
              3-“የዓባይ ጥቁር እንጨት ያብባል በሰኔ”
              4-“ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በትሳስ “
አይነት ቀጠሮዋዊ ገለፃን ወደጎን ብላ
                               ዓባይ
      የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
       የማይደርቅ የማይነጥፍ ከዘመን የፀና
       ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና በፍጥረት
       የፈሰሰ ውሃ ቀድሞ ከገነት
እያለች ከጥንት አዳም ጀምሮ በታላቁ መፅሀፍ ዓባይ” ግዮን”ይባል ከነበረበት ዘመን ጀምራ ታሪኩን ፣ጥቅሙን ውበቱን ታነሳሳለች ።
መለስ ብላም ዓባይ በጉዞው ለሚያልፍባቸው ከተሞች ምንያህል የህልውናቸው መሰረት እንደሆነ በማውሳት ፦
          “ብነካህ ተነኩ አንቀጠቀጣቸው
            መሆንህን ሳላውቅ ስጋና ደማቸው
             የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
              ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበርሃ
               አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
               ምን አስቀምጠሀል ከግብፆች ከተማ “እያለች ትጠይቃለች ።  ይሄን ሁሉ ካለች በኃላ የዓለማችን ቀጣዩ ስጋት ከሆነው የውሃ ፖለቲካ ጋር በማስተሳሰር ፦
ዓባይ …………ዓባይ…..ዓባይ ወንዛወንዙ ብዙ ነው መዘዙ “
እያለች ከብዙዎቻችን ቀድማ ስለ ታላቁ ወንዛችን ተብሰልስላለች።
ጂጂ በዘፈን ግጥሞቿ የምታነሳቸው ሀሳቦች በተመሳሳይ መልዕክት የታጨቁ እና አሰልች አይደሉም። አንተ ቃል አባይ ፣አንተ ወላዋይ ፣አንተ አሸሸ ባይ ፣አጥቸህ ፣ሰስቸህ ፣ጎድቸህ ከሚሉ ድግግሞሽ የታረሙ እና በታላላቅ ሀሳቦች የተሞሉ ናቸው ።
             ”   አሞራ ወድጄ አሞራ ሆኛለሁ
                ነብርን ወድጄ ነብር ሆኘ አውቃለሁ
                 ድብ አንበሳም ነበርኩ ከጥንት ተዋድጄ
                  ዛሬ ግን አቃተኝ ብርቄን ሰው ወድጄ “
   በሚል  የሰው ልጅንና የታላቁን ፍቅር ኃያልነት በምጡቅ ቃሎቿ ታስቃኛለች ።
ሲሻትም ደግሞ ፦”ተው አንተሰው ጉንፋን  እኮአይደለም የያዘኝ ፍቅር ነው “በማለት የፍቅርን ግዝፈት ልኬት ደረጃ ታስለካናለች ።
                                 ጂጂ ስለ አድዋ
                            አድዋ ዛሬናት አድዋ ትላንት
                            መቸ ተረሱና የወዳደቁት
                             የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
                              ሰው ተከፍሎበታ ከደምና ካጥንት
                              ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
                              ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር
                               ትናገር አድዋ ትናገር ሀገሬ
                                እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ
በነፃ የመጣ ነፃነት እንደሌለ አስረግጣ በመግለፅ የመላው አፍሪካ የነፃነት ውሃልክ የሆነውን ታላቁን አድዋ ትዘክራለች ።
ጂጂ ሀገሯን በዘር ፣በኃይማኖት ፣በጎሳ ለከፋፈሏት ክፉ መሪዎች ናእኩይ ሀሳባቸውን ለሚከተሉት.  የማንንም እኩልነት ማንም አይፃረርም ።እኩልነታችን ፍቅርን ያማከለ ከሆነ ሰባኪም አንፈልግም ።ፍቅር አንድ ያደርገናል ።በልዩነታችን ውስጥ ጥላቻን መሰረት አድርገን የሚያራርቁንን ነገሮች የእኩልነት መንገድ አድርገን ካመጣናቸው ግን አደጋው ይከፋል ።የሚል ስጋቷን ታጋራናለች ።
                      ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ
                      መድኒት አለው የማታማታ
                      ዘር ሳይለያየን ወይ ኃይማኖት
                      ከጥንት በፍቅር የኖርንባት
                      አናት ኢትዩጵያ ውዴ ውዲቷ
                      በኅጆ አያልቅም ሙሽርነቷ ።
መሪዎች በሚፈልጉትም መጠን ባይሆን በቻሉት የስልጣን ዘመን በሀገሯላይ እንዳሻቸው መጋለባቸው ጊዚያዊ ናሀላፊ ሀገርና ህዝብ ግን ቌሚና ዘላቁ እንደሆኑ ስትገልፅ
                            ደግም ንጉሥ መጣ
                            ክፉም ንጉሥ መጣ
                            ሁሉም ይሄዳሉ እንዳመጣጣቸው ያለችው ።
ጁጂ በሌላ ስራዋ” ፍቅር “ዘርም ቀለምም እንደ ሌላለው የምታመልከውን አምላክ ምሳሌ በማድረግ እንዲህ ትላለች ።
                           እግዛብሄር ጥቁርነው ነጭነው አትበሉ
                           ሁሉን የፈጠረ እሱነው ባምሳሉ
                           በመልክ ይመስለናል እኔንም አንተንም
                           ያንድ አባት ልጆችን ነን እህትና ወንድም
በዚህ ስራዋ ውስጥ እግዛብሄርን ለምን እንደምታምን ምክንያቷን በመዘርዘር ስታስረዳም
    በሚገድል በሚያድን በእግዛብሄር አምናለሁ
   በሚፈርድ በሚምር በእግዛብሄር አምናለሁ
       ለስሙም ለክብሩም ቆሜ እዘምራለሁ
እጂጋሁየሁ ሽባባው (ጁጂ)
የኔ ዘመን ድንቅ የጥበብ አርበኛ ይሄን ሁሉ የሁንሽላት ሀገር አምላክ ከክፉ ሁሉ ጠብቆ ትንሳኤዋን ያሳይሽ ።
  አሜን!
ከተወልደ በየነ (ተቦርነ)
ሀምሌ 13 .2010 ዓ.ም
July 21 2018
Filed in: Amharic