>

“ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ ማንም ሊያስቆመው አይችልም”  - ገዱ አንዳርጋቸው

ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ ማንም ሊያስቆመው አይችልም”  – ገዱ አንዳርጋቸው
በፋሲል የኔ አለም
ቪክቶር ሁጎ “Nothing is more powerful than an idea whose time has come” ይላል። በጣም እውነቱን ነው፤  አቶ ገዱም “ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ ማንም ሊያስቆመው አይችልም”  ሲሉ በአማራ ቲቪ ተናገሩ።  አቶ ገዱ ትናንት አንድ አስተሳሰብ ብቻ (አብዮታዊ ዲሞክራሲ) ትክክል ነው ብለው ያምኑ የነበሩ ሰው ናቸው፤ አያምኑበትም ነበር ቢባል እንኳ በዚያ ድርጅት ውስጥ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ሰው ናቸው። ዛሬ ግን የዚያን አስተሰሳብ እጸጾች መግለጽ ብቻ ሳይሆን፣ በአረጀው አስተሳሰብ ለመቀጠል የሚፈልጉትን ሃይሎች ፊት ሆነው ከሚታገሉ ሰዎች አንዱና ዋናው ሆነዋል።  አቶ ገዱ በአካላዊ ማንነታቸው አልተቀየሩም፤ አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው ግን ሙሉ በሙሉ  ተቀይሯል።  አቶ ገዱ ለውጡን ለመቀልበስ ከሚታገሉ የቀድሞ ጓዶቻቸው  የሚለዩት፣ በእኔ እምነት፣ “ ጊዜው የደረሰን ሃሳብ በምንም ምድራዊ ሃይል ማቆም እንደማይቻል” ፈጥነው የተረዱ  በመሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ  ለውጡን ደግፈው የሚታገሉትን የኢህአዴግ መሪዎች ሁሉ ይመለከታል።
በቅርቡ ስለእነ መንግስቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስት ታሪክ በአቶ ብርሃኑ አስረስ የተጻፈውን መጽሃፍ ሳነብ፣ እነመንግስቱ ንዋይ ከ60 ዓመት በፊት ያነሱዋቸው የነበሩት የነጻነት ጥያቄዎች፣  ዛሬ እኛ ከምናነሳቸው ጥያቄዎች ጋር በእጅጉ መመሳሰላቸው በጣም ገርሞኝ ነበር። እነ መንግስቱ ያነሱት ሃሳብ ጊዜው አልደረሰም ነበርና ሳይወለድ ቀረ። መንግስቱ ራሱ፣ “የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡” ብሎ እሱ ያነሳው ሃሳብ ጊዜው እንዳልደረሰ ለዳኞች ተናግሮ ነበር። ጊዜው ያልደረሰን ሃሳብ አንድ ሰው ብቻውን እንዳይወለድ ሊያደርገው ይችላል፤  ጊዜው የደረሰን አስተሳሰብ ግን ማንም ምድራዊ ሃይል ሊያቆመው አይችልም።
ጊዜው የደረሰን ሃሳብ ለማስቆም መሞከር፣ ጸቡ  ከሰዎች ጋር ሳይሆን ከጊዜ ጋር ነው፤ ጊዜ ሲጥል ደግሞ አይጣል ነው። መመለሻ የለም።
Filed in: Amharic