>

የተደረገልንን እናስተውላለን ግን?! (ዘውድአለም ታደሠ)

የተደረገልንን እናስተውላለን ግን?!
ዘውድአለም ታደሠ
ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቀን የደቀመዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ አጥቦ ሲጨርስ «ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?» ብሎ ጠየቃቸው!!
ሰው ከተደረገለት ይልቅ የተደረገበት ላይ ትኩረት ያደርጋል። ውለታ ፈጥኖ ይረሳል ቂምና በቀልን ልቡ ላይ ያትማል። የሰጡትን ይቀበላል። ነገር ግን አንዳንዴ ምን እንደተሰጠው እንኳ አያውቅም!! ለዚህ ይመስለኛል ኢየሱስ የተደረገላችሁን ታስተውላላችሁን? ብሎ የጠየቀው!!
ስለዶክተር አብይና የትግል ጓዶቹ ሳስብ እውነት ግን እኛ የተደረገልን ምን እንደሆነ ገብቶናል? ብዬ አስባለሁ!! …እኔ ስለዶክተር አብይና አብረውት ለለውጥ ስለቆሙ ጓዶቹ ሳስብ የሚሰማኝ ይሄ ነው …..
 ኢትዮጵያ መፈራረሷን አምነን ለቅሶ ተቀምጠን በነበረ ሰአት ፣ ዘረኝነት አየሩን በክሎት ከዳር እስከዳር ሐገር በግጭት ስትናጥ፣ ኢትዮጵያ ብሎ መጥራት አሳፋሪ የሆነበት ዘመን መጥቶ ሐገር ስትጨነቅ፣ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ከወደቀበት አንስተው በኩራት የሚጠሩ ወጣት መሪዎች ከኦህዴድ ውስጥ ብቅ አሉ!! በእንቦጭ ስበብ የኦሮሞ ወጣቶችን ወደባህርዳር አዝምተው ጉዟቸውን በፍቅር ጀመሩ!! አየሩን ሁሉ በኢትዮጵያ ስም እንደጢስ ሞሉት … ልባችን በፍቅር ነደደች!! ደነገጥን!! የምናየው ህልም ይሁን ፊልም ግራ ገባን!! እነለማ፣ እነአብይ፣ እነአዲሱ፣ እነገዱ ከህዝብ ጎን ሲቆሙ የዘመናችን ጎልያዶች በፍርሃት ራዱ!! ህዝቡ ተስፋ በቆረጠባት ኢትዮጵያ ዳግም ተስፋ ያደርግ ጀመር!! ጠብመንጃና ባለጠብመንጃ በዚያ እነዶክተር አብይና ህዝብ በዚህ ረድፍ ሆነው ግጥሚያ ጀመሩ …. በመጨረሻም ከህዝብ ጎን የቆሙት አሸነፉ!
ዶክተሩ በመጀመሪያ የፓርላማ ንግግሩ ከሰላሳ ግዜ በላይ ኢትዮጵያን በመጥራት የኢትዮጵያኒዝም ጉዞውን ቀደሰው!! ህዝብ ግራ ተጋባ!! ተቃዋሚዎች እየጠረጠሩ ተገረሙ!! ብዙዎች «እውነት ዶክተር አብይ ይከዳን ይሆን?» ብለው ሲተክዙ፣ ብዙዎች «የወያኔ ሎሌ ነው። ምንም የማድረግ አቅም የለውም» ብለው ተስፋችንን ሊያከስሙ ሲፍጨረጨሩ፣ ዶክተር አብይ ግን በመጀመሪያው ቀን የገባውን ቃልኪዳን ስጋ እያለበሰ ለህዝቡ ማሳየት ጀመረ  …..
የፖለቲካ እስረኞችን ጠራርጎ ፈታ!! ኢህአዴግን ለመጣል ጠብመንጃ ያነሳው አንዳርጋቸው ፅጌን ሳይቀር በመፍታት ቤተመንግስት ውስጥ በክብር ተቀበለው!! የዋልድባ መነኮሳት ፣ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊዎች ፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ዶክተሮች ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች …. በሙሉ ተጠራርገው ተፈቱ!!!!!
ለፓርቲያቸው ባላቸው ታማኝነት ብቻ ዙፋን ላይ የተወዘቱ ኤክስፓይርድ ዴታቸው ያለፉ ባለስልጣኖችን በማንሳት አቅምና ችሎታ ባላቸው ምሁራን ተተኩ!!
ውጭ በስደት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ተቃዋሚዎች በይፋ ወደሐገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ቀረበላቸው። የውጭ ሚዲያዎች ወደሐገር ውስጥ እንዲገቡ ጥሪ ተደረገ፣ በግፍ የተፈረደባቸው እነብርሃኑ ነጋና ጃዋር አህመድን የመሳሰሉ ፖለቲከኞች ክሳቸው ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ ተወሰነ!
ሚዲያዎች ነፃ ሆኑ!! በኢሳትና በኢቲቪ መሃከል ያለው ልዩነት ጠበበ፣ በየማረሚያ ቤቱ በመንግስት ሲከወኑ የቆዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በግልፅ ህዝቡ ጋር እንዲደርሱ ተደረገ!!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ መንግስት አሸባሪ እንደነበር አመኑ!! (ምናልባት በአለም የመጀመሪያው መሪ ናቸው የሚመሩትን መንግስት አሸባሪ ያሉ!)
ከግማሽ ምእተአመት በላይ የፈጀ ከመቶ ሺ በላይ ሰዎች የሞቱበት ፣ መቶ ሺዎች የተፈናቀሉበት፣ በመጎዳዳት ፖለቲካ ላይ የተመሰረተውን የኢትዮ ኤርትራ ታሪክ በመቶ ቀን ብቻ ሙሉ ለሙሉ ለወጡት!!! በመቶ ቀን ብቻ!! ይሄን በታሪክ ተመዝግቦ ዘልአለም የሚያስወድሳቸው ተግባር ፈፀሙ!! በመቶ ቀን ብቻ ኢትዮጵያ የኤርትራን አየር መንግድ ሃያ ፐርሰንት ገዛች። ቦርደሩ ለህዝብ ክፍት ሆነ። ለአመታት የተነፋፈቁ ወንድማማች ህዝቦች ለመጀመሪያ ግዜ ተገናኙ!! ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረው የአሰብ ጉዳይ ምላሽ አገኘ!! ይህ ሁሉ በመቶ ቀን ብቻ!!!
ከሱዳን ፣ ከግብፅ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ጋር ያለን ግንኙት የበለጠ ጠነከረ!! ዘልአለም የአለም መሳቂያ እንዳልሆንን ፣ ዛሬ አለም ስለኢትዮጵያ መልካም ማውራት ጀምሯል። የአለም ሚዲያዎች ሁሉ ስለኢትዮጵያ በጎ መፃኢ እድል ተነበዩ!!
ህዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ለመሪው አደባባይ በመውጣት ድጋፉን ገለፀ!! ለመጀመሪያ ግዜ ህዝብ የማይፈራቸውን ግን የሚያፈቅራቸውን መሪ አገኘ!! በአይዲዮሎጂ የማይገናኙ የተለያየ አቋምና አመለካከት ያላቸው ሰዎች ለመጀመሪያ ግዜ በአንድ ድምፅ ይናገሩ ጀመር!!
እነዚህና እነዚህን መሰል ቆጥረን የማንጨረሳቸው ክስተቶች የተፈፀሙት አራት ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ ነው!! በመቶ ቀን ብቻ!!!!!!
አንተ ህዝብ!! የተሰጠህን አመስግን!! ይህን ያሳዩህን መሪዎች አክብር!! ትናንትህን ዞር ብለህ ተመልከት!! ከሶስት ወር በፊት እየተገረፍክ፣ እየተሰደብክ፣ እየተረገጥክ፣ እየተገደልክ፣ በሃሰት እየተከሰስክ፣ ትኖር ነበር!! ለሃያሰባት አመት ያልተመለሰልህ ጥያቄ በሶስት ወር ተመልሶልሃል!! ዝቅ ብለህ አመስግን! በሆነው ባልሆነው አታለቃቅስ!! የእግዚሀርን አይን አትውጋ!! ምስጋና ቢስ፣ ውለታ ቢስ፣ አትሁን!! ክብረቢስ አትሁን!! የተደረገልህን በረከት ቁጠር!! ሰው አይሳሳትም አልልህም ግን ከተደረገልህ አንፃር የተደረገብህ ኢምንት ነው!! ሐገር መምራት በግ መጠበቅ አይደለም። መሪዎች ይሳሳታሉ ፣ስህተታቸውን ያርማሉ፣ ሁኔታህኮ ሰባሰባት ቢሊዮን ብርና ኮንዶሚኒየም ጠፋ ሲሉህ ጭጭ ብለህ የኖርክ አትመስልም!!
ህሊና ይኑርህ!! 
Filed in: Amharic