>
5:13 pm - Sunday April 18, 8083

ጠቅላያችንን ሁላችንም ተስፋ አሳጥተነው ወዳልተገባ መንገድ እንዳንመራው እንጠንቀቅ!!! (ፋሲል የኔዓለም)

ጠቅላያችንን ሁላችንም ተስፋ አሳጥተነው ወዳልተገባ መንገድ እንዳንመራው እንጠንቀቅ!!!
ፋሲል የኔዓለም
* ጽንፈኛ ኦሮሞዎች “ዶ/ር አብይ ጅማ ቢወለድም አማራ ነው” እያሉ ህዝቡን እየሰበሰቡ በእርሱ ላይ ለማነሳሳት እየሞከሩ ነው።
 
* የተወሰኑ ህወሃቶችም ለውጡን ለመቀልበስ ወታደራዊ ስልጠና ሳይቀር መስጠት ጀምረዋል።
 
* እነ አብዲ ኢሌ ለውጡን የደገፉ መስለው በየስፍራው ግጭት ይቀሰቅሳሉ። 
 
* ለውጡን ደግፈው የቆሙት አካሎች ደግሞ የአቋም መዛነፍ እየታየባቸው ያለ ይመስላል።
እውነት ለመናገር በዚህ ሰዓት እንደ ዶ/ር አብይ አህመድ እጅግ የሚያሳዝነኝ ሰው የለም።
ያለንበት ጊዜ በጥንቃቄ ካልተያዘ የፈረንሳይን አብዮት ታሪክ እንዳያመጣብን እፈራለሁ። የፈረንሳይ አብዮት መሪዎች ተራማጅ አላማዎችን ይዘው ቢነሱም በአመራር ጉድለት አብዮቱን ወደ ሽብር ለውጠውት ነበር። ሽብርን ለማስቆም የመጣው ናፖሊዮን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ራሱን ንጉስ አድርጎ ሾመ። ከዚያ በሁዋላ ፈረንሳይ ወደ ዲሞክራሲ ሃዲድ ተመልሳ እስከትገባ 90 ዓመት ያክል ወሰደባት።
ከተለያዩ ሊህቃን የሚሰነዘሩት አንዳንድ አደገኛ አስተሳሰቦች አገራችንን ወደ ሽብር መንገድ እንዳይከቷት እሰጋለሁ። ዶ/ር አብይ አገራችን ወደ ሽብር እየገባች ከመሰላቸው ጠንከር ያለ የሃይል እርምጃ መውሰዳቸው አይቀሬ ነው።፤ ሃይል መጠቀም የጀመረ መሪ ደግሞ ሃሳቦችን መቀበል ያቆምና ጉልበትን ማመን ይጀምራል። አምባገነንነትም መግቢያ በር ያገኛል። ይህንን የዘመን ክስተት ሊባል የሚችል ድንቅ መሪ በእኛ የአያያዝ ጉድለት በመጨረሻ አምባገነን መሪ እንዳናደርገው እሰጋለሁ።
እውን ለውጡን የሚፈልገው ክፍል ፍላጎቱንና ፍላጎቱን የሚያሳከበትን ስትራቴጂ ጠንቅቆ ያውቃል? እኛ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የምንታገል ሃይሎች፣ ዶ/ር አብይ የጀመሩትን የፍቅር መንገድ እየደገፍን፣ ዲሞክራሲያ ተቋማት እንዲገነቡ ግፊታችንን መጠናከር ሲገባን ፣ “እከሌን ሹምልን፣ እከሌን አውርድለን” እያልን፣ በቀደመው መንገድ መጓዛችን የመርህ ጥያቄ እንዳያስነሳብን እሰጋለሁ። ለእኔ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ሳይገነቡ የሚቀርቡት የስልጣን ጥያቄዎች ሁሉ ከፈረሱ ጋሪውን የሚያስቀድሙ ናቸው። ለብሄሮች መብት የሚታገል አንድ ፖለቲከኛ በየትኛውም መንገድ ቢሆን የብሄሩ ሰው በስልጣን እንዲወከል መታገሉ በእሱ አይን ከታዬ ትክክል ነው። ይህን ሰው መተቼት አይገባም፤ የታገለለት አላማ ነውና። ለዜግነት መብት የሚታገል ሰው ግን፣ ቅድሚያ የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲገነቡ መወትወቱን ትቶ “አሁን ባለው ስርዓት ውስጥ እነማን ተወከሉ?” የሚል ጥያቄ አንስቶ በዚያ ላይ አታካራ የሚፈጥር ከሆነ፣ የመርህ መዛነፍ አጋጥሞታል ብዬ እንዳስብ ያስገድደኛል።
እኔ ነጻ ተቋማት ሳይገነቡ ሁሉም ብሄሮች “ እኩል” ተወክለው ከሚያስተዳድሩት ስርዓት ይልቅ ፣ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ተገንብተው በህዝብ የተመረጡ የአንድ ብሄር ሰዎች የሚያስተዳድሩበትን ስርዓት መቶ በመቶ እመርጣለሁ። የምታገለው የዜጎችን እኩልነት ለማስፈን እንጅ የብሄሮችን እኩልነት ለማስፈን አይደለም። በእኔ እምነት የዜጎች እኩልነት ሳይሰፍን የብሄሮች እኩልነት ሊሰፍን አይችልም፤ የዜጎች እኩልነት የሚሰፍነው ደግሞ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሲገነባ ብቻ ነው። እኔን የሚያሳስበኝ “ማን መጣ” የሚለው ሳይሆን “ማን በምን መንገድ መጣ” የሚለው ጉዳይ ነው ። የተደላደለ መንገድ መስራት እንጅ በመንገዱ ላይ ማን ይመላለስበት የሚለው ጉዳይ የዲሞክራሲ ሃይሎችን ሊያሳስባቸው አይገባም ብዬ በጽኑ አምናለሁ። ይህን ስል ነጻ ተቋማት እስኪገነቡ በአገሪቱ ላይ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞች ሲሾሙ ዝም ብዬ አያለሁ ማለት አይደለም። እይታዬ በብሄር መነጽር አይሆንም እንጅ ፣ ከየትኛውም ብሄር ቢሆን ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ለአንድም ቀን ቢሆን እንኳን እንዲሾሙ አልፈቅድም። ዶ/ር አብይ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን እንደሚገነባ ግልጽ አድርጓል። በዋና ዋና ተቋማት ላይም መሰረታዊ ለውጦችን እያመጣ ነው። ዲሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲገነቡ የምንታገል ሁሉ ትኩረታችንን በዚህ ላይ ብናደረግ፣ እናተርፋለን እንጅ አንከስርም። ከሁሉም በላይ ዶ/ር አብይን ተስፋ አሳጥተነው በጭንቀት (frustration) ወደ አልሆነ መንገድ እንዳንመራው ለዲሞክራሲ የምንታገል ሃይሎች ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።”
Filed in: Amharic