>
5:13 pm - Saturday April 20, 3196

ባንዲራችን/ሰንደቅ ዓላማችን!!! (ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ)

ባንዲራችን/ሰንደቅ ዓላማችን!!!
ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ
ባንዲራ ቃሉ ጣልያንኛ፥ ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵኛ (አማርኛ) ነው። ባንዲራችን የሚለውን ቃል ይዤ የምጽፈው ዛሬ ሕዝቡ የሚጠቀምበት መሆኑን በመገንዘብ ነው። የጽሑፌ ዓላማ ባንዲራችንን ስለገጠመው ችግር ያለኝን አስተያየት ለማካፈል እንጂ፥ ሁለቱን ቃላት ለመተቸት አይደለም።
የባንዲራችን ቀለም አረንጓዴ፥ ቢጫ፥ ቀይ ነው። እነዚህን ቀለሞች የያዘ ባንዲራ የኛ መሆኑ የሚታወቀው በቀለሞቹ ብቻ ሳይሆን፥ ቀለሙን በያዙት ልብሶች አሰላለፍ ጭምር ነው። የአሁኑ አስላለፍ አረንጓዴ፥ ቢጫ፥ ቀይ ነው። በፊት ግን፥ ቀይ፥ ቢጫ፥ አረንጓዴ ነበር። የትራፊክ መብራቶችን የፈጠረው ጋሬት ሞርጋን የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ መብራቶቹን ቀይ፥ ቢጫ፥ አረንጓዴ ያደረገው የኢትዮጵያ ባንዲራ በአሜሪካ (በኋላም በመላ ዓለም) እንዲዘረጋ በማሰብ ነው። ግን ኢትዮጵያ ወደ ዓለም-አቀፉ ኅብረተሰብ ስትመጣ የቀለሞቹ አሰላለፍ በእስፓኝ ተወስዶ አገኘችው። ስለዚህ አሰላለፉን መለወጥ ነበረባት።
የቀለሞቹ ትርጕም የተሰጠው ባንዲራው ከተወለደ ወዲህ ነው። መቸም ልጅ ከመወለዱ በፊት ስም አይወጣለትም። ሁለተኛም፥ አንድ ትርጕም ሰጪ ባለሥልጣን ስለሌለ፥ ሁሉም እንደመሰለው ይተረጕመዋል። እኔ ሳድግ የተነገረኝ፥ “አረንጓዴው ልምላሜ፥ ቢጫው ሰብል፥ ቀዩ ላገር ደም ማፍሰስ” የሚል ነበረ።
ከባለሦስት ቀለም ልብስ ቀጥሎ አንድ አርማ ተጨመረበት። ያ አርማ፥ ባንዲራ የያዘ፥ መስቀል ያለበት ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረ። በተጨማሪም፥ ከራእየ ዮሐንስ የተወሰደ “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” የሚል ጽሑፍ ነበረው። የጥንት መንግሥታት ሁሉ የሃይማኖታቸውን ምልክት ባንዲራቸው ላይ እንደሚያደርጉት ጥንታዊት ኢትዮጵያም እንደዚያ ብታደርግ የሚያስገርም ነገር አይደለም። ሃይማኖትን ከፖለቲካ የለዩ አገሮች፥ ለታሪክነቱ ሲሉ ሃይማኖታዊ አርማቸውን አልጣሉትም። እኛ ግን ለሌሎች በማሰብ ቶሎ ስለምንደነግጥ፥ ጕዳዩ ሳይተችበት፥ አንበሳው ላይ ያለውን መስቀል በዘመነ ደርግ ጎምደን ጣልነው። ያ መናጥማ ቀለሞቹን ሳይቀር ሊለውጣቸው ፈልጎ ነበር። ጩኸት ቢበዛበት፥ ጨርቃቸውን ተውላቸው አለንና የራሱን አርማ (ኮከብ አይሉት የዳዊት ጋሻ) ለጠፈበት። “ተውላቸው” ሲል እሱና የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊትና ጀርባ መሆናቸውን መመስከሩ ነው። እኛም ሰውየው ምን ዛፍ እንደሆነ ከፍሬው አውቀነው ነበር።
ባንዲራችን አሁንም ችግር አለበት። ልሙጡን የሚፈልጉ አሉ። ልሙጡን የማይፈልጉ አሉ። ልሙጡን የሚፈልጉ በአብላጫ ብዙዎች ይመስሉኛል። ልሙጡን የማይፈልጉ ሁለት ቡድኖች ናቸው፤ አንዱ ቡድን አዲስ አርማ የለጠፉበት ኢሕአዴጎች/ወያኔዎችና ዘር ማንዘራቸው ናቸው። ሌላው ቡድን አፄ ምኒልክ ያስገበሩን ይኸንን ባንዲራ እያውለበለቡ ስለሆነ ሽንፈታችንን ስለሚያስታውሰን ዓይኑን አታሳዩን የሚሉ ናቸው።
ልሙጡን ባንዲራ የማይፈልጉ ቡድቦች አንዳንድ ነገሮችን ተመልክተው፥ አብዛኛው ሕዝብ የሚደግፈው አማራጭ ሲያጡ፥ ሐሳባቸውን ይለውጡ ይሆናል። አንደኛ፥ ለእስላሞችና ለሽንፎች ሲባል የአሸናፊነትና የክርስቲያንነት ምልክቶች ተነሥተውል። ሁለተኛ፥ ልሙጡን ባንዲራ ብዙ የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ምልክት አድርገውት የራሳቸውን ባንዲራ በአምሳያው ቀርጸዋል። ሦስተኛ፥ መሀንዲሱ ጋሬት ሞርጋን ባንዴራችንን በዓለም መንገዶች ላይ እንድታሸበርቅ አድርጓታል። አራተኛ፥ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፈልገዋል።
ሌላ ባንዲራ መፍጠር ይቻላል። ግን እነዚህን አራት ነጥቦች በምን ዓይነት ዘዴ አልፈን አብዛኛው ሕዝብ የሚቀበለው ባንዲራ መቅረጽ ይቻላል? ወይስ ክልል የሚባል ጠላት አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ መሆናችንን ስለካደብን፥ አንድ ባንዲራ አያስፈልግም ልንል ነው?
Filed in: Amharic