>

አሳባቂነት፡ ክፍል 1  (ጠቅላይ ሚኒስቴር ያልሆናችሁ ኣታንቡት!)

አሳባቂነት፡ ክፍል 1 
(ጠቅላይ ሚኒስቴር ያልሆናችሁ ኣታንቡት!)
ንዱአለም ቦኪቶ (ነጭ ለባሽ አንዲ ማኛ)
ሰላም ነው ጠሚያችን !? ምነውሳ ሰሞኑን ደግሞ ሰበር ዜና ጠፋሳ !? እኔ ድሮም ይሄን ሰበር ዜና በልክ ያድርጉት ያልቅቦታል ስል ነበር…አልሰማ አሉኝ እንጂ!…..ሰውኮ ወሬ ሲያጣ እንደዛ ባመሰገኖት አፉ ገና መንፈቅ እንኳን ሳይሞላዎት ላስ ላስ እያደረጎት ነው፡፡አይገርሞትም ግን ይሄ የተልባ ስፍር የሆነ ህዝብ!? …አሁን ደግም እነ ሽሜ የሚያወሩት ሲያጡ “ሰውየው  ድግስ በድግስ ሆነዋል” እያሎት ነው….ለኢሳያስ አቀባበል ድግስ ተደርጎ ነበር ….ኢሳያስ ሲሄድ ኢሳያስን በተመለከተ በተዘጋጀው ድግስ የተሳተፉ ሰዎች ምስጋና ማቅረቢያ ሌላ ድግስ ..ከዚያም በዚህኛው የምስጋና ማቅረቢያ ድግስ ላይ ለተሳተፉ ሰዎች ደግሞ ሌላ ምስጋና  ማቅረቢያ ድግስ (ሽሜ ነብስህ አይማርም መቼም!)…ከዛም የድግስ  “ቪሺየስ ሰርክል” ……ከዛም በአመቱ  መጨረሻ ጋሽ ገመቺስ (ዋና ኦዲተር) አዲንግ ማሽናቸውን ይዘው መነጽራቸውን ገፋ ገፋ እያደረጉ “ሂሳብ እንስራ!?” ብለው ሲያፋጥጦት ይታየኛል….. “ምንድነው ልጅ አብይ !?ለሩብ አመት እኮ ለቢራ እና ለቢሮ ያወጣኸው ገንዘብ በጣም የተጠጋጋ  ነው!” ሲሎት  እርስዎ ደግሞ የሚሉት አጥተው ቁልጭ ቁልጭ ….ጋሽ ገሜ አንዴ ከያዙ አይለቁ መቼም “…..ደግሞ እዚህ ጋር 60 ሚሊዮን ብር ! ያውም ለኬኔቶ!?… (ያው ፕሮቴስታንት ኖት ብዬ ነው)..ትንሽ እንኳን ራስን ያዝ ለማያደርግ ነገር …..ተው  እንጂ አብይ! ድግስህን ጋብ አድርገው  …!ልጅ እያሱን ልትሆን ነው እንዴ !?”ሲሎት …..እርስዎም በዚህ ተናደው ጋሽ ገመቺስን ወደ ሆነ አገር በአምባሳደርነት ሲፈይሯቸው ይታየኛል..(ያው ትልቁ ቅጣቶት እሱ ነው ብዬ ነው!) … ግምቴን ነው ያልኩት ደግሞ ሆሆ…!  ! በዚህ ተናደው እኔንም ወደ አንዱ አውሮፓ አገር ሾመው ልክ እንዳያስገቡኝ  ..ደግሞ ልኑርበት ልጄ !? ሆሆ… ሎል፡፡
እና ጠሚ ሆይ እባኮትን ይሄ ድግሶትን እና ከበርቻቻዎትትን ጋብ አድርገው ቆፍጠን ቆፍጠን ያሉ ነገሮችን ሰርተው ለህዝቡ ያሳዩ……በዛ ላይ መቸም እኔ አልደብቆትም …ይሄ የቦምቡ ውርወራ ውጤት ነገር በጣም እያሰተቾት ነው!..በነገራችን ላይ ይሄን የመሰለ ጮማ ወሬ ላሽ ሊሉን አስበዋል እንዴ!? እንደዛ ከሆነ አበሻን አያቁትም ማለት ነው! ህዝቤ ወሬ አስጀምሮ ከሚቀየስበት ግድብ አስጀምሮ የሚቀየስበት መሪ ይሻለዋል እኮ!…ሆሆሆ! … አንዳንዶችማ “ጠሚው “FBI ን አስመጥተናል” ያሉን የነጻት ወርቅነህን ኤፍቢአይ(ፊልሙን)  ነው እንዴ?!” እያሉ ሙድ እየያዙቦት ነውኮ!….እርስዎስ ግን ምን አንቀለቀሎት እንደዚህ አይነቱን ለሰበብ የማይመች የተሟላ ድርጀት ባገር ውስጥ ጉዳይ “ኢንቮልቭ” የሚያደርጉት!?..ጉዳዩን የያዘው የአገራችን ፖሊስ ቢሆን ኖሮ በቀላሉ ስለቦምቡ ውጤት በተነሳ ቁጥር ኮሚሽነሩ ጋሽ ዘይኑ በቲቪ ብቅ እያሉ “..ሁላችሁም እንደምታውቁት “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” ነው የሚባለው ..እናም ደግሞ  የአገራችን ፖሊስ በቴክኒክም ሆነ በሰው ሃይል አደራጀጀት የተሟላ ስላልሆነ ማቻኮል አያስፈልግም….”የቸኮለች የብብቷን ጣለች” አይደል የሚባለው…የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል..አትቸኩሉ… ” ምናምን እያሉ ሆዳችንን በተረትና ምሳሌ እየነፉ  እንደማንኛውም ምርመራ ቢያንስ አራት አመት ማስጠበቅ የሚችሉትን ጭራሽ እርስዎ  FBI? …እሰይ! ይበሎት! …በፊልም እንደምናውቀው ከሆነ ግን  እኔም የመሰለኝ የFBI ጀለሶች ገና ከፕሌን ወርደው መስቀል አደባባይ ደርሰው አንዲት ቁሩ ሲጋራ ከ”ክራይም ሲኑ” ላይ አግኝተው በመቀስ አንስተው በላስኪት ከተው ላጥ ሊሉ ሲል  ጋሽ ዘይኑ “ቀጥሉዋ ሌላስ!?” ሲሏቸው “ኢት ኢዝ ጁስት ኢነፍ…ሌላ ተጨማሪ ምንም አያስፈልግም” በማለት  እሷን ይዘው በጊዜያዊ ቢሮዋቸው  ውስጥ በአጉሊ መነጽር እያዩ የሆነ ካርታ ነገር ጠረጴዛቸው ላይ ዘርግተው እና የስታር ባክስ ቡና እየጠጡ በባለማንገቻ ሱሪ ላይ ሽጉጣቸውን በብታቸው አንጠልጥለው  …ሲጋራቸውን እያቦነኑ ወዲያ ወዲህ እየተንጎራደዱ “ኦራይት ….ሲጋራው ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወድቆ መገኘቱ የሚያሳየው ቦምቡን የወረወረው ሰው ዴፍኔትሊ ከሰሜን ኢትዮጰያ የመጣ መሆኑን ሲሆን ግማሽ እየቀረው ሲጋራውን መጣሉ ደግሞ ለገንዘብ ግድ እንደሌለው እና ምናልባትም ቦምቡንም ለመወርወር ከጀርባው ጠንካራ የልማት ድርጅት ስፖንሰር እንዳደረገው የሚያመላክት ፍንጭ ነው …በተረፈ ሲጋራውን መሬት ከጣለ በኋላ በሃይል የደፈጠጠው መሆኑ ደግሞ የላኩት ሰዎች የህዝቡን ጥያቄ እንዲሁ ሲያዳፍኑ እና ሰብአዊ መብቶችን  ሲደፈጥጡ የቆዩ ግሩፖች መሆናቸው የሚያሳይ ነው ፒሪሪረም ፒሪሪም… ቡም! ወርዋሪው ተክለእዝጊ ነው…..”፡፡ብለው ጠረጲዛወውን በጡጫ ….ከዛ ቶፕ ሴክሬት በሚል በቀይ በተጻፈበት ኤንቨሎፕ ውጤቱን ጠረጴዛዎት ላይ ስርአት በሌለው መልኩ ውርውር ያደርጋሉ ብዬ ነበር ፡፡ ከዛ ደግሞ እርስዎ በኢቲቪ ብቅ ብለው “ሰበር ዜና” …ምናምን ….ግን እስከ አሁን ወፍ የለም፡፡
ካልሆነ ደግሞ ሰሞኑን በቲቪ ብቅ ብለው “ፊልም ሌላ የገሃዱ አለም  ሌላ “ብለው ይገላግሉን  …የምሬን ነው! እንደው “ዳንኤል ብርሃነ” አይበሉኝና ሳስበው ሳስበው  “መልሱ/ውጤቱ” የተመቾት አልመሰለኝም!…..ግዴለም አንዳንዴ ጠላት ከሩቅ አይመጣም…ትክክለኛውን መልስ ይንገሩንና ያበጠው ይፈንዳ!… …ግን ደግሞ ከደበሮት መልሱንም  ይቀይሩትና ይገላግሉና! አፍተር ኦል ጠሚ ኖት! በዛ ላይ ይሄ የትም የሚሰራበት አሰራር ነው!.ያኔ አ.አ.ዩ ተማሪ እያለን አንድ የዶርሜ ልጅ የነገረኝን ልንገሮት …. አንድ የነሱ ዲፓርትመንት ፕሮፌሰር ለተማሪዎቻቸው  ሚድ ፈተና ሳይሰጡ ፋይናል ደረስባቸው፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው ከፋይናል አንድ ሳምንት በፊት ለፋይናል ያዘጋጇቸውን 5 ጥያቄዎች “ሚድ” ብለው ተማሪዎቹን ይፈትናሉ ….ከዛም በሳምንቱ ለፋይናል ሌላ ጥያቄ ማውጣት ይደብራቸውና እነኛኑ የሚድ 5 ጥያቄዎች ደግመው ፋይናል ላይ ያመጣሉ ፡፡ታዲያ አንዱ ጎበዝ ተማሪ እጁን ያወጣና “ፕሮፌሰር ይሄንን ጥያቄ እኮ የጥያቄዎቹ  ተራ ቁጥር ቦታ እንኳን ሳይቀያየር የዛሬ ሳምንት ተፈትነነዋል” ሲላቸው ምን ቢሉት ጥሩ ነው ..”ዝም ብለህ ስራ! መልሱን ቀይሬዋለሁ “…ሃሃሃ ..እና ኤፍ ቢ አዮ ችም  የፈለገውን ይበሎት  ካልተመቾት መልሱን ለምን አይቀይሩትምና አንገላገልም!?….ምክር ነው፡፡ ግን በአጭሩ ዋናው ከዚህ ጥያቄ መገላገሎትና እኛም ከዚህ ሃሳብ መውጣታን ብቻ ነው፡፡እንደውም እርስዎን ለመንቆር ነው መሰለኝ  በዚህ ሰሞን በፌቡ የምትዘዋወር አንዲት ቀልድ አለች …ጊዜ ካሎት ልልቀቅቦት ..አንዱ በታክሲ እየሄደ ዝርዝር ስላልነበረው መቶ ብር ለወያላው ይሰጠዋል …ከዛ ከአሁን አሁን መልሴን ይሰጠኛል ብሎ ቢጠብቅ  ወያላ ሆዬ ዝም! …ከዛ ሰውየው ድንገት ሳያስበው ጮክ ብሎ ምን ቢል ጥሩ ነው ..”አቦ በናትህ ሰውዬ መልሴን ስጠኝና ሌላ ነገር ላስብበት!?”..ሃሃሃ እኛም ያን ያክል የቦምቡን ውጤት ፈልገነው ሳይሆን እንዳው ሌላ ነገር እንድናስብበት ብቻ ነው ….ኋላ ላይ ደግሞ ሌሎች ሁለት ሰሞኑን የሚታሙባቸውን ነገሮች ይዤ እመለሳለሁ፡፡ እስከዛው ግን ይመቾት!   መልካም ቅዳሜ
እናንተም
ይመቻችሁ
Filed in: Amharic