>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8473

ማጨቃጨቅ የሌለበት የአዲስ አበባ ከንቲባ ጉዳይ!?! (ውብሸት ሙላት)

ማጨቃጨቅ የሌለበት የአዲስ አበባ ከንቲባ ጉዳይ!?!
ውብሸት ሙላት
በግሌ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሆነው ስለተሾሙት ሰዎች የብሔር ማንነታቸውን መሠረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት እስጥ አገባ ውስጥ መግባት፣አቧራ ማስነሳት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።
በመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ ዓይነቱ ውዝግብ (በተለይም የኦሮሞና የአማራ ደርዝ በማስያዝ) አሁን እየታየ ላለው ለውጥ እንቅፋት ከመሆን፣ በአማራ በኦሮሞ ሕዝቦች እንዲሁም በብአዴንና በኦህዴድ መካከል ውጥረት እንዲፈጠር ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ውጥረት እንዲፈጠር ማድረግ ደግሞ የስምምነት እንዳይኖር የሚሹት የሌሎች ፍላጎት ነው። ለፍላጎታቸው መሳካት ተባባሪ መሆን ብቻ ነው ትርፉ።
አቶ ድሪባ ኩማ ባይነሱ ኖሮ በሚቀጥውለ ዓትመ እስከሚደረገው ምርጫ ድረስ ሊቆዩ ይችሉ ነበር። አሁን የእሳቸውን ተግባር የሚያከውናውኑትም ከብሔር አንጻር አንድ ናቸው። ባይነሱ ኖሮ ከንቲባው ኦሮሞ፣ምክትሉ አማራ (አቶ አባተ ስጦታው) ሆነው ይቀጥሉ ነበር።
አዲስ አበባ ላይ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው እስካሁን የተርረጉትን የተበለሻሹ መዋቅርና አሠራሮችን የሚበጣጥስ (የሚያሻሽል) ሰው መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። ባይሆን ማስተካከያው በሁሉም መልኩ ፍትሐዊ መሆን አለባውቸ። ያንን መከታተል ነው። እርምጃ ለመውሰድ ደግሞ አብሮ ካቢኔ ሆኖ ሲሠራ ከነበረ ሰው ይልቅ አዲስ ሰው ቢሆን ይሻላል።
አዲስ አበባን የአዲስ አበባ ሰው ቢያስተዳድራት ተገቢነት ያለው አስተያየት ነው። ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ላይም ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን ጋር አብሮ የሚሔድ ነው። ይሁን እስካሁን የአዲስ አበባ የሆነ ፓርቲ እንዲኖር ስላልተደረገ ለወደፊት ማሰብ ነው የሚጠቅመው።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ቻርተር ሲሻሻል አንድን ሰው ከግምት በማስገባት (ሰውየው ማንም ይሁን ማን) መሆን አልነበረበትም። በዚያ ላይ ምክትል ከንቲባውን ከምክር ቤት አባል ውጭም ሊሆን እንደሚችል የተሠጠው ምክንያት አሳማኝ አልነበረም።
በአጭሩ የአዲስ አበባ ከንቲባ ተግባራትን እደዲሠሩ የተሾሙትን ኢንጂነር ታከለ ኡማን የብሔር ማንነታቸውን መሠረት በማድረግ ያለው ክርክር ውጥረት መፍጠር እንጂ ሌላ ፋይዳ የላቸውም ። መርሳት የሌለብን  ውጥረትን  የሚናፍቁ በርካታ መሆናቸውን ነው።
Filed in: Amharic