>

ከቀናት በኋላ የስብሃት ነጋ ህልም አፈር ድሜ ይበላል፤ የአባይ ፀሀዬ ትብታብ ይበጣጠሳል!!! (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ከቀናት በኋላ የስብሃት ነጋ ህልም አፈር ድሜ ይበላል፤ የአባይ ፀሀዬ ትብታብ ይበጣጠሳል!!!
ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን
ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስቲያን የታየው ልብን በደስታ የሚሞላ ነው:: የአንድ ቤተክርስቲያን አባቶች በህወሀት ምክንያት ከሩብ ክፍለዘመን በላይ የተኳረፉበት: የተለያዩበት ምዕራፍ ሊዘጋ ከጫፍ የደረሰ ይመስላል:: በገብርዔል ቤተክርስቲያን አባቶቹ አብረው ሲያስቀድሱ: አንድ ገበታ ላይ ቀርበው ማዕድ ሲቆርሱ: ሲሳሳቁና ሲደሰቱ ያዩ ምዕመናን በዕምባ ተራጭተዋል:: በደስታ ሲቃ ውስጥ ሆነው አልቅሰዋል:: ስሜቱ ልዩ ነበር:: ከቀትር በኃላም የነበረው መረሃግብር በአባቶቹ ፍቅርና ሰላም መውረድ ደስታና ሀሴት የሞላው ጉባዔ ተካሂዷል:: ተስፋው ጠንካራ ነው:: ዕርቅ ይወርዳል። ሰላም ይሰፍናል። ደስታም ይሆናል።
ለሁለት የተከፈሉት አባቶች ወደአንድ የመምጣታቸው ነገር መስመር ይዟል:: ከሀገር ውስጥና ከባህር ማዶ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆችና ጉዳዩን በቅርበትና በርቀት ሲከታተሉ የኖሩ አያሌ ኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮአቸውን ከዋሽንግተን ዲሲ ላይ ተክለዋል። ከአንድ ሳምንት በኋላም ኢትዮጵያ ታላቁን ብስራት ትሰማለች።
 የስብሃት ነጋ ህልም አፈር ድሜ ይበላል:: የአባይ ፀሀዬ ትብታብ ይበጣጠሳል። ቤተክርስቲያኒቱ የካድሬ መፈንጪያ የመሆኗ አሳዛኝ ታሪክ ይዘጋል። ቤተክህነትና ቤተመንግስት ግልጽ ድንበር የሚያበጁበት አዲስ ታሪክም ይጻፋል። ዶ/ር አብይ አህመድ የዚህ ታላቅ ዕርቅና ሰላም ሻምፒዮን ሆነው በታሪክ ይመዘገባሉ። እንዲህም ብለዋል ” የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የእናንተ ብቻ እንዳትመስላችሁ። የሁላችንም ናት። ሰላሟ ለኢትዮጵያም ሰላም ይሆናል።” በእርግጥም የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል።
ጉባዔው እንደጅማሬው ፍጻሜው ያማረ ይሆን ዘንድ እመኛለሁ። የዛሬው የምዕመናን ደስታ በኢትዮጵያ ምድር የሚታይ ሆኖ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ከደስታው የሚካፈሉበት ጊዜ ቅርብ እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ። ለዚህ መሳካት እጃችሁን ያስገባችሁ በሙሉ ምስጋና ይገባቸኋል። ጠ/ሚር አብይ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች በኩል የጀመሩት ተመሳሳይ የሰላምና የእርቅ መንገድ በድርብ ድል ኢትዮጵያን የሚያደምቃት በመሆኑ ልዩ አክብሮት ይገባቸዋል።
በተረፈ በድፍረት ልንነጋገርባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ መዘንጋት አይገባንም። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ስር ሰደው፡ መረባቸውን ዘርግተው ከማይቀለበስበት ደረጃ ለመድረስ ጉዞ የጀመሩ፡ ፍንጭ ያሳዩ አንዳንድ ችግሮች ላይ ደፍረን ልንወያይ ይገባል። የጠ/ሚሩን ልፋት የሚያኮስሱ፡ ህልምና ራዕዩን ሊያጨናግፉ የሚፍጨረጨሩ ሃይሎች መኖራቸውን እየታዘብን ነው። ስለነገው መነጋገር መጀመር አለብን። ለውጡ እንደጀመረ እንዲዘልቅና መጨረሻው ያማረ እንዲሆን ከዚህ በኋላ ምን መደረግ አለበት የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም። ለውጡን ይጎዳዋል በሚል በስጋት የምንዝጋቸው ጉዳዮች ነገ ከነገ ወዲያ  ውድ ዋጋ ሊያስከፍሉን እንደሚችሉ መታወቅ አለበት።
ምሁራኖቻችን ሀሳብና አቅጣጫ ይጠቁሙ ዘንድ ይጠበቃሉ። ፍጹም አወዳሽና ፍጹም ወቃሽ የሆነው ሁለቱ የምሁራን ጎራዎች ተሰብረው ወደ መሀል መምጣት አለባቸው።  ምሁራኖቻችን ከድብታው ነቅተው ለውጡን በትክክለኛ ጎዳና ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማገዝ የሚጠበቅባቸው ዛሬ ሳይሆን ትላንት ነበር። አሁንም አልረፈደም። እኛን የሚዲያ ሰዎችን ቅረቡና ሀሳብና ዕውቀታችሁን አካፍሉን። መሾኮርመሙ ሀገርን እየጎዳ ነውና። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስከአሁን ጉዞ የተሰነቀው ተስፋ በምሁራን በታሸና በተመከረ አቅጣጫ መታጀብ ካልቻለ አደጋው ከባድ ነው። የምሁራን ያለህ አታስብሉን!
 በእርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን መሀሉ ላይ ነን። ቅዱስ መጽሀፉ እንደሚለው መሀሉ ላይ ባለ አይፈረድም። መሀሉ ላይ ወጀብ አለ። አስፈሪ ማዕበል አለ። እሳተ ጎሞራ ተደቅኗል። ግን እንሻገራለን። በተስፋ ተነስተናል:: መዳረሻችንን እናውቀዋለን:: በመሃል ስለሚገጥመን እርግጠኞች አይደለንም:: መሀሉ አልተነገረንም:: ከመከራው አልፈን፡ ከድቅድቁ ጨለማ ተሻግረን፡ እሳትና ወጀቡን ከኋላችን ሸኝተኝ ወደ መዳረሻችን እንተማለን። ለዚህም ከዘረኝነት የጸዳ ስንቅ እንያዝ። በዘር መርዝ ያልተበከለ ውሃችንን በኮዳችን እንሙላ። ስንለያይ እንደክማለን። በአጭር እንቀጫለን።  በአንድነት ግን መሀሉን እንሻገራለን።
Filed in: Amharic